ቱርክ፤ እስራኤልና ሩሲያ | ዓለም | DW | 04.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ቱርክ፤ እስራኤልና ሩሲያ

በሥምምነቱ መሠረት እስራኤል ጦሯ ለገደላቸዉ ቱርካዉያን እና አሜሪካዊ ቤተሰቦች 20 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ትከፍላለች።ቱርክ ለፍልስጤሞች በእስራኤል ወደብ በኩል የርዳታ ምግብ፤ መድሐኒትና ቁሳቁስ ትልካለች።ሌዲ ለይላ የተባለቸዉ የቱርክ መርከብ 10 ሺሕ ቶን የሚመዝን የመጀመሪያዉን የርዳታ ቁሳቁስ ጭና ባለፈዉ አርብ መሕለቋን አሽዶድ ወደብ ጥላለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:59

ቱርክ፤ እስራኤልና ሩሲያ

የእስራኤል ጦር የርዳታ ምግብ ናመድሐኒት የጫኑ ቱርካዉያንን እና አሜሪካዊን ሲግድል ቤንያሚን ኔታንያሁ መሐመድ ዓሊ ፓሻን፤ጠይብ ኤርዶሐን ሱልጣን መሐመድ ዳግማዊን መስለዉ ነበር።የዋሽግተን፤ለንደን፤ፓሪስ መሪዎች እንደየራሳቸዉም፤እንደየቀዳሚዎቻቸዉም ምንም አለማዳርጋቸዉ: ለምንአንዳሰኘ ለምዕራባዉያን ያደረዉ የቱርክ ጦር የሩሲያን የጦርጄት መትቶ ጣለ።አብራሪዉን ገደለም።ሕዳር።እርምጃዉ ኤርዶኸንን ሱልጣን አብዱልመጂድ ቀዳማዊን፤ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቱንን ባንፃሩ ንጉስ ኒኮላስ ቀዳማዊን አሰመስሏቸዉነበር።መዘዙ ግን ቱርክን በሩሲያ ማዕቀብ ይሸነቁጥ ያዘ።የዋሽግተን-ብራስልስ ፖለቲከኞች ምንም እንዳልሆነ ምንም አለማድረጋቸዉ አልበቃ ያለ ይመስል፤የመቶ ዓመት አወዛጋቢ ታሪክ እየመዘዙ ቱርክን ሲያወግዙ ኤርዶኸን፤ኔታንያሁ፤ፑቱንም ዘየዱ።እራሳቸዉን እንጂ ቀዳሚዎቻቸዉን አለመሆናቸዉንአስመሰከሩ።ባለፈዉ ሳምንት ታረቁ።

ገሚስ ዓለምን ከአምስት መቶ ዓመታት በላይ ያስገበረዉ የኦስማን ቱርክ ሥርወ-መንግሥት በ1820ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጉልበቱ መብረክረክ፤ ክንዱ መዛል፤ግዛቱ መራድ ጀምሮ ነበር።

ይሁንና የዓለም አዲስ ልዕለ-ሐያል ገዢ ለመሆን አስፍስፈዉ ይጠባበቁ የነበሩት የለንደን፤የፓሪስና የሞስኮ ገዢዎች እርስበርሳቸዉ ሥለተፈራሩ፤ የሚሆነዉን ከመጠበቅ ሌላ በደካማዉ የዓለም ገዢ ላይ እጃቸዉን ማንሳት አልፈለጉም ወይም አልቻሉም።

በ1830ዎቹ አጋማሽ ሩሲያ ከቱርክ ጋር የነበራትን ጠብ ለማርገብ ስትስማማ፤ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ የካይሮዉ ገዢ የመሐመድ ዓሊ ፓሻ አል መስዑድ ኢብን አጋሕ አመፅ እና እርምጃ በሚከፍተዉ ቀዳዳ ለመግባት ያደቡ ገቡ።መሐመድ ዓሊ ፓሻ ከቱርክ አገረ-ገዢዎች ሁሉ ጠንካራ እና ዘመናይ ጦር የነበራቸዉ፤ ከፍልስጤም እስከ ባብኤል መንደብ፤ ከአሌክሳንደሪያ እስከ ጋምቤላ ጥግ የተዘረጋዉን ሰፊ ግዛት ይገዙ ነበር።በጦራቸዉ ብዛትና ዘመናዊነት፤ በግዛት-ሐብታቸዉ ስፋት የተማመኑት መሐመድ ዓሊ ፓሻ፤ ሱልጣን መሐመድ ዳግማዊ ተጨማሪ ግዛት እንዲሰጧቸዉ አለያ ሱልጣኑ በልጃቸዉ እንዲተኩ በመጠየቅ አመፀዉ፤የዛሬዎቹን ሶሪያና ሊባኖስን ወረሩ።1838።

የአንድ ሥርወ-መንግሥት ገዢዎችን በመሸምገል ሰበብ ቀደም ከተል ብለዉ ጣልቃ የገቡት ብሪታንያ እና ፈረንሳይ መጀመሪያ የመሐመድ ዓሊን ነባር ግዛቶች ግብፅ፤ ሱዳንና ፍልስጤምን፤የኋላ ኋላ መሐመድ አሊ የተመኟቸዉን ሶሪያ፤ሊባኖስ እና ሂጃዝን በቀላሉ ከጃቸዉ አስገቡ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዘር፤ በሐይማኖት፤ በፖለቲካ መርሕ፤ በሥልጣን ዘመንም ከመሐመድ ዓሊ ፓሻ ጋር ጨርሶ አይገናኙም።የሚመሯት ሐገር ግን የቱርኩ ሰፊ ግዛት አካል እንደነበረች እዉነት ነዉ።የጦር ሐይሏ ጥንካሬ፤ የሐብቷ ብዛትም ከመሐመድ ዓሊ ግዛቶች ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም።የእስራኤል ጦር ግንቦት 2010 የእርዳታ እሕል ጭና ዓለም አቀፍ ዉኃ ላይ ትቀዝፍ የነበረችዉን መርከብ ወርሮ ስምንት ቱርካዉያንን እና አንድ አሜሪካዊን በመግደሉ ሰበብ ቱርክ እና እስራኤል የገጠሙት ፉከራ-እና አፃፋ ፉከራ የነመሐመድ ዓሊን ዘመን አስታዋሽ ነበር።

እርምጃ ዉዝግቡ፤ ገላጋይ መጥፋቱ ያ ምድር ከመቶ-ዘጠና ዓመት በኋላም ለሐይል እንጂ ለሕግ፤ የማይገዛ መሆንኑ መስካሪ፤ ዓለምም የሐይለኞች እንጂ የሕግ አክባሪ-አስባሪዎች እንዳልሆነች አመልካች ነዉ።

ከስድስት ዓመት በኋላ ግን የአንካራ-ቴልአቪቭ መሪዎች ዘየዱ።ጠብ ዉዝግብ ፉከራቸዉ እንዳልጠቀመና እንደማይጠቅማቸዉ ተረድተዉ የሚጠቅማቸዉን ለማድረግ ተስማሙ።«ከቱርክ ጋር ሥላደረግነዉ ሥምምነት ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኬሪ አስረድቻቸዋለሁ።ዛሬ ቀትር ላይ በይፋ ይታወጃል።ይሕ ጠቃሚ እርምጃ ነዉ።ባንድ በኩል ግንኙነቱን ወደነበረበት የሚመልስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለእስራኤል ምጣኔ ሐብት ከፍተኛ ጥቅም አለዉ።ይሕን ቃል በአፅንኦት እገልፀዋለሁ ከፍተኛ አወንታዊ ጠቅም አለዉ።»

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።ባለፈዉ ማክሰኞ።በሥምምነቱ መሠረት እስራኤል ጦሯ ለገደላቸዉ ቱርካዉያን እና አሜሪካዊ ቤተሰቦች 20 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ትከፍላለች።ቱርክ ለፍልስጤሞች በእስራኤል ወደብ በኩል የርዳታ ምግብ፤ መድሐኒትና ቁሳቁስ ትልካለች።ሌዲ ለይላ የተባለቸዉ የቱርክ መርከብ 10 ሺሕ ቶን የሚመዝን የመጀመሪያዉን የርዳታ ቁሳቁስ ጭና ባለፈዉ አርብ መሕለቋን አሽዶድ ወደብ ጥላለች።

የቱርኩ ጠቅላይ ሚንስትር ቢናሊ ዪልዲሪም እንዳሉት ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያደረገችዉ ሥምምነት ለፍልስጤሞች ምግብና ቁሳቁስ በማቀበል ብቻ አይቆምም።በእስራኤል ከበባና ማዕቀብ ለሚማቅቀዉ የጋዛ ሕዝብ ዘመናይ ሆስፒታል እና መኖሪያ ቤት ለመገንባትም አቅዳለች።«በሥምምነቱ መሠረት ጋዛ ዉስጥ ሁለት መቶ አልጋ ያለዉ ዘመናይ ሆስፒታል እናስገነባልን።ሆስፒታሉ የፍልስጤምና የቱርክ ወዳጅነት ሆስፒታል ይባላል።ከዚሕም በተጨማሪ የቱርክ የቤቶችና የግንባታ መስሪያ ቤት ጋዛ ዉስጥ አዳዲስ መኖሪያ ሕንፃዎችን ይገነባል።»

እስራኤል ሙስሊሞች ከሚበዙበት ሐገራት ሁሉ ጠንካራ ግንኙነት የነበራት ከቱርክ ጋር ነበር።ባለፉት ስድት ዓመታት ግን የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት በጠብ፤ ዉግዘት፤እሰጥ አገባ ተቀይሮ ነበር።በአዲሱ ስምምነት መሠረት እስራኤል ለቱርክ ጋስ ትሸጣለች።በእስራኤል የቀድሞዉ የቱርክ አምባሳደር ኦጉዝ ሴሊኮል እንደሚሉት ወደ ቱርክ የሚጓዘዉ እስራኤላዊ ሐገር ጎብኚ ቁጥርም ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

«በ2008 ቱርክን የጎበኙት እስራኤላዉን 500, 000 ነበሩ።ባለፈዉ ዓመት ግን 200,000 ብቻ ናቸዉ።ሥምምነቱ የእስራኤል ሐገር ጎብኚዎችን ቁጥር በ2008 ወደነበረዉ ያደርሰዋል ተብሎ ይታሰባል።»ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከምጣኔ ሐብቱ ይልቅ ድርድር፤ ዉይይት፤ ሰላም በማያዉቀዉ ምድር በድርድር ዉይይት ጠብን የማርገቡ አስትምሕሮ ነዉ የሚጎላዉ።ቱርክ በጥቁር ባሕር ከምትዋሰናት ሐይል ጎረቤትዋ ሩሲያ ጋር ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ የገጠመችዉን ጠብ ለማርገብም ተስማምታለች።

የቱርክ ጦር ከሶሪያን ጋር የሚያዋስነዉን የሐገሩን ድንበር አልፎ የቱርክን የአየር ክልል ጥሷል ያለዉን አንድ የሩሲያ ተዋጊ ጄትን መትቶ የመጣሉ መዘዝ የምዕራባዉያንን ጥቅም ለማስከበር ሌት ከቀን እየባተለች በምዕራባዉያን የምትገፋዉ ቱርክን፤ከምዕራባዉያን እየተወዳጀች በሰበብ አስባቡ የምትጣላዉ ሩሲያንም ክፉኛ ጎድቶ ነበር።

ባለፈዉ ዓመት ይሕን ጊዜ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሩሲያዊ ሐገር ጎብኚ ቱርክ መዝናኛ ሥፍራዎች ይርመሰመስ ነበር።ዘንድሮ ግን ሩሲያ ቱርክን ለመበቀል በጣለችዉ ማዕቀብ ምክንያት አንድም ሩሲያዊ ሐገር ጎብኚ ወደ ቱርክ ዝር አላለም።

የቱርክና የሩሲያ

የንግድ ልዉዉጥ በወር በአማካይ ከ350 ሚሊዮን በላይ ነበር።የአዉሮጳ ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ከጣሉ ወዲሕ ደግሞ የሁለቱ ሐገራት የንግድ ልዉዉጥ አሻቅቦ ነበር።ካለፈዉ ሕዳር ወዲሕ ግን የንግድ ልዉዉጡ በእጅጉ አሽቆልቋል።ሁለቱ ሐገራት ግንኙነታቸዉን ወደነበረበት ለመመለስ ባለፈዉ ሳምንት ከተስማሙ በኋላ የቱርኩ ጠቅላይ ሚንስትር ቢናይሊ ዪልዲሪም ከእንግዲሕ ይለወጣል ብለዋል።

«ግንኙነቱን ወደነበረበት የመመለሱ ሒደት በተጨባጭ ተጀምሯል።የንግድ ግንኙነቱ ይቀጥላል።ይሕ ማለት ቱሪዝሙም በፍጥነት ይመለሳል ማለት ነዉ።»ሕዳር ላይ ይሕን ማሰብ ሲበዛ ከባድ ነበር።ፕሬዝደንት ጠይብ ኤርዶኻን ከአንካራ፤ ቭላድሚር ፑቲን ከሞስኮ ይወራወሩ የነበሯቸዉ ቃላት በ1853 ክሪሚያን ያነደደዉ ጦርነት ከመለኮሱ በፊት የነበረዉን ድባብ አስታዋሽ ነበር።

ያኔ አዉሮጳ ላይ ብቅብቅ ማለት የጀመሩት ፈረንሳይና ብሪታንያ እየሩሳሌም የሚገኙ የክርስትና ቅዱስ ሥፍራዎችን ለመጠበቅ በሚል ስም የኦስማን ቱርክ ሱልጣኖችን አስፈቅደዉ ከቅድስቲቱ ከተማ እግራቸዉን ተከሉ።እንደ ሁለቱ ሐገራት ሁሉ ጉልበታቸዉ እየፈረጠመ የነበረዉ የሩሲያ ዛሮች የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ቅዱስ መካናትን መጠበቅ እንዲችሉ ሲጠይቁ ግን ለንደን-ፓሪሶች እኛ በቂነን በሚል ሰበብ ቱርኮች እንዳይፈቅዱ አከላከሉ።

ቀዳማዊ ኒካላስ ቱርክንም ለመበቀል፤ ምሥራቅና ደቡባዊ አዉሮጳንም ከአዉሮጳ ተፎካካሪዎቻቸዉ ቀድሞዉ ከቱርክ እጅ ለመማረክ ወደ ደቡብ አዉሮጳ ያዘመቱት ጦር የዳንዩፕን ወንዝ ሲሻገር ከቱርኮች የገጠመዉን አፀፋ መቋቋም አልቻለም።ለሞቱ የሚያጣጥረዉን የኦስማን አገዛዝና ሞስኮ ላይ አዲስ የጎለበተዉ ሐይል የገጠሙትን ዉጊያ ሁለቱንም የሚያዳክም በመሆኑ ለለንደንና ለፓሪስ ሰርግና ምላሽ አይነት ነበር።

ጦርነቱ እየተራዘመ፤ እየሰፋ በተለይ ክሪሚያ ላይ እየጋመ፤ የሩሲያ ጦር እያየለ ሲመጣ ግን ፈረንሳይ እና ብሪታንያ ሌሎች ታማኞቻቸዉን አስከትለዉ፤ ለቱርክ ወግነዉ ሩሲያን ይወጉ ጀመር።ከ1853 እስከ 1856 በዘለቀዉ ጦርነት ከ600,000 በላይ ሰዉ አልቋል።

የታሪክ ተመራማሪዎች እንደመሰከሩት ሱልጣን አብዱልመጂድና ንጉስ ኒኮላስ ብዙ የፎከሩ-የዛቱበት፤ብዙ ጦር ያስፈጁበት ጦርነት የሩሲያን የመስፋፋት ምኞች፤ የቱርክን ያረጀ ጉልበት

ከማላሸቅ ባለፍ ለሁለቱም የተከረዉ የለም።አትራፊዎቹ እንደገና ኋላ የዓለም ልዕለ ሐያልነቱን የተቆጣጠሩት የለንደን-ፓሪስ ገዢዎችና ተከታዮቻቸዉ ናቸዉ።

አሜሪካ የምትመራዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል የሆነችዉ የቱርክ ጦር ባለፈዉ ሕዳር የሩሲያን የጦር ጄት መትቶ የጣለዉ፤ ከቱርክ ይልቅ ለምዕራባዉን ሲል፤ በምዕራባዉን ሙሉ ድጋፍ መሆኑ ለብዙዎች ሚስጥር አልሆነም።

ፕሬዝደንት ኤርዶኻን «ግዳይ» በጣሉ ማግስት የሩሲያን አፀፋ ለመቋቋም እንደ ሱልጣን አብዱልመጂድ ቀዳማዊ ሲዝቱ፤ሲፎክሩ የዋሽግተን ብራስልስ መሪዎች «አይዞሕ፤ አይዞን» ዓይነት፤ የኔቶ ድጋፍ እንደማይለያቸዉ አረጋግጠዉላቸዉ ነበር።የሩሲያ ማዕቀብ ቱርክን ሲሸንቁጣት ግን ዞር ብሎ ያያት የለም።

«ዘንድሮ ከ20 ዓመት ወዲሕ በጣም መጥፎዉ ጊዜ ነዉ።ምንም ገቢ የለንም።ዕዳችንን መክፈል እንኳን አልቻልም።ባለሥልጣናቱን እኛን እይረዱንም።»

ይላሉ ሩያዉያን ከሚዘወትሩት መዝኛ ስፍራ ያንዱ አካባቢ ታክሲ ነጂ።የቱርክ ገበያ ማጣት ለምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎች ከጥሩ የዜና ርዕሶች አንዱ ነዉ የሆነዉ።ሌላዉ ቱርክ መሸበሯ፣ ወይም ከመቶ ዓመት በፊት አርመኖችን መግደሏ ከዚሕ ካለፈ የቱርክ መንግሥት ሰብአዊ መብት መርገጡ ነበር የምዕራባዉያን ትኩረት።እንጂ የቱርኮች ችግር አልነበረም።

ግን ኤርዶኻን ሕዳር ላይ እንደተጃጀሉ አለመቅረታቸዉ በጀ።ቢዘገዩም በስምንተኛ ወራቸዉ ነቁ።ከእስራኤል ጋር እንዳደረጉት ሁሉ እርቅ አሉ።«ለፕሬዝደንት ፑቲን በላኩት ደብዳቤ፤ በተፈጠረዉ ነገር ጥልቅ ሐዘን የተሰማን መሆኑን ገልጫለሁ።»ኤርዶኸን ጦራቸዉ ጥፋተኛ ነዉ ብለዉ ይቅርታ አልጠየቁም።ለሟቹ ፓይለትም ቱርክ ካሳ አትከፍልም።ኤርዶኻን እንደመሪ፤ ያሉትን ማለታቸዉ፤ ቱርክ እንደሐገር ያደረገችዉን ማድረጓ ሕዳር ላይ እንደ ንጉስ ኒኮላስ የተገሰሉትን የፕሬዝደንት ፑቲንን ቁጣ ለማርገብ-በቂ፤ የሩሲያን ጥቅምም ለማስከበር፤ ለሠላምም ጠቃሚ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic