ቲምቡክቱ ፤ ሓቻምናና ዘንድሮ | አፍሪቃ | DW | 11.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ቲምቡክቱ ፤ ሓቻምናና ዘንድሮ

በሰሜን ማሊ ፤ ሰሐራ ምፍረ በዳ ጫፍ ላይ የምትገኘው ጥንታዊቷ ገናና የንግድ ማዕከል ቲምቡክቱ፣ እ ጎ አ በ 2012 ፣ ከአክራሪ ሙስሊሞች እጅ ከወደቀች ወዲህ የከተማይቱ የንግድ እንቅሥቃሴ ከቶውንም ማንሠራራት እንዳልቻለ ነው የሚነገረው።

ጥንታዊቷ የንግድና የትምህርት ማዕከል ቲምቡክቱ የአሁኑ ይዞታዋ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ፋቲማቱ ኧል ሐሰን ይባላሉ፣ የ 5 ልጆች እናት ናቸው። ቲምቡክቱ ከተማ ዳር ፣ ከቤታቸው ውጭ አቧራማ ወለል ላይ ተቀምጠው በጥቂት የፕላስቲክ ከረጢቶች የታሸጉ ፥ ሽንኩርት፤ ቃሪያና በፕላስቲክ ጠርሙስ የሚሞላ ዘይት ይሸጣሉ። ቁጭት እንጂ፣ ምንም ዓይነት ርካታ አይሰማቸውም።ሰማያዊውን ጎድጓዳ ሳህናቸውን እያሳዩ በቂ ማሽላ እንደሌላቸው ያስረዳሉ።

«ጂሐዲስቶቹ፣ ሴቶች ማንኛውንም ነገር እንዳይሸጡ አገዱ፤ ከቤት እንዳንወጣም ከለከሉን፤ በዚህም ሳቢያ ብዙዎች ከተማይቱን ለቀው ወጥተዋል። አሁን ቀስ በቀስ እየተመለስን፤ ሥራችንን እንደገና በመጀመር ላይ ነን። ግን ቀላል አይደለም። ሥቃይ ነው ኑሮ! ሥራ ለማንቀሳቀስ የወረት ብድር ያስፈልገናል። ያለኝን ማሽላ መጠን ተመልከቱ! ይህንም ለመሸጥ አልችልም። ቀደም ባለው ጊዜ የዚህን 6 እጥፍ ማሽላ አላጣም ነበር።»

ከ 3 ዓመት በፊት ፋቲማቱ ኧል ሐሰን 6 ሠራተኞች ነበሯቸው። እ ጎ አ በሚያዝያ ወር 2012 አክራሪ እስላማውያን ታጣቂ ኃይሎችከተማይቱን ሲቆጣጠሩ ፤ ሴቶች መሥራት የለባቸውም ብለው ከለከሉ።አንዲት ጎረቤታቸው እንዲያውም የመደብደብ ዕጣ ነበረ የገጠማቸው። የተደበደቡት ቤታቸው አጠገብ ዳቦ ሲጋግሩ በመገኘታቸው ነበር።ኧል ሐሰንና ቤተሰባቸው እንዲሁም በዛ ያሉ ወዳጆቻቸው ለመሰደድ ተገደዱ። ወደ ቲምቡክቱ የተመለሱት ፣ እ ጎ አ በ 2013 መግቢያ ላይ የማሊና የፈረንሳይ ወታደሮች ጅሃዲስቶቹን ሲያባርሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ የከተማይቱ የንግድ እንቅሥቃሴ ቀጥ ብሎ ነበር ።ለወጣቶች ፣ አልፎ አልፎ ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ፣ የሥራ ዕድል የለም

ኧልሐሰንም እንደገና ሥራ ማንቀሳቀስ የጀመሩት፤ CARE የእርዳታ ድርጅት በሰጣቸው ብድር ነው። በቲምቡክቱ የ CARE ሠራተኛ ቦካሪ ዲያሎ እንዲህ ይላሉ።

«ቀውሱ፤ የአካባቢውን ኤኮኖሚ ክፉኛ አናግቶታል። በመጀመሪያ ብዙዎች ከተማይቱን ለቀው ተሰደው ነበር። የተሰደዱትም ፣ የሚሠሩባቸውን የኑሮ መመኪያ መሣሪያዎቻቸውን ትተው ነው። ጂሃዲስቶቹ አብዛኛውን ከጥቅም ውጭ አድርገውባቸዋል። »

ሳሌም ዑልድ ኧል ሃጂም ከተማይቱ አንዳች የማንሠራራት ምልክት እንደማይታይባት ነው የሚናገሩት። አሁን በጡረታ ዕድሜ ላይ የሚገኙት የታሪክ ፕሮፌሰር፤ ስለከተማይቱ በዛ ያሉ ታሪኮች ጽፈዋል። በተለይ የቲምቡክቱ ወርቃማ ዘመን ስለሚባለው! ከተማይቱ አንድ ዘመን ፤በጨው፤ በዝሆን ጥርስና በባሪያ ንግድ የገነነች ነበረች። በአሁኑ ጊዜ ቲምቡክቱ የንግድ እንቅሥቃሤ አይታይባትም ፤ ሱቆች እንደተዘጉ ናቸው ፍርሃትም ነግሷል ነው የሚባለው። የታሪክ ምሁር ሳሌም ዑልድ ኧል ሃጂ--

«ከጂሃዲስቶቹ ጎን ለጎን፤ ሕዝቡን የሚያሸብሩ ወሮበላ ሽፍቶችም ነበሩ።በተለይ ወደ ሞሪታንያ፤ አልጀሪያ፤ ሞፕቲ በሚያመራው ጎዳና ! ለዚህም ነው ፣ ነጋዴዎች፤ ወደ ከተማይቱ የማይመለሱት። በተለይ ዐረቦቹ፤ ብዙዎቹ ጂሃዲስቶች ናቸው ስለተባለ፣ ተመልሶ መምጣቱን ይፈራሉ።»

የዓለም ሕዝብ የባህል ቅርስ ወደተሰኘችው ጥንታዊ መስጊዶችና አብያተ መጻሕፍት ወዳሏት ታሪካዊ ከተማ ዝር የሚል አገር ጎብኚ(ቱሪስት)ም የለም። በሰሜን ማሊ መታገት፤ ወይም መዘረፍ እጅግ የተስፋፋ በመሆኑ!በሁለት ቀን ጉዞ በሚደረስበት መዲና ባማኮ የሚገኘው መንግሥትም የተዳከመ ነው።ሰፊውን ሰሜናዊውን ምድረ በዳማ ግዛት መቆጣጠር እንደተሳነው ነው።የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ተልእኮ (MINUSMA) አባላት የሚገኙት በታላላቅ ከተሞች ብቻ ነው።

እስከቲምቡክቱ የተዘረጋ የአስፋልት መንገድ የለም።ነጋዴይቱ ወ/ሮ ፋቲማቱ ኧልሐሰን ግን ብሩሕ ተስፋ ነው ያላቸው። «አክራሪ ሙስሊሞቹ ተባረዋል ።ዋናው ቁም ነገር ይህ ነው። የምሸጠውን ሸቀጣ ሸቀጥ ለመግዛት ጎረቤቶቼ ገንዘብ ባይኖራቸውም ፤ ሁኔታው እየተሻሻለ እንደምሄድ አልጠራጠርም» ነው የሚሉት ወ/ሮ ፋቲማቱ ኧል ሐሰን!

ተክሌ የኋላ/አድሪያን ክሪሽ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic