ተጨማሪ 28 የምርመራ ቀናት በእስር | ኢትዮጵያ | DW | 21.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ተጨማሪ 28 የምርመራ ቀናት በእስር

በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ በሽብር ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራል ኮንግሬስ አመራሮች እና የነገረ-ኢትዮጵያ ዋና አርታዒ ተጨማሪ 28 የምርመራ ቀናት ተወሰነባቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:21 ደቂቃ

ተጨማሪ 28 የምርመራ ቀናት በእስር

በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ዋና ጸኃፊ አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች የፓርቲው አመራሮች አርብ መጋቢት 9/2008 ቀን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ቀርበው ተጨማሪ 28 የምርመራ ቀናት ተሰጥቶባቸዋል። አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች 22 ተጠርጣሪዎች ሚያዝያ 7/2008 ዓ.ም. ከችሎት ይቀርባሉ። ፖሊስ 28 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ከጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ለእስር የተዳረገው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ይገኝበታል። በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው ለወራት በእስር መቆየታቸውን የተቹት የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና አያያዛቸውንም ተችተዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ እቅድ ላይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከህዳር2 እስከ የካቲት 12 2008 ዓ.ም. በ33 ወረዳዎች ብቻ የደረሰውን የሞት፤የአካል ጉዳት፤ንብረት ማውደም የእስራት፤መሰወር እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ባተተበት ዘገባ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀማቸውን ጠቁሟል። «በተቃውሞው ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን ቁጥር መንግስት እንኳ አያውቅም» የሚሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን የሆነው 'ነገረ-ኢትዮጵያ' ጋዜጣ ዋና አርታዒ ጌታቸው ሺፈራው በሽብር ተጠርጥሮ ከታሰረ ወራት ቢያልፉትም እስካሁን ክስ አልተመሰረተበትም። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የታሰረው በሙያው ነው የሚሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እስካሁን ድረስ ከማንም ጋር መገናኘት እንዳልተፈቀደለት ተናግረዋል።

በእነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ ለእስር የተዳረጉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በፖሊስ የተጠየቀባቸው 28 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የተወሰነባቸው በአከራካሪው የኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህግ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 3 አማካኝነት ነው። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽ ለማካተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic