ቱርክ ፣የአሸባሪዎች ጥቃትና በአውሮፓ ያላት ሚና | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 13.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ቱርክ ፣የአሸባሪዎች ጥቃትና በአውሮፓ ያላት ሚና

ባለፈው ቅዳሜ የ97 ሰዎች ህይወት የጠፋበት የአንካራው የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ማወዛገቡ ቀጥሏል ። የቱርክ መንግሥት ራሱን እስላማዊ መንግሥት (IS) ብሎ የሚጠራው ቡድን ጥቃቱን ሳይጣል አልቀርም ሲል የቱርክ ኩርዶችና የቱርክ ፕሬዝዳንት ተቃዋሚዎች ደግሞ ለጥቃቱ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:15

የቱርክ ሚና በአውሮፓ


በቱርክ ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና በሃገሪቱ የሚካሄዱ ግጭቶችም እንዲቆሙ ለመንግሥት ሰላማዊ ጥሪ ለማስተላለፍ ነበር ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት በቱርክ ዋና ከተማ በአንካራ ሰላማዊ ሰልፍ የተካሄደው ።የቱርክ መንግሥት ተቃዋሚዎችና ከቱርክ ነፃ ለመውጣት የሚታገሉት የኩርዶች ደጋፊዎች የተካፈሉበት ሰላም እንዲሰፍን ይጠይቅ የነበረው ይህ ሰላማዊ ሰልፍ ግን የሰላም ተፃራሪዎች ሰለባ ሆነ ።ሰልፈኞች መፈክሮቻቸውን አንግበው እየዘመሩ እና እየጨፈሩ የሰላም መልዕክታቸውን እያስተጋቡ በመሄድ ላይ ሳሉ በድንገት ከባድ ፍንዳታ ደረሰ ።
አንዴ ብቻ አልነበረም ተደገመ ። ከሰልፈኞቹ መሃል የተደባለቁ ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ባፈነዷቸው ቦምቦች የ97 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ 190 ውን ደግሞ አቆሰለ ። አደጋው ሁለቱ አጥፍቶ ጠፊዎች በታጠቋቸው እያንዳንዳቸው 5 ኪሎ ግራም በሚመዝኑ ሁለት ቦምቦች መድረሱን መንግሥት አስታውቋል።ኩርዳውያንና ተቃዋሚዎች ለቅዳሜው ጥቃት ተጠያቂው የቱርክ ፕሬዝዳንት የጠይብ ሬቼፕ ኤርዶሃን መንግሥት ነው ሲሉ ወዲያውኑ ነበር የከሰሱት ።ኩርዶችን የሚደግፈው የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር፣ መንግሥት ሁሉንም ነገር በሚቆጣጠርበት በሃገሪቱ ዋና ከተማ ይህ ዓይነቱ ጥቃት እንዴት በጠራራ ፀሀይ ሊፈፀም ይችላል ሲሉ በመጠየቅ ነበር ተቃውሞአቸውን ያሰሙት ። ሊቀመንበሩ ሴልሃቲን ዲሚትሪስ በምህፃሩ

AKP «የፍትህና የልማት ፓርቲ »የሚባለውን የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ፓርቲም ነፍሰ ገዳይ ብለውታል።
«ወፍ ዝር ሲል እንኳን የማያመልጠው መንግሥት ፣ በርዕሰ ከተማይቱ እምብርት የደረሰውን እልቂት መከላከል ሊሳነው አይገባም ነበር ። AKP ከአሁን ወዲያ ሀቁን ሸፋፍኖ ሊያልፍ አይችልም ። ነፍሰ ገዳዮች ናችሁ በእጃችሁ ደም አለ »
ዲሚትሪስ የቅዳሜ ጥቃት መልዕክት አንድ ነውም ብለዋል ።
«መልዕክቱ አንድ ነው ።ይኽውም« በመሃል አንካራ በጠራራ ፀሀይ ልንገድላችሁ ልንሰነጣጥቃችሁ እንችላለን » ነው። ይህ በኛ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ብቻ አይደለም ፤ ለሁሉም ማሳየት የፈለጉት መንገዳችንን የሚያደናቅፈውን መግደል እንችላለን እናም ምንም አደባባይ የሚወጣ ነገር አይኖርም የሚል ነው መልዕክቱ ።»
ተቃዋሚዎች ይህን ቢሉም መንግሥት ግን፣ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው በምሃፃሩ IS የሚባለውን ቡድን በጥቃቱ እንደሚጠረጥር አሳውቋል ። ከIS ሌላ በቱርክ የታገደው በአህፅሮቱ PKK የሚባለው የኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ እና ቱርክና የአውሮፓ ህብረት በአሸባሪነት የፈረጁት ግራው የአብዮታዊ ህዝቦች ፓርቲም እንዲሁ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች መሆናቸውን የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩቶግሉ ትናንት ተናግረዋል ። የቱርክ መንግሥት ለጥቃቱ አሸባሪዎችን ወይም አሸባሪ የሚላቸውን ተጠያቂ ቢያደርግም ሃላፊነቱን ወደ መንግሥት የገፋው ያመዝናል ። ባለፈው እሁድ ጥቃቱን በመቃወም አደባባይ የወጡት በሺህዎች የሚቆጠሩ ቱርኮች «ወንጀለኛው መንግሥት የእጁን ያገኛል »ሲሉ ዝተዋል ።
ጥቃቱ ያሳደረባቸውን ስሜት ለመግለፅ አደባባይ ከወጡት ሰልፈኞች አንዱ ኦንደር ኢስለር ነው ። ኦንደር ይህን ሁሉ ችግር

ያስከተለው የራስን ጥቅምን ማሳደደድ ነው ይላል ።
«የጥቃቱን ፈፃሚዎች ሁሉም ያውቃቸዋል ።ገዥው ፓርቲ ለራሱ ጥቅም ብሎ በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ቱርክን ወደ ርስ በርስ ጦርነት ጎትቶ አስገብቷታል ።»
የዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ ለቅዳሜው ጥቃት ተጠያቂነቱ ወደ መንግሥት ያመዘነበት ምክንያት አለ ይላል ።በቱርክ ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የተባለው የቅዳሜው የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት በሃገሪቱ የሰላም ተስፋን አደብዝዟል ። ከ18 ቀናት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ምክር ቤታዊ ምርጫ በፊት የደረሰው ይህ አደጋ ሃገሪቱን ወደ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳያመራትም አስግቷል ።እንደገና ገበያው ።
በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ አውሮፓን ከእስያና ከመካከለኛው ምሥራቅ የምታገኛኘው ቱርክ ልዩ ቦታ የሚሰጣት ሃገር ናት ።ቱርክ ከስምንት ሃገራት ጋር ትጎራበታለች ።በስተደቡብ ሶሪያ ና ኢራቅ በስተምሥራቅ ኢራን ና አዘርባጃን በሰተሰሜን ምሥራቅ ጆርጅያ በሰተሰሜን ምዕራብ ቡልጋርያ በስተምዕራብ ግሪክ በስተሰሜን ጥቁር ባህር ያዋስኗታል። ከአውሮፓ ጋር ባላት

ትስስር ፣የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል በመሆንዋ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ የምዕራባውያንን ጉዳይ ለመፈጸም በቀጥታም ይሁን በአጋርነት ብዙ አስተዋፅኦ የምታደርግና ልታደርግም የምትችል ሃገር ናት ።ቱርክ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን ብትመኝም እስካሁን አልተሳካላትም ።ሆኖም ከህብረቱ ጋር የተለየ ግንኙነት ያላት ሃገር ናት ። ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውንና ሌሎችንም አሸባሪ ቡድኖች ለመከላከል እንዲሁም ወደ አውሮጳ የሚጎርፈውን ስደተኛ ለመግታት ቱርክ አሁን የአውሮፓ ህብረት ከመቼውም በበለጠ ትብሯሯን የሚሻ ሃገር ሆናለች ።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ባለፈው ሳምንት ብራሰልስ ብቅ ባሉበት ወቅት በነዚሁ ጉዳዮች ላይ ተመክሯል ።ህብረቱ በተለይ ከቱርክ ጋር ሊተገበር ይገባል ያለውን የድርጊት መርሃ ግብር አቅርቦላቸው ነበር ። ገበያው እንደሚለው መርሃ ግብሩ በ3 ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ።ኤርዶሃንም በበኩላቸው ለነዚህ ጉዳዮች ማስፈፀሚያ የሚውል ከፍተኛ ገንዘብ ፣በሶሪያ ስደተኞች ሊሰፍሩ የሚችሉበት ነፃ ቀጣና እንዲፈጠር ፣ ሶሪያ ላይ የበረራ ማዕቀብ እንዲጣል ፣ ለዜጎቿ የአውሮፓ ህብረት የቪዛ ህግ እንዲላላ ጠይቀዋል ።ኤርዶጋንንና የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በነዚህ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተስማምተው ተለያይተዋል ።
77,695,904 ህዝብ ያላት ቱርክ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጧ የቸራት ስልታዊ ጠቀሜታ ተፈላጊ አድርጓታል ።በዚህ ሰበብ ቱርክን በእጅጉ የሚፈልጉት ምዕራባውያን ፖለቲካዋ አስተማማኝ ካልሆነው ከዚህችው ሃገር መንግሥት ጋር አብሮ የመሥራት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል ።

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic