1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታሪኩ ጌታቸዉ / ባላክ፤ ወጣቱ የኪነ-ጥበብ ሰዉ ከጅማ

ሐሙስ፣ ሰኔ 6 2016

በጅማ ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ክህሎታቸዉን የሚያዳብሩበት የ«እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብ» ኃላፊ ነዉ። ቀደም ሲል ክበቡ የኤድስን አስከፊነት እና ጥንቃቄዉን ለወጣቱ ለማስተማር በግብረሰናይ ድርጅት የተቋቋመ ነበር። ድርጅቱ ስራዉን ሲጨርስ፤ ወጣቱ ሌሎች የኪነጥበብ መክሊት ያላቸዉን ይዞ ክህሎታቸዉን ማዳበር ጀመረ።

https://p.dw.com/p/4h0p8
እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብ
እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብምስል Mother Reflection Art Club

ታሪኩ ጌታቸዉ / ባላክ፤ ወጣቱ የኪነ-ጥበብ ሰዉ ከጅማ

ታሪኩ ጌታቸዉ / ባላክ፤ ወጣቱ የኪነ-ጥበብ ሰዉ ከጅማ 

"እንደምነህ እግዜር ፣ ሰማይ ቤት እንዴት ነው? - "እመጣለሁ" ብለህ ፣ ቆየህሳ ምነው ? - እኛማ ይኸውልህ...- ለእልፍ አ'ላፍ አለቃ ፣ ማመልከቻ ፅፈን - ለወፈ ሰማይ ህዝብ ፣ መድረክ ላይ ለፍፈን - ፆለት ቤታችንን ፣ እኛው ላይ ቆልፈን - የምድር አተካራ ፣ ህግጋቱን አልፈን - ደብዳቤ ላክንልህ ! - አይንህን ካየነው ... - ሁለት ሽህ ዘመን ፣ እንደቀልድ አለፈ - የመምጣትህ ተስፋ እየኮሰመነ...- መቅረትህ ገዘፈ። እንደውም እንደውም.. - ‹‹በ'መጣለሁ ተስፋ ሁለት ሽ ዘመን ፣ ቀጥሮን ከጠፋ - በቀጠሮው ሰአት ፣ መምጣት ከተሳነው - "እግዜር አበሻ ነው እያሉ ያሙሃል ፣ እኔ ምን አውቃለሁ!?!"

ለእግዜር የተላከ ደብዳቤ ከተሰኘዉ በአሌክስ አብርሃም ከተደሰረሰዉ ረዘም ካለ ግጥም ቆንጠር አድርጎ ያቀረበልን እንግዳችን ወጣት ታሪኩ ጌታቸዉ ነዉ። በጅማ ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ክህሎታቸዉን የሚያዳብሩበት የ«እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብ» ኃላፊም ነዉ። ይህ ክበብ ቀደም ሲል የኤድስን አስከፊነት እና ጥንቃቄዉን ለወጣቱ ለማስተማር የተቋቋመ እንደነበር በተለይ በትወና ሞያ በድንቅ መነባንቡ የሚታወቀዉ ታሪኩ ጌታቸዉ ነግሮናል። ታሪኩ ጌታቸዉ በሚኖርባት ጅማ ከተማ የሚታወቀዉ በስሙ ሳይሆን ባላክ በሚለዉ ቅፅል ስሙም ነዉ። የእግር ኴስ ተጫዋች ነበርኩ፤ ልጆች ስሙን ያወጡልኝ በዝያን ግዜ ጠንካራ ተጫዋች ስለነበርኩ ነዉ ሲል ታሪኩ ታሪኩን አጫዉቶናል።  

ከ 13 ዓመት በላይ የሆነዉ ታሪኩ ጌታቸዉ የሚመራዉ የወጣቶች ክበብ፤ ብዙ ለኪነ-ጥበብ ፍቅር እና ተሰጦ ያላቸዉን ወጣቶች ድጋፍ እንዳደረገ ብሎም ወደ ለከፍተኛ ተቋማት ትምህርት እንዳበቃም ነግሮናል። ማዕከሉ በጅማ ለመጀመርያ ጊዜ የኤድስን አደገኛነት እና፤ ከኤድስ እንዴት መጠበቅ ይቻላል በሚል ሲሰራ በነበረ ግብረሰናይ ድርጅት የተቋቋመ ነበር። ወጣት ታሪኩ ጌታቸዉ እና ጓደኞቹ በድርጅቱ ዉስጥ የኤድስን አደገኛነት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያስተምሩ ቆይተዋል። የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ስራዉን ጨርሶ ከተማዋን ሲለቅ ወጣቶቹ የ«እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብ» በሚል የኪነ-ጥበብ ክህሎታቸዉን የሚያዳብሩበት ክክለብ ዉስጥ ሲሰሩ ቆይተዋል።

"Mother Reflection Art Club" in Jimma City, Ethiopia
ምስል Mother Reflection Art Club

ወጣቱ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪ ታሪኩ ጌታቸዉ፤ በታዋቂዉ የኪነ-ጥበብ መድረክ ጦብያ አዲስ አበባ ላይ ተጋብዙ በመድረክ ስራዎቹን አሳይቷል። የአንድ ሰዉ ተዉኔት ለማቅረብ በሌሎች መድረኮችም ተጋብዞ ነበር። ይሁን እና ከሁለት ዓመት በፊት በደረሰት አደጋ ምክንያት እግሩ ላይ ህመሙ በማገርሸቱ እንደልቡ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በኪነ-ጥበቡ መድረክ መሳተፍ አልቻለም።

የኪነ-ጥበብ መክሊቴን በቁም ነገር መጠቀም እፈልጋለሁ ያለን ታሪኩ ጌታቸዉ በተለይ በቴክቶኩ መንደር በሚያቀርባቸዉ ተዉኔታዊ መነባንቦች ሥነ-ግጥሞች ተወዳጅነትን እና እዉቅናን እያገኘ ነዉ። እኔ ቲክቶክ የቧልት መንደር ስለሚመስለኝ የጀመርኩት እጅግ ዘግይቼ ነዉም ሲል ነግሮናል።

እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብ
እናት ነፀብራቅ የኪነ-ጥበብ ክበብምስል Mother Reflection Art Club

በቲክቶኩ መንደር በጅሮንድ የሚል መለያ ስም ያለዉ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪዉ ታሪኩ ጌታቸዉ፤ በጅማ ከትዉልድ ስሙ ይልቅ ባላክ በሚለዉ እንደሚታወቅ ነግሮናል።  ይህ ስሙን ያገኘዉ ገና የ 13 ዓመት የእግር ኳስ ተጫዋች ታዳጊ ሳለም ነዉ።  

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ