ቱሪዝምና የልማት ድርሻው | ኤኮኖሚ | DW | 28.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቱሪዝምና የልማት ድርሻው

ቱሪዝም በርከት ባሉ ታዳጊ ሃገራት በያመቱ በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስገኝ ጠቃሚ የኤኮኖሚ ዘርፍ ነው። በሌላ በኩል ይሄው ዘርፍ ሙስናና ቀውስ የተጣባው መሆኑም ይታወቃል። ተጠቃሚዎቹ እጅግ ጥቂት በእጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረው ታዲያ የቱሪዝሙ ዘርፍ በጥቅሉ ዘላቂ ለሆነ ልማት የግድ ዋስትና እንዳልሆነ ያመለክታሉ። የቱሪዝሙ ዘርፍ ደግሞ ደጋግሞ እንደሚታየው ለፖለቲካ ቀውስም በጣሙን የተጋለጠ ነው። የወቅቱ የግብጽ ሁኔታ ለዚሁ ወቅታዊ ጭብጥ መረጃ ሆኖ ይገኛል። የአገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ በመፍራት ብዙ ቱሪስቶች በመቅረታቸው በቀይ ባሕር የቱሪስት መዝናኛዎች የሚያገለግሉ በርካታ የሆቴል ሠራተኞች በሚቀጥሉት ሣምንታትና ወራት ምናልባትም ለመቦዘን እንዳይገደዱ እያሰጋ ነው።

ለነገሩ ቱሪዝም ግብጽ ውስጥ ከ 2011 ዓ-ም ዓብዮት በፊት እያገገመ ሲሄድ በተከታዩ 2012 ዓ-ም 11,5 ሚሊዮን ሰዎች አገሪቱን ጎብኝተው ነበር። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር ሃያ ከመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። ጽናት ያለው ይመስላል። የቱሪዝም ኤኮኖሚ የተፈጥሮ ቁጣና ውዝግቦች ቢጫኑትም በቀላሉ የማይበገር የኤኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ነው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት አፈ-ቀላጤ ሣንድራ ካርቫዎም የሚናገሩት።

«ቱሪዝም በዓለም ላይ በቀላሉ እንዲጠፋ ሊደረግ የማይችል ዘርፍ ነው። እርግጥ የተፈጥሮ ቁጣና ውዝግቦች በዘርፉ ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። ሆኖም ግን የቱሪዝም ዘርፍ ሁኔታው እንደተረጋጋ በፍጥነት መልሶ ሊያገግም የሚችል ነው። አብዛኛውን ጊዜ እንዲያውም ከቀውሱ በኋላ ቀድሞ ከነበረው የበለጠ ፈጥኖ ሊያድግ ይችላል»

ስለዚህም በዘርፉ ዓለምአቀፍ ድርጅት ዕምነት ቱሪዝም በተለይ በታዳጊ ሃገራት ዘንድ ትልቅ የዕድገት መንኮራኩር ነው። ቱሪዝም ዛሬ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከአጠቃላዩ የኤኮኖሚ ውጤት ዘጠኝ በመቶ የሚሆነው ድርሻ አለው። ከ 11 አንዱ የሥራ ቦታም በዚሁ ዘርፍ ላይ ጥገኛ ሆኖ ይገኛል። በግብጽም የቱሪዝሙ ዘርፍ ታላቁ አሠሪ ሲሆን በአገሪቱ 13 ከመቶ የሚሆነው የሥራ ቦታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዚሁ የጉዞ ዘርፍ ጋር የተሳሰረ ነው።

የሆቴሉ ንግድ ብቻ አይደለም፤ ታክሢ ነጂው፣ ቅርሣ ቅርስ ቸብቻቢው፣ የግንባታው ዘርፍ፣የምንጣፍ ኢንዱስትሪው፤ እንዲሁም የእርሻ ምርት አቅራቢውና የዕጅ ስራ ባለሙያው ወዘተ - ከዚሁ ይጠቃለላሉ። በሌላ በኩል የሥራው ጥራት ግን «ብሮት ፊር ዲ ዌልት» የተሰኘው የጀርመን የረድዔት ድርጅት ባልደረባ አንትዬ ሞንስሃውዘን እንደሚሉት ያን ያህል አይደለም።

«ምን ዓይነት የሥራ መስኮች እንደተፈጠሩ ጠለቅ ብለን በምንታዘብበት ጊዜ ሥራው በቱሪዝም ወራት ላይ የተመሠረተ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ተቀጣሪዎቹ በዝቅተኛ ደረጃ የሚያገለግሉ ናቸው። በሥልጠና የማደግ ብዙ ዕድል የላቸውም። ቱሪዝም በታዳጊ ሃገራት ጠቃሚ የልማት ዘርፍ ሲሆን እርግጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከረሃብ መስፈርት በታች በሚኖርበት ሁኔታ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሆኖ አይገኝም። ከዚህ አንጻር የግድ የልማት መንኮራኩር ሆኖ ሊታይ አይችልም»

ግብጽ ውስጥ ከአንድ-አምሥተኛ የሚበልጠው ሕዝብ ከብሄራዊው ዝቅተኛ የድህንነት መስፈርት በታች ነው የሚኖረው፤ በጀርመን ፌደራል የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስትር ተቋም የቀረበ መረጃ እንደሚያመለክተው። ቱሪዝም ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ በሆነባት በኬንያም ይሄው ዘርፍ የአገሪቱን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት 11 ከመቶ ድርሻ ይይዛል። ሆኖም ግማሹ የአገሪቱ ሕዝብ የሚኖረው በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰች ገቢ ነው።

እርግጥ ልማት የገንዘብ ጥያቄ ብቻ አይደለም። የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ፤ እንዲሁም የተፈጥሮ ጸጋና የባሕላዊ ቅርሶች እንክብካቤም የዚያኑ ያህል ጠቃሚ ነገር ነው። በጎ አስተዳደር ሳይኖርና በውሣኔ ሂደቶች ላይ የአገሬው ሕዝብ ተሳትፎ ሳይኖርበት ደግሞ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ለተሻለ ብልጽግና አስተዋጽኦ ሊኖረው አይችልም። የጀርመን ዓለምአቀፍ ድርጅት GIZ የጀርመንን ፌደራል የኤኮኖሚ ተራድኦ የሚኒስትር ተቋም በመወከል የጉዞ አካባቢዎችን መዋቅራዊ ይዞታ በማሳደግ በኩል በርካታ መንግሥታትንና ኩባንያዎችን ያማክራል። ሆኖም አንጋፋው የድርጅቱ አማካሪ ክላውስ ሌንገፌልድ እንደሚሉት ዘርፉ ገና ለልማት ዕርዳታ እንግዳ ነው።

Türkei Kaiser Wilhelm Brunnen im Hippodrom

የቱርክ የቱሪስት መስህብ

«ቱሪዝም የሚያሳዝን ሆኖ የልማት ዕርዳታ በሰፊው ያተኮረበት ዘርፍ አይደለም። እርግጥ ይህ እኛ ባለመፈለጋችን አይደለም። በውስጥ ባለመካተታችን እንጂ!ብዙ መንግሥታት የግልጽነትና የበጎ አስተዳደር ጥያቄዎች በዘርፉ ለሚደረግ የልማት ትብብር ከጀርመን አኳያ እንደ ቅድመ-ግዴታ ሆነው እንዲነሱባቸው አይፈልጉም»

በሌንገፌልድ አስተሳሰብ ከዚህ የዘለቀ ሌላም ችግርም አይታጣም።

«አንዱ አከራካሪ ጉዳይ አዘውትሮ የሚጠሰው የመሬት አጠቃቀምና ይዞታ ሕግ ነው። ኩባንያዎችና መንግሥታት ግልጽነት በጎደለው መንገድ በሚደረግ መዋዕለ-ነዋይ የተለየ ጥቅም ለማግኘት ይሞክራሉ። ይህ ደግሞ ለቱሪዝም የሚበጅ አይደለም»

ሁኔታው ለቱሪዝም ዕድገት ካለመበጀቱም በላይ ሕዝብን መጉዳቱም የሚጠበቅ ነው።

«የችግሩ ተሸካሚ አገሬው ሕዝብ ነው። በሆቴሎችና በወደቦች ግንቢያ የተነሣ አገሬው ለሕልውናው ወሣኝ ከሆነው የአሳ ማጥመድ ተግባር ይገለላል። ብሄራዊ መናፈሻዎችን ለማነጽ ሲባል ነዋሪውን የማስወጣት ድርጊትም አለ። ሆቴሎችና አየር ጣቢያዎችን ለማነጽም እንዲሁ መሬት መወረሱ የተለመደ ነገር ነው»

155 ዓባል ሃገራትን የጠቀለለው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ታዲያ ገና በጎርጎሮሳውያኑ 1999 ዓ-ም ይህንኑ ተጽዕኖ ለመከላከል አንድ የኤቲክ-ኮድ፤ የሞራል መርህ ማስፈኑ ይታወሳል። ደምቡ እርግጥ አሳሪነት የሌለው ለማሕበራዊና ተፈጥሮን ለተንከባከበ ዘላቂ የቱሪዝም ኤኮኖሚ ዕድገት የቀረበ የሃሣብ ካታሎግ ሊባልም የሚችል ነው። ሰነዱ በውስጡ የቱሪዝምና የጉዞ ነጻነት መብትን እንዲሁም የቱሪዝሙ ኢንዱስትሪና አንግዶች በአስተናጋጅ ሃገራት ፊት ያለባቸውን የተፈጥሮ ጥበቃ ሃላፊነትም ይጠቀልላል። የሠረተኞች መብት መጠበቅም የሰነዱ አካል ነው።

«የሰነዱ ወይም የኮዴክሱ ጠቀሜታ የተወሰኑ ደምቦቹ በብዙ ሃገራት ተወስደው በብሄራዊ ሕጎች ውስጥ መካተታቸው ነው። ይህ ለምሳሌ ሕንድን ይመለከታል»

ነገር ግን አሥር ነጥቦችን የጠቀለለው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሰነድ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አሳሪነት ስለሚጎድለው ፍቱንነቱ የተወሰነ ነው።

«ሰነዱ ጭብጥ እርምጃዎችን ባለመዘርዘሩ ተግባራዊነቱ ዝቅተኛ ነው። ደምቡ 13 ዓመት ሲሆነው በተግባራዊነት ረገድም ትልቅ ክፍተት ነው ያለበት»

በመሠረቱ በአንድ አካባቢ የሚደረግ የቱሪዝም የመስፋፋት ሂደት የሕዝቡን መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎትና ጥቅም ሊጋፋ አይገባውም። ይህም በዓለምአቀፉ የቱሪዝም ድርጅት መርህ መሠረት በሚመለከታቸው ወገኖች መከበር ይኖርበታል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic