ታሪካዊው የማላዊ የድጋሜ ምርጫ፤የኮንጎ የቅኝ ግዛት ጠባሳዎች | አፍሪቃ | DW | 29.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ታሪካዊው የማላዊ የድጋሜ ምርጫ፤የኮንጎ የቅኝ ግዛት ጠባሳዎች

ደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማላዊ ያለፈው ዓመት 2019 ዓ/ም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደች ቢሆንም ምርጫው ፍትሃዊ አልነበረም በሚል ሀገሪቱ ለወራት በተቃውሞ ስትታመስ ቆይታለች።ይህ ውዝግብ መቋጫ እንዲያገኝ ጉዳዩ ወደ ሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ተመርቶ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:24

ታሪካዊው የማላዊ የድጋሜ ምርጫ፤የኮንጎ የቅኝ ግዛት ጠባሳዎች

ደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ማላዊ ያለፈው ዓመት 2019 ዓ/ም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደች ቢሆንም ምርጫው ፍትሃዊ አልነበረም በሚል ሀገሪቱ ለወራት በተቃውሞ ስትታመስ ቆይታለች።ይህ ውዝግብ መቋጫ እንዲያገኝ ጉዳዩ ወደ ሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ተመርቶ ነበር።የህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት ዳኞችም ምርጫው ወጥነት የጎደለው በመሆኑ ውጤቱ ተሰርዞ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ያለፈው የካቲት ወስነዋል። በውሳኔው መሰረትም ያለፈው ማክሰኞ  የሀገሪቱ ዜጎች ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ በድጋሚ ድምፅ ሲሰጡ ውለዋል።
በጎርጎሮሳዊው ግንቦት ወር 2019 በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሙታሪካ 38,6% ሁለተኛው ዕጩ ቻካዌራ 35% እንዲሁ ምክትል ፕሬዳንቱ ሳሎስ ቺሊማ 20% ድምፅ አንዳገኙ ይፋ ቢደረግም፤ ቺሌማ ምርጫው ፍትሃዊ አልነበረም በሚል ከፕሬዝዳንቱ ጋር እሰጣገባ ገቡ። የሀገሪቱ የህገ-መንግስት ፍርድ ቤትም  የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን መሰረዝና መደለዝን ጨምሮ  ሌሎች በርካታ ጉድለቶች ተገኝቶበታል በሚል ምርጫው እንዲሰረዝ ያደረገ ሲሆን፤ በድጋሚ አሸንፌያለሁ ብለው  ስልጣናቸውን ለማደላደል ቃለ መሃላ  ፈፅመው የነበሩት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ ውሳኔውን ተቃውመው ለከፍተኛው ፍርድቤት ይግባኝ ጠይቀው ነበር።ሆኖም ግን የሀገሪቱ ፍርድ ቤቱ የፕሬዚዳንቱን ቅሬታ ውድቅ በማድረግ ምርጫው እንዲደገም  ውሳኔ አሳለፏል።ይህ ውሳኔ  በብዙዎች ዘንድ ለአፍሪቃ በዲሞክራሲ ብዙ ማይል ርቀት እንደመጓዝም ተቆጥሯል።በማላዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠይቁ ሰልፎችን የሚያስተባብረው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት መሪ ጊፍት ቴሬፕንስ ይህንን ይጋራሉ።
«የፍትህ አካላት አስፈላጊ ውሳኔዎችን ለመወሰን በተለይ ምርጫዎች ላይ  ገለልተኛ ሆነው አይተናል።  ከዚህ በተጨማሪ ማላዊውያን በሀገሪቱ ውስጥ ሲያደርጓቸው የነበሩ ሰልፎችም የሚያሳዩትም ዲሞክራሲያችን እያደገ መሆኑን ነው ።»
ያለፈው ማክሰኞ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ  የተወዳደሩት ከጎርጎሮሳዊው 2014 ጀምረው ሀገሪቱን በመምራት ላይ  የሚገኙት ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ፣ ከማላዊ  ተራማጅ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ላዛሩስ ቻክዌራ ከተቃዋሚው የማላዊ ኮንግረንስ ፓርቲ እንዲሁም ብዙም እውቅና የሌላቸው ፒተር ኩዋኒ ከማባኩዋኩ ከንቅናቄ ለዲሞክራሲ ናቸው፡፡የተቃዋሚ ፓርቲው ቻክዌራ ያሸንፋሉ  የሚል ግምት በአብዛኞች ዘንድ አለ።
በ2019ኙ የድህረ ምርጫ ሁከት አንዳንዶች ህይወታቸውን አጥተዋል የአካል ጉዳትና  የንብረት ውድመትም አስከትሏል። ስለሆነም በአብዛኞቹ ማላዊያን ዘንድ አዲሱ ምርጫ ከወራት ተቃዉሞ በኋላ ሀገሪቱ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንድትመለስ ሊያደርግ የሚችል አዲስ ጅምር ይሆናል የሚል ተስፋ አለ ፡፡
«ጥሩ ነገሮች ይመጣሉ። ምክንያቱም  ይህ መንግሥት ሁሉንም ነገር አበላሽቶብናል። ሁሉም ሰው እያለቀሰ ነው። እኛ ይህንን እና ያንን እየሞከርን ነው ነገር ግን እየረዳን አይደለም ፣ ስለሆነም አሁን ከሚመጣው መንግስት ለውጥ እየጠበቅን ነው ተስፋም አለን፡፡»
ማላዊ ድህነትን እና ሙስናን ለመዋጋት እየታገለች ያለች ሀገር ስትሆን፡፡በሙስና ጠቋሚ ዝርዝር ውስጥ ከ189 ሀገሮች መካከል 123 ደረጃ ላይ በሰብዓዊ ልማት አመላካች ዝርዝር ደግሞ 172ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የፖለቲካ ተንታኙ ብራይት ሙሃንጎ በምርጫው ወደ ስልጣን የሚመጣው ይህንን ችግር እንዲፈታ ይጠብቃሉ።
«የማላዊ ተራማጅ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ 60 በመቶ ድምፁን ያጣው በስልጣን ዘመኑ የተፈፀሙ የሙስና ፣የማህበራዊ አገልግሎት ችግር ፣የሀይል አቅርቦትና የኤለክትሪክ መብራት ችግር ሊሆን ይችላል።ስለዚህ የማላዊ ኮንግረንስ ፓርቲ ስልጣን ላይ መቆየት ከፈለገ እነዚህን ችግሮች መፍታት አለበት።»
ምርጫውን የተከታተለችው የዶቼ ቬለ የማላዊ ዘጋቢ ሚሪያም ካሊዛ  የዘንድሮው ምርጫ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር ሰላማዊ እንደነበር ገልፃ ፤ማሊያውያን ከአዲሱ ፕሬዝዳንታቸው ብዙ ይጠብቃሉ ትላለች። 
«ሰዎች ለውጥ ይጠብቃሉ።በአሁኑ ወቅት ሙስናና ጎሰኝነትን በመሳሰሉ ችግሮች መንግስት ይወቀሳል።እና ሰዎች ብዙ ይጠብቃሉ።ሰዎች መብታቸውን መጠቀም ይፈልጋሉ።ማላዉያን ነፃ መሆን አለባቸው ።ሰዎች የጎሳ ካርድ ሳይጠቀሙ ማላዊያን  ብቻ መሆን አለባቸው።»
በጎርጎሮሳዉያኑ ሰኔ 6 ቀን 1964 ነፃነቷን ከብሪታኒያ ያገኘችው ማላዊ የባህር በር የሌላት ሀገር ስትሆን  ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት።ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ የተመሰረተ ሲሆን የጤና የትምህርት እንዲሁም መሰረተ ልማቶች ያልተሟሉባት ሀገር ነች።

ግጭት፤ የንጉስ ሊዮፖልድ ውርስ በኮንጎ 

በመካከለኛው አፍሪቃ ክፍል የምትገኘው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች ሀገር ነች።ሀገሪቱ በወርቅ፣በዩራኔም ፣በመዳብና በአልማዥ ማዕድናትና የበለፀገች ስትሆን በጎማ ዛፍ ፣በጥጥ፣በቡናና ሌሎች ምርቶችም የታወቀች ነች። የውብ የተፈጥሮ ልምላሜና የከበሩ ማዕድናት ባለቤት የሆነችው ይች ሀገር ግን ለህዝቦቿ ልማትና እድገት ማምጣት ተስኗት መለያዋ  ግጭትና ድህነት ሆኗል።ለዚህም በሀገሪቱ የቅኝ ግዛት ዘመን የጣለባት ጠባሳ ቀላል አመሆኑ ይነገራል።
 በጎርጎሪያኑ 1885  በበርሊን ኮንፍረንስ አውሮፓውያን አፍሪቃን በቅኝ ግዛት ለማስተዳደር ሲከፋፈሉ ኮንጎ በቤልጄሙ ንጉስ ሊዮፖልድ ሁለተኛ እጅ ወደቀች።ንጉሱ ሀገሪቱን « ነፃ ግዛት» ብለው በመሰየም ራሳቸውን የሀገሪቱ ንጉስ አድርገው ሾመ።
ከዚያም የሀገሪቱ ህዝብ በባርነት የንጉሱ አገልጋይ ሲሆን የዝሆን ጥርስን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳሻቸው ሲቆጣጠሩ ቆዩ።በጨካኝ ገዥነታቸው የሚታወቁት ንጉስ ሊዮፖልድ የሀገሬውን ሰው የበይ ተመልካች መሆን ሳያንሰው  ከሞት ቅጣት እስከ እጅ መቁረጥ ድረስ የተለያዩ ዘግናኝ በደሎችን ይፈፀሙ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል። የኮንጎ ታሪክ ከዚህ መሰሉ ግፍ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ የማዕከላዊ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ትስስር አስተባባሪ  ጋዚነ አሚስ። 
«የዲሞክራቲክ ኮንጎ ታሪክ ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ ብዙዉን ጊዜ ከፍተኛ ግፍና ከኢፍትሃዊነት ጋር የተያያዘ ነው።የቤልጄም የቅኝ ግዛት አስተዳደር  ምንም አይነት የፖለቲካ ፣የትምህርታትና የማህበራዊ ኑሮ  እድገት እንዳይኖር የተቻለውን ሁሉ ጥረት አድርጓል።» 
ኮንኮ በጎርጎሪያኑ ሰኔ 30 ቀን 1960 ዓ/ም ከቅኝ ግዛት ነፃ ብትሆንም የቅኝ ግዛት ዘመን ጥሎባት ያለፈው የመከፋፈልና እርስበእርስ ያለመተማመን አባዜ ከ60 ዓመት በኃላም ቢሆን በእርስ በርስ ጦርነትና በድህነት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል።ለዚህም የቅኝ ግዛት ዘመን ፖሊሲ አስተዋፅኦ እንዳለው ጋዚነ ይናገራሉ።
«በተቃራኒው የቤልጂየም ቅኝ ግዛት አስተዳደር በደንበኝነትና እና በተለዬ  ጥቅምና ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ ፖሊሲ በሀገሪቱ ውስጥ ያራምድ ነበር። ስለዚህ ኮንጎ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ እንኳ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነበረች። ነፃነቷን ካገኘች ከ1960 ዓ/ም በኋላ አሁንም ድረስ በእውነቱ እንደ ነጻ ሀገር መሆን አልቻለችም። ግጭቶችና ጥቃቶች አሁንም ቀጥለዋል።» 
ሀገሪቱ ነጻነቷን ካገኘች ከስድስት የቀውስ አመታት በኋላ በ1965 ወደ ስልጣን የመጡት ሞቡቱ ሴሴ ኮ ኮንጎን  ለሶስት አስርተ ዓመታት ሲያስተዳድሩ የህዝቡን ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ በዝርፊያ ላይ ነበር በስልጣን ላይ የቆዩት።በ1997 ለህክምና ከሀገር በወጡበት በመፈንቅለ መንግስት ሎረን ዲሴሬ ካቢላ ፕሬዚዳንት ሆኑ።በ2001 ዓ/ም እኝህ ፕሬዝዳንት በጥይት የተገደሉ ሲሆን ልጃቸ ጆሴፍ ካቢላ በምርጫ  በ2006 ወደስልጣን መጥተዋል።ከብዙ ወራት ብጥብጥና ሁከት በኋላ በ2019 ዓ/ም ደግሞ በምርጫ ፊሊክስ ትሺከዲ ስልጣን ይዘዋል።ያም ሆኖ ከጥቂት ሊሂቃን በቀር አብዛኛው ህዝብ አሁንም ድረስ በአስከፊ ድህነት ይኖራል።ከ2004 ጀምሮ በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የእርስ በርስ ግጭት አለ። በዚህ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቅለዋል።ኮንጎ ከዚህ ሁሉ ችግር ጋር  60ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን አክብራለች።
የቤልጀሙ ንጉስ ሊዮፖልድ ሁለተኛ ሀውልት ሰሞኑን በአውሮፓ« የጥቁር ህይወት ዋጋ አለው»የተቃውሞ ሰልፈኞች ተሰባብሮ በእሳት ተቃጥሏል።በኮንጎ ህዝብ ላይ የፈፀሙት በደል  ግን ጠባሳው አሁንም ቀጥሏል።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic