«ታሪኩን የሰዉ ልጅ መስማት አለበት» ዋቱ ዋቴ | ባህል | DW | 15.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

«ታሪኩን የሰዉ ልጅ መስማት አለበት» ዋቱ ዋቴ

አዉቶቡስ ዉስጥ የገቡት የአሸባብ ታጣቂዎች የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ተጓዦችን ነጥለዉ አዉጥተዉ ለመግደል ሲጥሩ፤ አዉቶቡስ ዉስጥ አብረዉ ሲጓዙ የነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ጣልቃ ገብተዉ አፈሙዝ የተደገነባቸዉን ክርስትያን ተጓዦች ሕይወት ለማትረፍ ያደረጉት ፍልምያን የሚያስታዉስ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:29

ከዋቱ ዋቴ ፊልም ዋና አዘጋጅዋ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

ከሁለት ዓመት በፊት ኬንያ ዉስጥ መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረ አንድ አዉቶብስ ላይ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት ላይ ተመስርቶ የተሠራዉ «ሁላችንም» የሚል የኪስዋሂሊ ቋንቋ ስያሜን የያዘዉ ዋቱ ዋቴ የተሰኘዉ ፊልም ለፊልም ጥበብ ሥራ የዓለማችንን ታላቁን ሽልማት ለማግኘት መታጨቱ በፊልም ሥራዉ ከተሳተፉት አልፎ ለጀርመንም ሆነ ለኬንያ የፊልም እንዱስትሪ ታላቅ ኩራት ሆንዋል። የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮችን አሳፍሮ ኬንያን መሃል እያቆራረጠ ሰሜን ምስራቅ ኬንያ ማንዴራ በሚባል አካባቢ ላይ በአሸባሪዎች ጥቃት ስለደረሰበት የሕዝብ ማመላለሻ አዉቶቡስ ታሪክ ጀርመናዊትዋ የፊልም ሥራ ጥበብ ባለሞያ ካትያ ቤንራት በኪስዋሂሊ ቋንቋ ዋቱ ዋቴ ማለትም ሁላችንም የሚል ርዕስን ሰጥታ እዉነተኛ ታሪክን በፊልም ጥበብ የድኅረ ምረቃ ሥራዋን አቅርባለች። በፊልሙ ላይ የታጠቁ እስላማዊ አማፅያን አዉቶቡሱን ማንዴራ ላይ አስቁመዉ ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሁሉንም የክርስትና እምነት ተከታዮች መረሸን ያዙ።

«ሁላችንም» ማለት «ዋቱ ዋቴ» የተሰኘዉ የጀርመናዊትዋ በፊልም ጥበብ የድኅረ ምረቃ የመጨረሳ ስራ ማለት እስካሁን በዓለማቀፍ የፊልም ዘርፍ የተማሪዎች ኦስካር ሽልማትን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቶአል። ጀርመናዊትዋ የፊልም ሥራ ጥበብ ምሩቅዋ ካትያ ቤርናት በዋቱ ዋቴ የፊልም ሥራዋ ሃሙብርግ ከተማ በሚገኘዉን በፊልም ሥራ ተቋም መምህራንዋን ብቻ ሳይሆን እዉቅናን ያገኘችዉ በዓለሙ የፊልም ሥራ መድረክ በሆሊዉድም ለሽልማት የመጨረሻ ዙር እጩ ሆና መቅረቧ ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቶላታል።

« ቤቴ ዉስጥ ቁጭ ብዬ የግብር ሂሳብ መስራት ስለነበረብኝ እቤቴ ቁጭ ብዬ ወረቀት እያገላበጥኩ ሳለ ስልኬ ጮሆ ሳነሳ ከበቨሪሂልስ ነዉ እየደወልንዉ አሉኝ፤  ከሆሊዉድ እንደተደወለ ገባኝ፤ ከዝያም ነገሩኝ፤  ከዝያ በቃ…»

በኬንያዋ ንዴራ በሚባል ቦታ ላይ ተጓዦችን አሳፍሮ የነበረ አንድ አዉቶቡስ ዉስጥ የገቡት የአሸባብ ታጣቂዎች የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ተጓዦችን ነጥለዉ አዉጥተዉ ለመግደል ሲጥሩ፤ አዉቶቡስ ዉስጥ አብረዉ ሲጓዙ ከነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ጣልቃ ገብተዉ አፈሙዝ የተደገነባቸዉን ክርስትያን ተጓዦች ሕይወት ለማትረፍ ያደረጉት ፍልምያን የሚያስታዉስ ነዉ። ጀርመናዊትዋ የፊልም ስራ ባለሞያ ካትያ ቤርናት በኬንያ በሕዝብ ማመላለሻ አዉቶቡስ ላይ ስለደረሰዉ ጥቃትና ሙስሊም ተሳፋሪዎች ክርስትያኑ እንዳይገደሉ ስለመዋደቃቸዉ የሚዘረዝረዉን ዜና ያነበበችዉ ቀደም ሲል ጀርመን ዉስጥ በወጣ ጋዜጣ ላይ ነበር። ከዝያም ነዉ ርዕሱን በተመለከተ ጥናት አድርጋ ና ታሪኩን ጽፋ ፊልሙን ለመቅረፅ ወደ ኬንያ ያመራችዉ።

በኬንያ ገብታ ፊልሙን ለመቅረፅ አስራ አንድ ቀናት ቢፈጅብ የፊልም ሰራተኞች መታሰር ፤ የኤሌትሪክ መቆራረጥና የጄኔሪተር መበላሸት የመሳሰሉ ነገሮች ሥራዋን ከባድ አድርጎባት እንደነበር ተናግራለች። ዋቱ ዋቴ የተሰኘዉ ይህ የ 22 ደቂቃ ፊልም ለሽልማት ከታጨ በኋላ በእጩነት የቀረቡት የፊልም ጥበብ ሰራተኞች ታዋቂዎቹ የፊልም ሰራተኞች እና አክተሮች በሚገኙበት መድረክ የምሳ ግብዣ ተጠርተዉ ጀርመናዊትዋ የፊልም ስራ ባለሞያ ጉዞዋን ወደ ሎስ አንጀለስ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ሳለች ነበር ከዶይቼ ቬሌ ጋር ባደረገችዉ ቃለ-ምልልስ ስለሚደረገዉ የምሳ ግብዣ ከሽልማት አሰጣጡ ጋር ትስስር ይኖረዉ ይሆን ለተባለችዉ ጥያቄ ይህን መልስ ሰታ ነበር።

«ቀስ በቀስ ሁኔታ እዉን መሆኑን እየተቀበልኩ ነዉ። በርግጥ ምን እንደተከሰተ ገና በትክክል አላገናዘብኩም። ፌልሙ በሆሊዉድ ለሽልማት በእጩነት መቅረቡን በሰማን እለት፤ ፊልሙን ኬንያ ዉስጥ እዲታይ አድርገናል። ምክንያቱም በፊልሙ 95 በመቶ የሚሆኑት ተዋናዮች እና አቀናባሪዎች ኬንያዉያን በመሆናቸዉ ነዉ። በዚህ ምክንያት ብቻ ፊልሙ ታጨም አልታጨም በኬንያ እንዲታይ እና ፊልሙን በጋራ ለመመረቅ ወስነን ነበር። ለተመልካች ፊልሙ ከቀረበ በኋላ ከተመልካቹ ጠንካራ የሆነ ስሜትን እና አስተያየቶችን ነዉ ያገኘነዉ። በርግጥ ፊልሙ ለሽልማት መታጨቱን ከሰማን በኋላ ደስታዉ የላቀ ነበር። እንዲያም ሆኖ በርግጥ በእጩነት መቅረቡን ልቤ እስኪቀበለዉ እና ሁኔታዉን እስካብላላዉአንድ ሁለት ቀናትን ወስዶብኛል። አሁን እስከ ወድያኛዉ ማንም የማይሽረዉ የሰራሁት ፊልም ለኦስካር ሽልማት የታጨልኝ የፊልም ስራ ባለሞያ መሆኔን አረጋግጫለሁ። እናም ፊልሙ ለታዋቂ ሽልማት መታጨት የፊልም ሰራተኛ ቡድኑ በጣም የምንወደዉን ሥራችንን በቀጣይ እንድንሰራ ፈቃድ የተሰጠን መሆኑን የሚረጋገጥበት ነዉ ብዬ አምናለሁ።»    

ዋቱ ዋቴ በተሰኘዉ ፊልሞ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ለህይወታቸዉ ስጋት ላይ ወድቀዉ አንዱ ለአንዱ ተገን ሆኖ ሲፋለም ያሳያል። ይህ ፊልም በሰሩበት ጊዜ በጀርመን የስደተኞች ጉዳይn በተመለከተ ከፍተኛ ክርክርና ዉይይት እየተካሄ ነበር ። ከዚህ አንፃር ፊልሙ ምን አይነት ሚናን ይጫወታል ብለሽ ታምኛለሽ ተብሎ ከዶይቼ ቬለ ለቀረበላት ጥያቄ ካትያ ቤርናት ፤ «የስደተኞች ጉዳይን በተመለከተ በጣም የረበሸኝ ነገር ስደተኞችን ላለመቀበል የነበረዉ ክርክር፤ ዉይይት እንዲሁም የሚሰነዘሩ የተለያዩ ተቃራኒ አስተያየቶች በመስማቴ ነበር። ይህ አይነቱን ስሜቴን አብሪአቸዉ ያለሁት የፊልም ሰራ ቡድን አባላት ሁሉ የሚጋሩት ነዉ። ሰዎች ሌላ ኃይማኖት በመከተላቸዉ አልያም ከሌላ ሃገር ስለመጡ ብቻ አናስገባም፤ አልያም አንቀበልም፤ ብሎ መከልከል የማንቀበለዉ ነገር ነዉ። ሰዎችን ወደ ሃገራችን አናስገባም የሚለዉን ሃሳብም ሙሉ በሙሉ እቃወማለሁ። ሰዎች ርዳታችንን ሲፈልጉ እና በርግጥም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከሆኑ መረዳዳት አስፈላጊ ነዉ የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ርዕስ ላይ ብዙ መነጋገርና መወያየቱ አልያም በጉዳዩ ላይ አንድ የአሰራር እቅድና ሕግን በማዉጣቱ  ላይ እስማማለሁ። ነገር ግን ፈጽሞ መከልከሉ ትክክል አይደለም ወደ ሃገራችን ሽብርተኝነት እንዲገባ የሚያደርግ ጉዳይ ነዉ። እኛ በፊልም ያቀረብነዉ ታሪክ በጣም  ጠንካራ መልክትን ያዘለ ነዉ። ከሁሉ በላይ ግን ታሪኩ መከሰቱን ስናይ የሚያሳዝንና በጣም የሚያባባ ሆኖ እናገኘዋለን። ሰዎች እርስ በራሳቸዉ መደጋገፋቸዉን የሚያሳይ ጠንካራ መልክት ያዘለ  ታሪክም ነዉ። ይህ ታሪክ በእዉን የተፈፀመዉ በድሎት እንደምንኖርበት ጀርመን ደኅንነቱ የተረጋገጠ ቦታ ላይ ባለመሆኑ ምክንያት፤  ታሪኩን በፊልም መልክ ለእይታ ለማቅረብ ተገፋፋሁ።»

በፊልሙ በአፍሪቃ የተፈፀመ እዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ነዉ ። ይህን ፊልም ለመቅረፅ ወደ አፍሪቃ ማለትም ኬንያ ለመጓዝ ከመነሳትሽ በፊት ምናልባትም ችግሩ በአፍሪቃ የተፈፀመ በመሆኑ ታሪኩን የራስ እንደማድረግ ስራ ይቆጠራል በሚል ሊከብድ ይችላል የሚል ጥርጣሪን ይዘሽ እንደነበር በድረገፅሽ ላይ ፅፈሽ ነበር። እዉነት ጥርጣሪዉ እና ስጋቱ ቦታዉ ላይ  እዉን ሆንዋል?

 

ታሪኩ ኬንያ ዉስጥ የተፈፀመ በመሆኑ ፤ ታሪኩን በሚዛናዊ ሁኔታ ለመተረክ ትክክለኛዉን መንገድ አገኛለሁ? በሕጋዊስ ነኝ? በሚል በግሌ ጥርጣሪ ዉስጥ ገብቼ ነበር። በመጨረሻ ርዕሱን እንድወስድና እንድሰራዉ ትምምን ዉስጥ የገባሁት በኬንያ ከሚገኙ የፊልም ስራተኛ ቡድናት፤ የታሪክ ፀሐፊዎች ጋር ከተወያየሁ በኋላ፤ ታሪኩ በኬንያ ይፈፀም እንጂ ታሪኩ ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያለዉ መሆኑን ተገነዘብኩ በኋላ ነበር። ታሪኩ የሰዉ ልጆች ሁሉ እንዲህ ቢሆኑ ብዬ የምመኘዉ አይነት ብሻ ትምህርት የሚገኝበት ሆኖ አግንቸዋለሁ። የሰዉ ልጅ አንዱ ለአንዱ ደኅንነት ማሰቡ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ ነዉ። ይህ መሰረታዊ ግዴታ ደግሞ እኛ ጋርም ሆነ ሮም አልያም እስራኤል ተመሳሳይና መሰረታዊ ነገር ነዉ።  ይህ በመሆኑ ነዉ በፊልም መልክ ዳግም ታሪኩን እንድተርክ ያገፋፋኝ። ፊልሙ የአፍሪቃ ሽልማትን አግኝቶአል። ይህ የሚያሳየዉ ፊልሙ በአፍሪቃዉያኑ  ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ነዉ። ይህን ሁኔታ በተለይ በኬንያ በዓይናችን ያየነዉ እና የምንመሰክረዉ ጉዳይ ነዉ። በዚህም ይህን ታሪክ ከተፈፀመበት ማዕከል በፊልም መልክ ማቅረባችን እና ተቀባይነት በማግኘቱ በርግጥም ዉጤትን አስገኝቶልናል። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ»  

ዋቱ ዋቴ የተማሪዎች ኦስካር ጨምሮ እስካሁን ወደ ስድሳ የሚሆኑ ሽልማቶችን አግኝቶአል።  በፊልም ጥበብ ስራ ላይ በጥቂት ጊዜያት አይነቱን ስኬት ያልተለመደ ነዉ። ለዚህ አይነቱ ጥሩ ዉጤት ምስጥሪ ምን ይሆን ? ለሚለዉ ጥያቄ ወጣትዋ ጀርመናዊት ካትያ ቤርናት ጥያቄዉን ለመመለስ በርግጥ ከባድ መሆኑን በመግለፅ ነዉ የመለሰችዉ ። 

«ለዚህ መልስ ማግኘት በርግጥ በጣም ከባድ ነዉ። ምክንያቱም በአንድ አንድ ነገሮች ላይ ጥርጣሬዎች ስላሉኝ ነዉ።  በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ ሆኜ የምሰራዉን ነገር ለማኅበረሰቡ ለማስተላለፍ በእኔ በግሌ በጣም ይከብደኛል። በዚህ ረገድ ፈተና የሚገጥመኝ እኔ ብቸኛዋ ሴት ነኝ ብዬ አላምንም። እንድያም ሆኖ እኔ የሴቶች መብት መከበር እየጎለበተ ከመጣበት ዘመን ትዉልድ አንዷ ነኝ። በዚህም ምክንያት እናቶቻችን በቁርጠኝነት ያደላደሉልንን ይህን ትልቅ ቁም ነገር የማስቀጠል ግዴታ እንዳለብን አውቃለሁ።  ከጊዜ ወደ ጊዜ ሴቶች እራሳቸውን በተገቢው መልኩ በቁርጠኝነት መግለፅ የመቻላቸዉ ዉጤት ይህ ነዉ»          

በቅርቡ በርሊን ላይ በተካሄደዉ የዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል ላይም ሆነ በሆሊዉዱ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ወሲባዊ ትንኮሳን በተመለከተ የተቃዉሞ ዘመቻ ተካሂዶአል። ካትያ ቤርናት በፊልም ስራ መስክ ላይ ሳለሽ ወሲባዊ ትንኮሳ አጋጥሞሽ ያዉቃልን? ለሚለዉ ጥያቄ ፤

«በሴቶች ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ትንኮሳ በፊልም ስራ ገበታ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጋራ ስራ ቦታ የሚከሰት ጉዳይ ነዉ። አዎ እንዲህ አይነቱ ችግር ቀደም ሲል በመስክ ስራ ላይም ሆነ በግሌ አጋጥሞኛል። ይህ አይነቱን ሁኔታ በቀልድ መልክ በትክክለኛ አነጋገር መልስ መስጠት ቢቻልና ችግሩ ማቃለል ቢቻል ምኞቴ ነዉ። እስከዛሬ ድረስ በዚህ መልክ መልስ ለመስጠት ያደረኩኩት ጥረት ግን አልተሳካም። እናም እንዴት ማድረግ እንዳለብኝና ለችግሩ በቀላሉ መልስ መስጠት እንዳለብኝ አላዉቅም።» 

    

በተለይ በፊልሙ አለም የሚታየዉን ወሲባዊ ትንኮሳ በመቃወም #MeToo የተሰኘ ዘመቻ መካሄዱ በችግሩ ላይ ትኩረት እንዲሰጠዉ ሆንዋል። በፊልም ስራ መድረክ በሴቶች ላይ የሚካሄደዉ ይህ አይነቱ ትንኮሳ ይቀራል አልያም ሁኔታዉ ይቀየራል የሚል እምነት ይኖራት ይሆን?

«አዎ ሁኔታዎች እየተቀየሩ መሆናቸዉን አምናለሁ። አብዛኞች ዘመቻዉን ለራስ ጥቅም በማዋላቸዉ ትንሽ አመኔታ የታጣበት መስሎ ታይቶአል። ቢሆንም ዘመቻዉ ሁኔታዎችን ለማሻሻል እና ለጥሩ ነገር የቆመ መሆኑን አምናለሁ። በራስ መተማመንን በተመለከተ በጀርመንም ቢሆን ለዉጦች እየታዩ ነዉ። ዘመቻዉ አሁንም በይበልጥ ጥሩ ዉጤትን ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ። በዝያ ላይ በብዙ ሰዎች የሚወደዱትና ስራቸዉን የሚያደንቁላቸዉ እንደ ፊልም አክተርዋ Meryl Streep ያሉ ሰዎች በዚህ ዘመቻ ጀርባ የቆሙ ትልቅ ጉልበት በመሆናቸዉ በጣም ጥሩ ሆኖ አግንቸዋለሁ። ዘመቻዉን በተመለከተ ከሌላ አቅጣጫ ለሚሰነዘረዉ ከፍተኛ ስድብ ወቀሳ መልስ ሳይሰጡ  በአንፃሩ ችግሩን ተቋቁመዉ ነገሮችን ወደ ጥሩ ለመለወጥ መስራታቸዉን በጣም ወደጅዋለሁ።  በዚህም ምክንያት ሁኔታዉ በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ ነዉ ብዬ አምናለሁ።»

በመጨረሻ ለወጣት ጀርመናዊት የፊልም ጥበብ ባለሞያ የቀረበዉ ጥያቄ ጎልደን ግሎብስ እንዲሁም ግሪሚ በተሰኞች በዓለም አቀፍ የፊልም ሥራ ሽልማቶች ላይ ሴቶች ጥቁር ልብስንና ነጭ ጽጌሪዳ አበባን ይዘዉ በሴቶች ላይ የሚቃጣዉን ወሲባዊ ትንኮሳ ተቃዉመዋል። በቀጣይ ይህ አይነቱ ዘመቻ በዓለም አቀፍ መድረኮች ቢካሄድ አንቺም አብረሽ ይህን አይነቱን ዘመቻ የምትሳተፊ ይመስልሻል?

«ያለምንም ጥርጥር ። ሁልጊዜም ቢሆን ሳይመስለኝ ምንም ነገር አብሪ አልሰራም። ግን ጉዳዩ ትክክል ነዉ የሚል እምነት ካለኝ፤ እዉነት ነዉ፤ በአብሮነት አንድ ኃይልን መገንባት እንችላለን፤ ይኖርብናልም »

በ90ኛዉ የሆሊዉድ የኦስካር ሽልማትን ለማግኘት የታጨዉና በጀርመናዉያን እና ኬንያዉያን የተሰራዉ በእዉነታ ላይ የተመረኮዘዉ 22 ደቂቃ ፊልም እስከአሁን ወደ 60 የሚሆኑ ሽልማቶችን ለማግኘት መብቃቱ ሰዎች የበጎነት ታሪኮችን እዉን ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸዉ አመላካች መሆኑን ጀርመናዊትዋ የፊልም ሥራ ጥበብ ባለሞያዋ ካትያ ቤንራት ተናግራለች።  ሰዎች የደግነትና መደጋገፍ ታሪክን መስማት ይፈልጋሉ ስትል ፊልሙን በምሳሌ በመጥቀስ መሰል ተጨማሪ ታሪኮችን ለማየት ለማግኘት መሞከራችን እንቀጥል ስትልም ተማፅናለች። በዚሁ ፊልም ላይ ዋና ተዋናይ ከሆኑት ኬንያዉያን መካከል ተዋናይት ቻርሊ ካሮሚ እዉቅናን ያገኘች ባለሞያ ሆናለች። በጎርጎረሳዉያኑ ታህሳስ 21፤ 2015 ዓ,ም  ኬንያ ማንዴራ በተባለ አካባቢ በሕዝብ ማመላለሻ አዉቶቡስ ላይ የአሸባብ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 28 ሰዎች መገደላቸዉ ይታወሳል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዩ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች