ቱሪዝም በኦሮሚያ ክልል እና ተግዳሮቱ
የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ከሰሞኑ «የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት» በሚል ባለድርሻ አካላትን ያገናኘውን አውደ ርዕይ ከፍቶ ትናንት ከአመሻሽ እስከ እኩለ ለሊት የመዝጊያ ስርዓቱን አከናውኗል፡፡ በዚህ የቱሪዝም ኮሚሽኑ አውደ ርዕይ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈው ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን ከማስተዋወቅም ባለፈ በዘርፉ ተግዳሮቶችም ላይ ተመካክረዋል፡፡
እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ1994 “ትራቨል ኢትዮጵያ” የተሰኘውን የአስጎብኚ ድርጅት ከፍተው የቱሪዝም ኢንደስትሪውን የተቀላቀሉ ወ/ሮ ሳምራዊት ሞገስ ስለ ዝግጅቱ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ ነው አስተያየታቸውን የጀመሩት፡፡ “የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ዘርፉን ለማነቃቃት ከማስተዋወቅ ጀምሮ እየሰራ ላለው ስራ አድናቆት አለኝ፡፡ ለአመራሮቹም እውቅና መስጠት ይገባል፡፡ ዋናው የአገሪቱ ቱሪዝም ዘርፍ የሆነው የኢትዮጵያ ቱሪዝምም ከዚህ ብዙ መማር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡”
አንጋፋ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤቷ ወ/ሮ ሳምራዊት ሞገስ ከዚሁ ጋር አያይዘው በሰጡት አስተያየታቸው ግን አሁን ላይ ኢንደስትሪውን ማነቆ ሆኖ የያዘው የሰላም እጦት ችግር እሳቸውን ጨምሮ በርካቶችን መፈተኑ አልቀረም፡፡ ዘርፉ ኮሽታን አይወድም የሚሉት የአስጎብኚ ባለሙያዋ በሰላም ችግሩ የገጠማቸውን ሂደቶችም ዘርዝረው አስረድተዋል፡፡ “የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት የደመደመው የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በርካታ የቱሪስት ፍላጎቶች ወደ እኛ ይመጡ ነበር፡፡ እኛ ግን አትምጡ ነበር የምንላቸው፡፡ ምክኒቱም ኃላፊነት አለብን እነሱን በሰላም እንደ ተቀበልን በሰላም የመሸኘት፡፡ ሰላም በእጅጉ አስፈላጊያችን ነው፡፡”
የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤትና የቱሪዝም ባለሙያዋ ትልቁ ምኞቴም ይህ ነው ይላሉ፡፡ “በሚቀጥለው ዓመት መስቀል ስናከብር አገሪቷ ሰላምን ተላብሳ ብርከት ያሉ ቱሪስቶችን ተቀብለን እንድናስጎበኝ አልማለሁ እመኛለሁ፡፡” የጸጥታ ዞታው የፈተነው ዘርፉ አሁን ላይ ሰራተኛን እስከ መቀነስ እንዳደረሳቸውም አስረድተውናል፡፡
በሮባ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅት የሃላል ቱሪዝም ኮንሰልታቱ አቶ ታሪኩ ኃይሉም ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን የዘርፉ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉንም በተለይም በኦሮሚያ ክልል ላይ አተኩሮ ጎብኚዎችን የሚያስጎበኘው ድርጅቱ ምንም እንኳ የጸጥታ ችግሩ አልፎ አልፎ ብስተዋልም ቱሪዝም የተቋረጠበት የክልሉ አከባቢ የለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ “እዚህም እዛም የሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ደግሞ ያንን በሰፊው በክልሉ ስዕል ገር ማመሳሰል ተገቢ አይደለም፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ባሁን ወቅት በስፋት ጎብኚዎች የሚጎበኙአቸው አከባቢዎች አሉ፡፡ ከባሌ እስከ ጂማ እና ምእራብ ወለጋ እያስጎበኘን ነው፡፡ ነግር ግን ደግሞ ኮሽታዎች ዘርፉን አልረበሹትም ማለት አይቻልም”ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ቱሪዝምኮሚሽን ባለስልጣናትም በክልሉ ያለውን የፀጥታ ችግር ስጋት የሚያጠላውን ጥላ ሳይሸሽጉ፤ ነገር ግን በክልሉ ሰዎች የፀጥታውን መረጃ እየተቀበሉ የሚጎበኙት የክልሉ አከባቢዎች በዛሉሲሉ ይሞግታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሲለሺ ግርማም ከሳምንታት በፊት በዶቼ ቬለ ተጠይቀው በአገሪቱ ግጭት ያለባቸው አከባቢዎች በቱሪዝም ላይ ብቻ ኑሮአቸውን የመሰረቱትን ጨምሮ በርካቶችን ብጎዳም አመቺ በሆኑ የአገሪቱ አከባቢዎች ጎብኚዎችን የመቀበሉ ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በሰሞነኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት አውደ ርዕይ የቱሪዝም ባለድርሻ አካላት እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ቻይና ካሉ አገራት ተሳትፈው እንደነበርም ተነግሯል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር