1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ታብታብ፤እየተዘወተረ የመጣው ዲጅታል ገንዘብ ማግኛ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 3 2016

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የክሪፕቶከረንሲ ወይም ዲጅታል ገንዘብ ለማግኘት ወጣቶች ብዙ ጊዚያቸውን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ ያሳልፋሉ።ይህንኑ ዲጅታል ገንዘብ ለማግኘት በተለይ «ታብታብ» የሚባለው ዲጅታል መድረክ በአሁኑ ወቅት እየተለመደ ነው።ለመሆኑ ይህ ዲጅታል መድረክ ገንዘብ ያስገኛል ወይ? ጥቅም እና ጉዳቱስ? ሕጋዊነቱስ?

https://p.dw.com/p/4i7by
Symbolbild Bitcoin
ምስል Dado Ruvic/REUTERS

ታብታብ፤እየተዘወተረ የመጣው የዲጅታል ገንዘብ ማግኛ


የቴክኖሎጂ እድገት የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘዬ  በእጅጉ እየለወጠ ይገኛል።ቴክኖሎጅ ከለወጣቸው የሰው ልጆች መስተጋብሮች መካከል የንግድ እና የመገበያያ ዘዴ አንዱ ነው። በዚህ በዘርፍ የዘመኑ ቴክኖሎጅ ከወለዳቸው አሠራሮች መካከል «ክሪይፕቶከረንሲ»የሚባለው ዲጂታል ገንዘቦችን ለመገበያያነት የማዋል ዘዴ አንዱ ነው።ክሪፕቶ ከረንሲ  በኮምፒዩተር አውታረመረብ በኩል ለመገበያያነት እና ለዝውውር  የተነደፈ ዲጂታል ምንዛሬ ሲሆን፤  በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሃገራት ሰዎች በክሪፕቶከረንሲዎች አማካይነት ክፍያ መፈጸም እየተለመደ መጥቷል።ነገር ግን ይህ ዲጅታል ገንዘብ የሳይበር ደህንነት ባለሙያው አቶ ብሩክ ወርቁ እንደሚሉት እንደ መንግሥት ወይም ባንክ ባሉ ማዕከላዊ ተቋማት  ቁጥጥር የማይደረግበት ነው።መርካቶን በስልካችን

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በርካታ ክሪፕቶካረንሲዎች  ያሉ ሲሆን  በስፋት ከሚታወቁት መካከል «ቢትኮይን» የሚባለው ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያም እነዚህን መሰል ክሪፕቶ ከረንሲዎች ለማግኘት  በበይነመረብ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም  እየተለመደ መጥቷል። ከነዚህም መካከል በአሁኑ ወቅት ብዙ መነጋገሪያ የሆነው «ታብ ታብ» የሚባለው ዲጅታል መድረክ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በ«ታብ ታብ» አማካኝነት የክሪፕቶከረንሲ ወይም ዲጅታል ገንዘብ ለማግኘት ወጣቶች  ብዙ ጊዚያቸውን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ ሲያሳልፉ ይታያል። ስለዚህ ዲጅታል መድረክም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተደጋግሞ ይወራል።አቶ ብሩክ እንደሚሉት ሰዎች መነሻ «ክሪፕቶ ከረንሲ» ወይም ዲጅታል ገንዘብ የሚያገኙት በግዥ፣ በስጦታ ወይም በሽልማት መልክ  አልያም ሥራ ሠርተው በክፍያ መልክ ሊሆን ይችላል።

አቶ ብሩክ ወርቁ፤የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ
አቶ ብሩክ ወርቁ፤የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያምስል Privat

ያም ሆኖ «ታብታብ» በትክክል ገንዘብ ያስገኛል ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ገንዘብ ማስገኘቱ እንዳለ ሆኖ የራሱ ስጋቶችም አሉት።
የክሪፕቶከረንሲ የማግኛ ሂደትን ስንመለከት የግለሰቦች የገንዘብ ባለቤትነት መዝገቦች በዲጂታል ደብተር ውስጥ ይቀመጣሉ። ይህም የግብይት መዝገቦችን ለመጠበቅ፣ ተጨማሪ ሳንቲሞችን ለመፍጠር እና  ለመቆጣጠር ፣ የገንዘብ ባለቤትነት ዝውውርን  ለማረጋገጥ  በኮምፒዩተር የታገዘ  ጠንካራ የውሂብ መሰረት/ወይም ዳታ ቤዝ/ አለው።አሳሳቢው የኦንላይን ባንክ ዘረፋ
«ብሎክ ቼይን» በተባለው ቴክኖሎጅ ላይ ተመስርቶ ምዕናባዊ ዲጅታል ገንዘብ የማሰባሰብ ሂደት «ማይኒንግ» ወይም ማዕድን ማውጣት የሚል አቻ ትርጉም የያዘ ስም አለው። ማይኒንግ አዳዲስ ምዕናባዊ ዲጅታል ሳንቲሞችን ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ግብይቶችን ለመፈፀም ያገለግላል።  ገንዘቡን የሚያሰባስቡት ሰዎች ደግሞ «ማይነርስ» ወይም ማዕድን አውጭዎች ይባላሉ።
በዓለም ዙሪያም ይህንን ሚስጥራዊ ዲጅታል የገንዘብ ዝውውር የሚመዘግቡ፣ የሚያረጋግጡ እና ደህንነቱን የሚጠብቁ  ግዙፍ እና ያልተማከለ የኮምፒውተር ትስስር ያላቸው ምዕናባዊ ደብተሮችም አሉ። በዚህ መንገድ ክሪፕቶከረንሲ  ያለው ሰው ግብይት መፈፀም  ይችላል። ነገር ግን አቶ ብሩክ ግብይቱ የተገደበ ነው ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በርካታ ክሪፕቶካረንሲዎች  ያሉ ሲሆን  በስፋት ከሚታወቁት መካከል «ቢትኮይን» የሚባለው ዋነኛ ተጠቃሽ ነው
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በርካታ ክሪፕቶካረንሲዎች  ያሉ ሲሆን  በስፋት ከሚታወቁት መካከል «ቢትኮይን» የሚባለው ዋነኛ ተጠቃሽ ነውምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

ስለ ክሪፕቶከረንሲ  የማይዳሰስ ዲጂታል ገንዘብ  ሲነሳ ሕጋዊነቱ አብሮ ይነሳል፤ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ባወጣው መግለጫ፤ በዚህ  የማይዳሰስ ምዕናባዊ ዲጅታል ገንዘብ መገበያየት በሀገሪቱ እየተስፋፉ መምጣቱን ገልጾ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ይፋዊ መገበያያ ገንዘብ ብር በመሆኑ ክሪፕቶከረንሲ በሀገሪቱ ተቀባይነት የሌለው ሕገ ወጥ ድርጊት መሆኑን አስታውቋል።
ስለሆነም በየትኛውም የክፍያ መፈፀሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት እንደማቻልም በወቅቱ አስጠንቅቆ ነበር። 
ምንም እንኳን ባንኩ ይህን ይበል እንጂ በዘመነ  ዲጅታል እና በአጽናፋዊ ትስስር ማለትም ግሎባላይዜሽን ነገሮችን በክልከላ  ለመቆጣጠር መሞከር አስቸጋሪ በመሆኑ  ተገቢ ፖሊሲ ማውጣት አስፈላጊ  እንደሚሆን አቶ ብሩክ ያስረዳሉ።

ከዚህ ባሻገር ይህ ዲጅታል ገንዘብ በመረጃ ሰርሳሪዎች ለስርቆት የተጋለጠ ሲሆን፤ይህንን በተመለከተ ገዢ ሕግ ባለመኖሩም  በክሪፕቶከረንሲ  በሚያደረግ  ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው ግለሰቡ ብቻ ነው።የአፍሪቃን የኤልክትሮኒክ ግብይት አቅምን መክፈት
በሌላ በኩል በክሪፕቶከረንሲ በሚደረጉ ግብይቶች ላይ የሻጭ እና የገዢ ማንነት ይፋ ሳይደረግ ግብይት ለመፈፀም የሚያስችል በመሆኑ፤ ቀረጥ የማይከፈልበትም ሲሆን፤ ሕገ ወጥ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የተከለከሉ ነገሮችን ሊገዙ እና ሊሽጡበት እንደሚችሉም ባለሙያው ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብንም ሕጋዊ አድርጎ ለመጠቀም ስለሚያስችል፤ለሃገራት ትልቅ ስጋት ደቅኗል።አቶ ብሩክም በግለሰብም ይሁን በማኅበረሰብ ደረጃ  ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ናቸው።

ክሪፕቶከረንሲ ወይም ምዕናባዊ ድጅታል ገንዘብ ለመረጃ ሰርሳሪዎች ለስርቆት የተጋለጠ ነው።
ክሪፕቶከረንሲ ወይም ምዕናባዊ ድጅታል ገንዘብ ለመረጃ ሰርሳሪዎች ለስርቆት የተጋለጠ ነው።ምስል STR/NurPhoto/picture alliance

እንደ ቻይና፣ ኢራን፣ቦሊቪያ እና ኮሎምቢያ ያሉ ሃገራት እንደ ቢት ኮይን ያሉ ክሪፕቶከረንሲዎችን በይፋ የከለከሉ ቢሆንም፤ እስካሁን ግን ሌሎች ሃገራት ውግዘትም ሆነ ምስጋና ከማቅረብ ተቆጥበው ጉዳዩን በጥሞና እያጤኑት ነው።ምክንያቱም የክሪፕቶከረንሲ ግብይት ድንበር በሌለው የበይነመረብ  ዓለም የሚካሄድ በመሆኑ መንግሥታት ቁጥጥር ለማድረግ ያዳግታቸዋልና። ከዚህ አንፃር የአጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት ከባለሙያዎች ለጊዜው የቀረበ የመፍትሄ ሃሳብ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ
ሸዋዬ ለገሠ