ቱኒዝያ ከመታመኛው ድምፅ በኋላ | አፍሪቃ | DW | 02.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ቱኒዝያ ከመታመኛው ድምፅ በኋላ

በቱኒዝያ በቅርቡ የመንግሥት ለውጥ ይደረጋል። ለመንግሥቱ ለውጥ ምክንያት የሆነው የሀገሪቱን ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተሀድሶ አጓተዋል በሚል ስልጣናቸውን እንዲለቁ በተደጋጋሚ ግዙፍ ግፊት አርፎባቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር ሀቢብ ኤሲድ ባለፈው ቅዳሜ የብዙዎቹን የምክር ቤት እንደራሴዎች የመታመኛ ድምፅ ማጣታቸው ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:59

ቱኒዝያ

ይህ ሁኔታ የሕዝብ ዓመፅ ከተካሄደባቸው ዐረባውያት ሀገራት ሁሉ ስርዓተ ዴሞክራሲን በመትከሏ እንደ አርአያ ለታየችው ቱኒዝያ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

የቱኒዝያ ጠቅላይ ሚንስትር ሀቢብ ኤሲድ በመታማኛው የድምፅ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደማያገኙ ግልጽ ነበር። ምክንያቱም፣ በጥምር መንግሥት ውስጥ የተጠቃለሉት አራት ፓርቲዎች የሀገሪቱን ተሀድሶ አጓተዋል በሚል ለሚወቅሱዋቸው ኤሲዲ በጠቅላላ ድምፃቸውን እንደማይሰጡዋቸው ቀደም ሲል አሳውቀዋቸዋል። በድምፅ አሰጣጡ ስነ ስርዓት ላይ ከ217 የምክር ቤት እንደራሴዎች መካከል ከተሳተፉት 191 መካከል 118 ድምፃቸውን ሲነፍጉዋቸው፣ 27 ድምፅ ከመስጠት ታቅበዋል፣ የደገፉዋቸው ሶስት ብቻ ነበሩ። በዚህም የተነሳ የ67 ዓመቱ ጠቅላይ ሚንስትር ኤሲድ ከ18 ወራት በኋላ ስልጣናቸውን መልቀቅ ተገደዋል።
« እኔ የመራሁት የዚህ መንግሥት ዓላማ አመራሩን ዘላቂ ማድረግ ነበር። ምክንያቱም የሀገሪቱ ሁኔታ ቀጣይ የሆነ አሰራር ያስፈልገዋል። ከዚህ የተለየ አሰራር ሁሉ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል። ለኤኮኖሚያችን ፣ እንዲሁም፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ለስማችን፣ በጣም መጥፎ ነው። »


የየትኛውም ፓርቲ አባል ያልሆኑት ሀቢብ ኤሲድ ግፊት ያረፈባቸው እጎአ የካቲት ፣ 2015 ዓም የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ከያዙ ወዲህ ሲሆን፣ የቱኒዝያ ፕሬዚደንት ቤጂ ኬይድ ኤሴብሲ ሳይቀሩ ከጥቂት ጊዜ በፊት በይፋ ድጋፋቸውን ነፍገዋቸዋል።
የቱኒዝያ ሕዝብ የቀድሞው ፕሬዚደንት ቤን አሊ እጎአ በ2011 ዓም ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ከተቋቋመው የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ብዙ ነበር የጠበቀው። ግን ብዙዎቹ ቱኒዝያውያን የጠበቁት አልተሟላላቸውም፣ አሁንም የኤኮኖሚ ቀውስ ሰለባዎች እንደሆኑ ይገኛሉ። በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበቱ እና ስራ አጥነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፣ የቱሪዝሙ ዘርፍ ሙስሊም አሸባሪዎች በጣሉዋቸው ጥቃቶች የተነሳ ተንኮታኩቶዋል። ብሩህ የወደፊት ዕድል የማይታያቸው ቁጣቸው የገነፈለ ብዙዎቹ የቱኒዝያ ወጣቶች በየጊዜው ለተቃውሞ ብለው አደባባይ ይወጣሉ። ከርሳቸው በፊት የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ይዘው የነበሩት የእስላማዊው «ኤናሀዳ» ፓርቲ አባል አሊ ላራዬድህ ጠቅላይ ሚንስትር ኤሲድ
ለነዚህ መሰል ችግሮች መልስ ያላስገኘ ደካማ መንግሥት ነው በሚል ቢወቅሱም፣ ኤሲዲ ቀላል ሁኔታ እንዳላጋጠማቸው ነው የገለጹት።
« እኛ ይኸ መንግሥት በሰራው ስራ ላይ አይደለም ድምፅ የሰጠነው። በምን ዓይነት ሁኔታ ስራውን እንዳከናወነ ስንመለከት፣ ያስመዘገበው ውጤት ተቀባይነት አግኝቶዋል። እርግጥ፣ ጉድለቶች ነበሩ። ይሁንና፣ አሁን የተጀመረው ጥረት ቀጣዩ መንግሥት ወደፊት እንዲራመድ እና አስፈላጊዎቹን ተሀድሶዎች እንዲያነቃቃ አዲስ እና የተሻለ ሁኔታ ይፈጥራል። »
«ኤናሀዳ» በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ቦታ ለማግኘት ተስፋ አድርጎዋል። ፕሬዚደንት ኤሴቢሲ ከተለያዩት ፓርቲዎች፣ ከአሰሪዎች ማህበር እና ከጠንካራው የሙያ ማህበራት ቡድን የተውጣጣ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲመሰረት ይፈልጋሉ። ይህ ሀገሪቱ በከፋ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ባንድ ወቅት ተሞክሮዋል። ሀሳቡን የሚደግፉት ኒዳ ቱኔስ የተባለው የጥምሩ መንግሥት አባል የወግ አጥባቂው ህብረት የምክር ቤት አንጃ መሪ ሶፍየን ቱቤል ትክክለኛው እጩ ሊቀርብ ይገባል ባይ ናቸው።

Tunesien, Beji Caid Essebsi

ፕሬዚደንት ቤጂ ኬይድ ኤሴብሲ


« የብሔራዊ አንድነቱን መንግሥት መርህ በተግባር የሚተረጉም ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ባለሙያም የሆነ መሪ በመፈለግ ላይ ነን። የሀቢብ ኤሲዲ መንግሥት መርህ ካስቀመጠው ዓላማው ከ10 ወይም 15% የማይበልጠውን ብቻ ከግብ ማድረሱ ነበር ድክመቱ። የኤኮኖሚውን ውጤት ስንመለከት በጣም የወደቀ ነበር። ኤኮኖሚውን ማሳደግ ይኖርብናል። »

የዐረቡ ዓለም በሕዝብ ዓመፅ ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ ፣ ቱኒዝያ የተሳካ ምክር ቤታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመከተልዋ ባካባቢው እንደ አርአያ ታይታለች። ለዚህም እጎአ በ2015 ዓም የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ለመሆን መብቃቷ ይታወሳል። ይሁንና፣ እንደ ግራ ፓርቲዎች ህብረት፣ ሕዝባዊ ግንባር አባል ጂላኒ ሀማሚ አስተያየት፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ መረጋጋት አሁን ስጋት ተደቅኖበታል።
«
የሀገሪቱ ጊዚያዊ ሁኔታ ይበልጡን እየተበላሸ መሄዱ አይቀርም፣ ምክንያቱም፣ አዲስ መንግሥት እስኪመረጥ ድረስ ገና ሁለት ወር መጠበቅ አለብን። በዚሁ ጊዜ ሀገሪቱን፣ ኤኮኖሚዋን እና የሕዝቧን ጥያቄ በተመለከተ ምንም የሚሰራ ነገር አይኖርም። »
ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚንስትር ሀቢብ ኤሲዲ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ ከተጣማሪ ፓርቲዎች ጋር ተተኪያቸውን የመምረጡን ምክክር ካጠናቀቁ በኋላ፣ የቱኒዝያ ፕሬዚደንት ኤሴብሲ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሰየም የአንድ ወር ጊዜ ይኖራቸዋል፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርም ካቢኔአቸውን ለምክር ቤት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። እስከዚያ የቱኒዝያ ፖለቲካ ባለበት ይቆያል የሚል ስጋት ተፈጥሮዋል።

ዱንያ ሳዳቂ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic