ቱርክን የከፋፈላት ሕዝበ-ውሳኔ | ዓለም | DW | 17.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ቱርክን የከፋፈላት ሕዝበ-ውሳኔ

በሽብር ጥቃቶች እና የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ የታመሰችው ቱርክ ትናንት በሕዝበ-ውሳኔ ፓርላሜንታዊውን ሥርዓተ-መንግሥት በጠንካራ ፕሬዝዳናታዊ አሰራር ለመቀየር ወስናለች። ተቃዋሚዎች ግን በጠባብ ልዩነት እና አወዛጋቢ ሒደት ሕገ-መንግሥቱ እንዲቀየር የተላለፈው ውሳኔ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:07

የቱርክ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት

ትናንት በቱርክ የፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ደጋፊዎች የአገራቸውን ሰንደቅ አላማዎች በአደባባይ ሲያውለበልቡ ተቃዋሚዎቻቸው ቁጭት ላይ ነበሩ። ኤርዶኻን አብዝተው ያቀነቀኑት ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ የጠቅላይ ሚኒሥትርን ሥልጣን ሽሮ ስልጣንን ሁሉ በፕሬዝዳንቱ እጅ ጠቅልሎ ያስገባል። ተቃዋሚዎች እንገዳደረዋሉን ባሉት ሕዝበ-ውሳኔ ሕገ-መንግሥቱ ይሻሻል ይሚለው ኃሳብ 51.4 በመቶ ድምፅ አግኝቶ በጠባብ ውጤት አሸናፊ መሆኑን ያስታወቁት የቱርክ ከፍተኛ ምርጫ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሳዲ ጉቬን ናቸው።

«በተቆጠሩት ድምፆች 56,147,506 ድምፅ ሰጪዎች አሉ። 594,076 ድምፅ ጪዎች ደግሞ አልተካተቱም። ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል የሚለው 24,763,516 ድምፆች አግኝቷል። አይሻሻልም የሚለው ደግሞ 23,511,155 ድምጾች ማግኘቱን ለመረዳት ችለናል። በዚህም መሰረት ይሻሻል የሚለው አሸናፊ ሆኗል።»

ውጤቱ ባለፈው አመት በመንግሥታቸው ላይ ከተሞከረ መፈንቅለ-መንግስት የተረፉት ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን እስከ ጎርጎሮሳዊው 2029 ድረስ እና ከዚያም በኋላ በሥልጣን እንዲቆዩ ይፈቅድላቸዋል። በመፈንቅለ-መንግስት ሙከራው ማግሥት 47,000 ሰዎች አስረው 120,000 ከሥራ ያባረሩት ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን የሕዝበ-ውሳኔው ውጤት «ታላቅ ትርጉም አለው» ብለዋል።

«እነዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች ተራ ለውጦች አይደሉም። ይሐ ልዩ እና ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ፓርላማው እና ህዝቡ በእንዲህ አይነት ጠቃሚ ለውጥ ላይ ሲወስኑ በቱርክ ታሪክ የመጀመሪያው ነው።»
ኤርዶኻን እንዳሉት በቱርክ ታሪክ እና የመንግሥት አወቃቀር ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያስከትለው ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት አከራካሪ ሆኗል። ተንታኞች ጠባቡ ውጤት በኤርዶኻን አመራር ሥር ቱርክ ለመከፋፈሏ ምልክት ነው ሲሉ ይደመጣል። የዋናው ተቃዋሚ የሪፐብሊካን ሕዝቦች የፖለቲካ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር ቡሌንት ቴዝካን የሕዝበ-ውሳኔው የድምፅ አቆጣጠር አከራካሪ ነው ብለዋል።

«ምን ያክል ማኅተም ያላረፈባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዳሉ አሊያም ምን ያክሉ የተሳሳቱ መሆናቸውን መናገር አይቻልም። በከፍተኛ ምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ እነዚህ ማኅተም ያላረፈባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ትክክል ተብለው ሳይመዘገቡ ወደ ድምፅ ኮሮጆው እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም ምክንያት ውዝግብ ያስነሳውን የሕዝበ-ውሳኔ ሕጋዊነት መፍትሔ መፍጠር የሚቻለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው። ይኸም ከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽኑ የሕዝበ-ውሳኔውን ውጤት ውድቅ ማድረግ አለበት።» ታዛቢዎችም የሕዝበ-ውሳኔው ከቅስቀሳው ጀምሮ ፍትኃዊ እንዳልነበር በመናገር ላይ ናቸው። የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት እና የዴሞክራሲያዊ ተቋማት እና ሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ቢሮ በጥምረት ካካሔዱት በኋላ የቅስቀሳ ዘመቻው ለሁለቱም ወገኖች እኩል አልነበረም ብለዋል። የታዛቢ ቡድኑ ኃላፊ ሴዛር ፍሎሪን ፕሬዳ የኋላ ኋላ የተደረጉ ለውጦች አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን አስወግዷል ሲሉ ተችተዋል። ታዛቢዎቹ ተገቢው ማኅተም ያላረፈባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲቆጠሩ በከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽኑ መወሰኑ ተገቢ አልነበረም ባይ ናቸው። 

ከውጤቱ በኋላ ገዢው የፍትኅ እና ልማት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በአባልነት እንዲቀላቀሉት ግብዣ አቅርቧል። የፓርቲው ምክትል ሊቀ-መንበር ሙስጠፋ ኤሊታስ ፕሬዝዳንቱ የመሰረቱትን ፓርቲ መልሰው ቢቀላቀሉ «ደስተኛ እንሆናለን» ብለዋል። በሕዝበ-ውሳኔው ከሚሻሩ የሕገ-መንግስቱ አንቀፆች አንዱ ፕሬዝዳንቱ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ስለማይፈቅድ ነበር ኤርዶኻን ከሶስት አመታት በፊት ከፍትኅ እና ልማት ፓርቲ ለቀው የወጡት። የሑርየት ጋዜጣ የአንካራ ቢሮ ኃላፊ ሴርካን ዴሚርታስ አሁን በቱርካውያን ዘንድ የፈጠረው መከፋፈል ለመጪዎቹም ጊዜያት አስጊ ነው የሚል ፍርሃት አላቸው።«አሁን በቱርክ ማኅበረሰብ ዘንድ የተፈጠረ ትልቅ ግራ መጋባት እየተመለከትን ነው። በፖለቲካውም ይሁን በማኅበራዊ ጉዳዮች ይሐ ይኸ ፅንፈኝነት ዘላቂ የሚሆን ይመስላል።መጪዎቹ ቀናት ፈታኝ ይሆናሉ። ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻንም ሆኑ ገዢው ፓርቲ አገሪቱን ለማስተዳደር አመቺ ሁኔታ አያገኙም። ስለዚህ በመጪዎቹ ቀናት እና ሳምንታት የቱርክ ማኅበረሰብን መከፋፈል እና ፖለቲካዊ ነፀብራቁን እንመለከታለን።»በሕዝበ-ውሳኔው መሰረት የቱርክ ህገ-መንግሥት ሲሻሻል ፕሬዝዳንቱ እያንዳንዳቸው አምስት አመታት ለሚረዝሙ ሁለት የሥልጣን ዘመናት አገሪቱን እንዲመራ ይፈቀዳል። የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን፤አንድ አሊያም በርካታ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ይሾማል።በፍትኅ ሥርዓቱ ውስጥ ጣልቃ መግባት ይችላል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ውሳኔውም ከፕሬዝዳንቱ እጅ ይገባል። በአንፃሩ የጠቅላይ ሚኒሥትሩ ሥልጣን ይሻራል።

 
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic