ቱኒዚያ፤ ከተቃዉሞ ሠልፍ ወደ ተቃዉሞ ሠልፍ | ዓለም | DW | 25.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ቱኒዚያ፤ ከተቃዉሞ ሠልፍ ወደ ተቃዉሞ ሠልፍ

የኑሮ ዉድነት፤ ሥራ አጥነት እና የአስተዳደር በደል ያንገፈገፈዉ የቱኒዚያ ወጣት መንግሥትን በመቃወም በየከተሞቹ አደባባዮች መሠለፍ ጀምሯል። የተቃዉሞ ሠልፉ የዛሬ አምስት ዓመት የቀድሞዉ አምባ ገነን ገዢ ዜን ኤል አቢዲን ቤን ዓሊን ከሥልጣን ያሰወገደዉን ሕዝባዊ አመፅ ያክል ጠንካራ አይደለም።

ይሁንና የሕዝባዊ አመፁ መንፈስ ከስሜቱ ያልጠፋዉ ወጣት ወደ አደባባይ እንዲወጣ የሚደረግለት ጥሪ እየተጠናከረ ነዉ። በተቃዉሞ ሠልፉና በጥሪዉ መሐል ሰዎች መገደላቸዉ ፅንፈኞች ሠላማዊዉን ትግል ለራሳቸዉ አላማ ይጠቀሙባታል የሚል ሥጋት አስከትሏል። ሰዎች መሞት-አስከሬኖች መቆጠር ጀምረዋል።ባለፈዉ ሐሙስ ካስሪን አዉራጃ በተነሳ ጠብ አንድ ፖሊስ ተገድሏል። የቱኒዚያ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር እንደሚለዉ ግጭት ባየለበት ሠልፍ ላይ ፅንፈኞችም ተካፍለዉ ነበር። ፅንፈኞች ሠላማዊዉን ተቃዉሞ ለዓላማቸዉ ስኬት ሊጠልፉት እንደሚችሉ መገናኛ ዘዴዎችም ሲያስጠነቅቁ ነበሩ።

ሐሙስ፤ የፖሊስ ነብስ የጠፋበት የተቃዉሞ ሠልፍ የተቀጣጠለዉ አንድ የ28 ወጣት ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ መሞቱ ነበር። ሪድሐ ያሕዩአን ሥራ ለመቀጠር አመልክቶ ነበር። ከቀጣሪዉ መስሪያ ቤት የማስታወቂያ ሠሌዳ ሲመለከት ሥሙን ካመልካቾች ሥም ዝርዝር ዉስጥ ያጣዋል። ሥሙ በመሠረዙ የበገነዉ ወጣት እዚያዉ ካስሪን አገረ-ገዢ ሕንፃ አጠገብ ከሚገኝ የኤሌክትሪክ ምሰሶ ላይ ወጣ። ወጣቱ ኤሌክትሪኩን ወይም በተገላቢጦሹ ኤሌክትሪኩ ወጣቱን ይያዝ አይታወቀም። ብቻ ሞተ።

Arbeitslose Jugend in Tunesien

ሥራ ያጡ ቱኒዚያዉያን ወጣቶች

የወጣቱ ሞት፤ ዕድሜ፤ ምክንያቱም ከዓምስት ዓመት በፊት እራሱን በእሳት አጋይቶ የቱኒዚያን ሕዝባዊ አብዮት ካቀጣጠለዉ መሐመድ ቡአዚዚ ጋር ተመሳሳይ ነዉ። የምሥራቅ ቱኒዚያይቱ አዉራጃ ካስሪን ከመሐመድ ቡአዚዟ ከተማ ሲዲ ቦዉዚድ ብዙ አትርቅም። ቡአዚዚ ያቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ የቱኒዚያን የረጅም ዘመን ገዢ ከሥልጣን አስወግዷል። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያጎነቁል፤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ምክንያት ሆኗል።

ለወጣቱ ግን ያዉ በገሌ አይነት ነዉ። ከ15 ከመቶ የሚበልጠዉ ሥራ አጥ ነዉ።ኑሮ ተወድዷል። ተስፋም የለም።«የተቃዉሞ ሠልፉ የሚጠበቅ ነበር» ይላሉ የቱኒዚያ የምጣኔ ሐብትና የማሕበራዊ መብት ማሕበር ሊቀመንበር አብዱረሕማን ሔድሒሊ«ወጣቱ ብዙ ጠብቆ ነበር። መንግሥት ግን ምንም ራዕይ የለዉም።» አከሉ።

የዶቸ ቬለዉ የመግሪብ አካባቢ የፖለቲካ ተንታኝ ሞንሴፍ ስሊሚ ደግሞ መንግሥት በመተቸት ጠንከር ይላሉ።

Proteste in Kasserine Tunesien

የተጋጋለዉ ተቃዉሞ

«መንግሥት ለለቃዉሞዉ የሰጠዉ ምላሽ የንቀት ነዉ።የካስሪንን አመፅ ያባባሰዉ ራሱ መንግሥት ነዉ።መጀመሪያ የተወሰደዉ እርምጃ የፀጥታ ችግር እንዳለ የሚያመለክት ነበር። በመሠረቱ በርካታ ሌሎች ጭግሮች አሉ። ማሕበራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ችግሮች። ከቱኒዚያ ማሕበረሰብ አብዛኛዉ ክፍል የያዘዉ ወጣቱ ይበልጥ ተገልሏል። ሥራ አያገኝም። በፖለቲካዉ ዉሳኔም ተሳትፎ የለዉም።»

የዛሬ አምስት ዓመት የቤን ዓሊን መንግሥት ከሥልጣን ያስወገደዉ ወጣት ሁሉንም ሲያጣ አደባባይ ቢወጣ አይደንቅም ባይ ናቸዉ-ስሊሚ። ተቃዉሞዉ ካስሪን ይበርታ እንጂ ላ ፕሬስ የተባለዉ የቱኒዚያ ጋዜጣ እንደዘገበዉ በሁሉም የሐገሪቱ ክፍሎች እየተዛመተ ነዉ።

የቱኒዚያ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ለወጣቶቹ ጥያቄ መልስ ያለዉን ዕቅድ አስተዋዉቋል። የመንግሥት ቃል አቀባይ ኻሊድ ቾኬት መንግሥታቸዉ በካስሪን አዉራጃ አምስት ሺሕ የሥራ-መስኮች እንደሚከፍት፤በ60 ሚሊዮን ዩሮ አንድ ሺሕ መኖሪያ ቤቶች እንደሚያሰራ ቃል ገብተዋል።

የፖለቲካ ተንታኝ ሚንሴፍ ስሊሚ ይሕ በቂ አይደለም ባይ ናቸዉ። የቱኒዚያ ፖለቲከኞች የርስ በርስ ሽኩቻቸዉን አቁመዉ ችግሩን መፍታት አለባቸዉ።

«ፖለቲከኞቹ እራስ ወዳድ ናቸዉ።በአብዛኛዉ የሚያስቡት የግል ሽኩቻቸዉን ነዉ። ወጣቱ ግን ከሕብረቱሰቡ ዉስጥ ወደ ጠርዝ እየተገፋ ነዉ። የፖለቲካዉ መደብ በግል ጥቅሙ የታሠረ ለመሆኑ ገዢዉ ፓርቲ ኒዳ ቱኒስ በግልፅ ያመለክታል።»

የቱኒዚያ ተማሪዎች ማሕበር መሪ ዋኤል ኑርም የመንግሥትን የሥራ-ፈጠራና የቤት ዕቅድ ዉድቅ አድርጎታል። ጠቅላይ ሚንስትር ሐቢብ ኢስድ ለወጣቱ ጥያቄ ሁነኛ መፍትሔ ካልሰጡ ሥልጣን መልቀቅ አለባቸዉ ባይ ነዉ። ተቃዉሞዉም ከሁለቱ አንዱን እስኪያገኝ ይቀጥላል።

የወጣቶቹ ተቃዉሞ ለፅንፈኞች በር ይከፍታል የሚለዉ ሥጋትም እየናረ ነዉ። ላ ፕሬስ እንደዘገበዉ በተለይ ማዕከላዊ ቱኒዚያ ዉስጥ ያደፈጡ ፅንፈኞች ተቃዉሞዉ በማጋጋም በቅጡ ያልጠናዉን የመንግሥን መዋቅር ለማናጋት መሞከራቸዉ አይቀርም። የፖሊሱ ግድያም የፅንፈኞቹን ማንሰራራት ጠቋሚ ነዉ።ስሊሚ ሥጋቱን ለማስቀረት መፍትሔ የሚሉት አሁንም በመንግሥት እጅ ነዉ።

«መንግሥት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሥርዓቱ ለቱኒዚያ ወጣቶችን ችግር ለማቃለል ፖለቲካዊ ፍቃደኝነቱ ያላቸዉ መሆኑን ማሳየት አለባቸዉ።»

ኬርሽተን ክሪፕ / ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic