ቱርክ የሩስያን የጦር ጄት መታ ጣለች | ዓለም | DW | 24.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ቱርክ የሩስያን የጦር ጄት መታ ጣለች

የሩስያ የጦር ጄት በቱርክ ተመቶ ከወደቀ በኋላ በቱርክ መንግሥት ጥያቄ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት «ኔቶ» ልዩ ስብሰባ መጥራቱ ተመለከተ። የኔቶ ቃል አቀባይ እንደገለፁት፤ አንካራ የሚገኘዉ የቱርክ መንግሥት ስለተፈጠረዉ አደጋ መረጃ መስጠት ይሻል ።

የቱርክ ጦር ሠራዊት ዛሬ ከቀትር በፊት ሶርያ ድንበር አቅራብያ ሱ 24 ተብሎ የሚታወቅ አንድ የሩስያ የጦር ጀት መቶ መጣሉን ቱርክ አስታውቃለች። ክልሌ ተጥሷል ስትል የገለፀችዉ ቱርክ ከተደጋጋሚ ማስጠንቀቅያ በኋላ አውሮፕላኑን መተው የጣሉት ሁለት F16 የቱርክ ተዋጊ ጀቶችዋ መሆናቸውን ማመልከትዋ ተዘግቧል።

ሩስያ በበኩልዋ አዉሮፕላኑ በሶርያ የአየር ክልል ዉስጥ፣ ከቱርክ ድንበር አንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የነበረና ሶርያ አየር ክልል ዉስጥ ከድንበሩ አራት ኪሎሜትር ርቀት ላይ መዉደቁን በመግለጽ የቱርክን ዘገባ አስተባብላለች። የሩስያ መንግሥት አዉሮፕላኑ ተመቶ መዉደቁ ከፍተኛ መዘዝ እንደሚያስከትከትል አስታዉቋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን ሁኔታዉ ከጀርባ በኩል የተሰነዘረ ዱላ ነዉ ሲሉ መናገራቸዉን ዜና ምንጭ «ሮይተርስ» ዘግቦአል።

Russland Kampfjet Suchoi Su-24

ሱ 24 ተብሎ የሚታወቀዉ የሩስያ የጦር ጀት

የሩስያዉን አዉሮፕላን ያበሩ የነበሩት ሁለት ፓይለቶች እስካሁን የደረሱበት ቦታ በዉል ባይታወቅም፤ የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር አዉሮፕላኑ ተመቶ እንደወደቀ በሰጠዉ መግለጫ ሁለቱም የአዉሮፕላኑ አብራሪዎች በጃንጥላ ለመዉረድ እንደቻሉ አስታውቆ ነበር። በሶርያ የአማጽያን ተወካዮችና የሶርያ መንግሥት ተቃዋሚዎች ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት አንዱ ፓይለት ሞትዋል አንዱ ደግሞ የደረሰበት አይታወቅም። ይህ በእንዲህ እንዳለ «ናታሊ» የተሰኘ አንድ የሩስያ የንግድና የጉዞ ወኪል ወደ ቱርክ የሚደረግ ማንኛዉንም ጉዞና ንግድ ማቋረጡን አስታዉቋል።

በሌላ በኩል የሩስያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ ቱርክ የነበራቸዉን ጉዞ መሰረዛቸዉን ቃላቀባያቸዉ አስታዉቀዋል።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ