ተገን ጠያቂዎችና ጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 01.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ተገን ጠያቂዎችና ጀርመን

በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ጀርመን ተገን እንድትሰጣቸው የጠየቁ ስደተኞች ቁጥር በኢንዱስትሪ በበለፀጉ ሌሎች ሃገራት ካመለከቱት ቁጥር ጋር ሲነፃጸር ከፍተኛ ነው ። ሆኖም አብዛኛዎቹ ጀርመን እንድትቀበላቸው የጠየቁ አመልካቾች የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት እድላቸው አነስተኛ መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሞያዎች ይናገራሉ ።

ጀርመን ውስጥ ካለ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሰቀቀን ህይወት በመግፋት ላይ የሚገኙም ጥቂት አይደሉም ።በሃገራቸው ከሚካሄድ ጦርነት የፖለቲካ ጫና የዘር ማጥፋት ወንጀልና ከመሳሰሉት ችግሮች በመሸሽ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ወደ ተለያዩ ሃገራት ይሰደዳሉ ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ሰሞን እንዳስታወቀው በጎርጎሮሳውያኑ 2013 በዓለማችን በልዩ ልዩ ችግሮች ሃገሩን ለቆ የተሰደደው ሰው ቁጥር ከዛሬ 12 ዓመት ወዲህ ከፍተኛው ነው ።ለዚህም ድርጅቱ በዋነኛ ምክንያትነት ያቀረበው የሶሪያውን የርስ በርስ ጦርነት ነው ።ከሶሪያና ከሌሎች ሃገራት ተሰደው በ2013 በኢንዱስትሪ በበለፀጉት ሃገራት ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ያመለከቱ ስደተኞች ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ ነው ። ለአብዛኛዎቹ ተመራጭዋ ሃገር ጀርመን ናት ። ጀርመን በአመልካቾች ብዛት የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች ። በዓመቱ ጀርመን ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ያመለከቱ ስደተኞች ወደ 110 ሺህ ይጠጋሉ ። ዩናይትድ ስቴትስ ሁለተኛውን ደረጃ ስትይዝ የጥገኝነት ማመልከቻ ያስገቡት ቁጥር 88 ሺህ ነው ። የጀርመን የተገን አሰጣጥ ሂደት ቢያንስ አንድ ዓመት ወይም ደግሞ ከዚያ በላይ የሚወስድ በመሆኑ ከአመልካቾቹ ምን ያህሉ ጀርመን እንደሚቆዩ አይታወቅም ። የአብዛኛው ተገን ጠያቂዎች ምርጫ ጀርመን የሆነበት ምክንያት እያነጋገረ ነው ። በራይንላንድ ጀርመን የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የመንፈሳዊ አገልግሎት መሪ ማንፍሬድ ሬኮቭስኪ ምክንያቱ ሃገሪቱ ከምትገኝበት የእድገት ደረጃ ጋር የተገናኘ ነው ይላሉ

«ይህ በርግጠኝነት ከሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታና ከማህበራዊ ስርዓታችን መረጋጋት ጋር የተያያዘ ነው ።»

ጀርመን ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች መብት የሚቆመው ፕሮአዙል የተባለው ድርጅት ምክትል ሃላፊ ቤርንት ሜሶቪክ ጀርመን ተገን እንዲሰጣቸው የሚያመለክቱ ሰዎች ቁጥር ስለ ጨመረበት ምክንያት የሰጡት አስተያየት ግን ከዚህ የተለየ ነው ።

«አብዛኛዎቹ በሌላ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገር የተመዘገቡ ናቸው ። እዚያም አብዛኛዎቹ ተገን ጠያቂዎች እስከመኖራቸው የተረሱ በአግባቡም ያልተያዙና የሃገራቱ ስደተኞች አቀባበል ስርዓት የተከተለ አይደለም ።ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ ካለ አንዳች ምክንያት ለእስር ይዳረጋሉ ። በዚህ የተነሳም ከስደተኞቹ የተወሰኑት ጀርመን የተሻለ ይሆናል በሚል ተስፋ ነው ወደዚህ የሚመጡት »

ይሁንና ይህን ተስፋ ይዘው መጀመሪያ የገቡበትን የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገር ለቀው ወደ ጀርመን የመጡ ተገን ጠያቂዎች ጀርመን ውስጥ ተገን የማግኘት እድላቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው ። ከምክንያቶቹ አንደኛው በአውሮፓ ህብረት ህግ መሰረት አንድ ተገን ጠያቂ ጉዳዩ መታየት ያለበት መጀመሪያ በገባበት ሃገር መሆኑ ነው ። የጀርመን የውጭ ዜጎችና የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጀርመን እንድትቀበላቸው የሚያመለክቱ ተገን ጠያቂዎችን ወደ መጡበት ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ ይሞክራል ። በተለይ የተሻለ አያያዝ አላቸው ተብለው ከሚታሰቡት ሃገራት የሚመጡት ሰዎች ማመልከዎች ተቀባይነት ያለማግኘት እድላቸው ከፍተኛ ነው ። በሜሶቪክ እምነት በ2013 ጀርመን ከደረሷት 110ሺህ የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻዎች አብዛኛዎቹ በቀደመው በ2012 ዓም ጥያቄአቸው ውድቅ የተደረገባቸው ስደተኞች ማመልከቻዎችም ናቸው ።ጥቂት የማይባሉም የፖለቲካ ጭቆና ወይም ኢሰብዓዊ ቅጣቶች አይፈፀሙባቸውም ለህይወት አስጊ አይደሉም ከሚባሉ የባልካን አገራት ነው የመጡት ። የጀርመን መንግሥት ከነዚህ ሃገራት የሚሰደዱትን ሰዎች ማመልከቻቸውን በቀላሉ ውድቅ ለማድረግ የሚረዳውን ህግ እያረቀቀ ነው ።«አሁን የፌደራል ጀርመን መንግስት ከምዕራብ ባልካን ሃገራት የመጡ ስደተኞች ላስገቧቸው የጥገኝነት ማመልከቻዎች መልስ መስጠት የሚችልበትን ረቂቅ ህግ እያዘጋጀ ነው ። በጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓመታዊ ዘገባ አንድ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ቢነሱም በተጠቀሱት ሃገራት ስላሉ የሰብዓዊ መብት ችግሮች ግን የተባለ ነገር ነገር የለም ። »

የዚህ ህግ ዓላማ ሰርቢያ ቦስኒያና ሌሎች 3 ሃገራትን የተረጋጉና አስተማማኝ ከሚባሉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ማስገባት ነው ። ይህ ከተደረገም ከነዚህ ሃገራት የሚመጡ የተገን ጥያቄ ማመልከቻዎችን ወዲያውኑ ውድቅ ለማድረግ ይቻላል ። ለስደተኞች መብት ተቆርቃሪው ድርጅት ምክትል ሃላፊ ቤርንት ሜሶቪክ ይህ ትርጉም የለሽ አሰራር ነው ይላሉ ። ጀርመን ተገን እንዲሰጣቸው ከሚጠይቁት መካከል የተሻለ እድል ያላቸው ሶሪያውያን ናቸው ። ምክንያቱም የሃገራቸው የሶሪያ ሁኔታ አጠራጣሪ አይደለም ። ጀርመን 10 ሺህ ሶሪያውያን ስደተኞችን ለመቀበል ቃል ገብታለች ። በጥብቅ መስፈርት ተመርጠው እስካሁን ጀርመን የገቡት ግን 3500 ብቻ ናቸው ። ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች መንገዶች ጀርመን የገቡ 11900 የሶሪያ ስደተኞች ጥገኝነት እንዲሰጣቸው አመልክተዋል ። የሶሪያ ስደተኞች ጀርመን ከሚገኙት ተገን ጠያቂዎች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ።የተገን ጠያቂዎቹ ብዛትና ጀርመን ልትቀበል ቃል የገባችው የሶሪያ ስደተኞች ቁጥር የሚመጣጠን አይደለም ። ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የራይንላንድ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ጀርመን የምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር ወደ 100 ሺህ ከፍ እንዲል ጠይቃ እንደነበር ሃላፊው ማንፍሬድ ሬኮቭስኪ ያስታውሳሉ ።

«ሁሌም ወደነርሱ የምንጠቁማባቸው ሌሎቹ ቁጥሩ ሊታመን የማይችል ስደተኛ ጫንቃቸው ላይ ተጭኗል ። ከኛ በኤኮኖሚ እጅግ ደካማ በሆኑ ጎረቤት ሃገራ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች አሉ ። እኛ ደግሞ ምን ማድረግ እንችላለን ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። »

አንዳንድ ጀርመናውያን አስተያየት ሰጭዎች ጀርመን ስደተኞች በብዛት ከተቀበለች ጫናው ይከብዳታል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ ። ሪኮቭስኪ ግን ለዚህ መልስ የሚሰጡት እጎአ ከ1992 እስከ 1995 በተካሄደው የቦስኒያ ጦርነት ወቅት ጀርመን የተቀበለቻቸውን ስደተኞች ብዛት በማስታወስ ነው ። በወቅቱ ጀርመን ግጭት ከተከሰተበት ከዚህ አካባቢ ከ320 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላለች ። ይህ አሃዝ ሪኮቭስኪ እንዳሉት በ2013 ጀርመን ተገን እንድትሰጣቸው ከጠየቁት ስደተኞች በሶስት እጥፍ ይበልጣል ። በሌላ በኩል ጀርመን ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው 400 ሺህ የሚደርሱ የውጭ ዜጎች የሚገኙባትም ሃገር ናት ። ከዛሬ ነገ ወደ ሃገራችን እንባረራለን ከሚል ስጋት ጋር የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች በሃገሪቱ ምንም መበት የላቸውም ። ትክክለኛውን የጤና አገልግሎት ዋስትናም አያገኙም ። ከነዚህ አንዷ ጀርመን ለ15 ዓመታትየኖረችው

የኢክዋዶርዋ ማርያ ናት። ማርያ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስትንቀሳቀስ ጥንቃቄ ተለይቷት አያውቅም ። ባቡር ከተሳፈረች ትክክለኛውን ቲኬት ይዛ ነው ፤ መንገድ ስታቋርጥ እንኳን መኪና የለም ብላ ቀይ መብራት ጥሳ አታልፍም ። በቀን 12 ሰዓት ወለልና መፀዳጃ ቤቶችን በምታጸዳበት የስራ ቦታዋ እረፍት አታውቅም ። በቂ ደሞዝ ባታገኝም ሁሌም በሰዓቱ በሥራ ገቦታዋ ላይ የምትገኝ አንድም ቀን አመመኝ ብላ የማታውቅ ታታሪ ሴት ነበረች ።ለ15 ዓመታት ይህን መሰሉን ህይወት በጀርመን ያሳለፈችው ማርያ ከ 5 ዓመት በፊት ጊዜ ስላጠራት የተለመደውንና ጊዜ የሚወስድባትን ነገር ግን ለርስዋ አስተማማኝ የነበረውን መንገዷን ትታ በሌላ አማራጭ መንገድ ለመሄድ ትወስናለች ። ዋናው ባቡር ጣቢያ ስትደርስ እንደ አጋጣሚ ፖሊሶች የሰዎችን ህጋዊነት ለማረጋገጥ መታወቂያ ሲጠይቁ ትደርሳለች ። ማርያ ባለፉት 15 ዓመታት ያለ ህጋዊ ሰነድ ነበርና የምትኖረው ተፈላጊውን ማስረጃ ማቅረብ አልቻለችም ። በዚህ አጋጣሚ የተያዘችው የአንዲት ልጅ እናት ማርያ ከልጅዋ ጋር ወደ ሃገርዋ ተጠርዛ ተልካለች ። ልጅዋንና ርስዋን በህክምና ይረዱ ቦን የሚገኝ የግብረ ሰናይ ድርጅት ባልደረቦች ጀርመንን ለቃ ከመሄዷ በፊትም ተሰናብታቸዋለች ። የድርጅቱ ምክትል ሃላፊ ኡልሪሽ ኮርትማን በጀርመን የማርያን መሰል ህይወት የሚገፉ ስደተኞች ህይወት አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ።

«ባህርይዋ ከሚያስቀናም ዓይነት በላይ ነበረ ። ግን በድብቅ መኖር ግዴታዋ ነበር ያልተከፈለበት የመጓጓዣ ቲኬት በባቡር ውስጥ ይዞ መገኘት ከሃገር እስከመባበረር የሚያደርስ ትልቅ አደጋ አለው ። እናም ዘወትር እያዛለሁ ወይም ተቆጣጣሪዎች ይደርሱብናል በሚል ስጋት ይኖራሉ ። ለህክምና አገልግሎት የሚሆን ገንዘብ የላቸውም ጀርመን ውስጥ ያለ ገንዘብ ምንም ማድረግ አይቻልም ።»

የቀድሞዋ መምህርት ዚግሪድ ቤከር ቪርት ቦን የሚገኝ ጀርመን ያለ ህጋዊ ሰነድ ለሚኖሩ ስደተኞች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ናቸው ። ወይዘሮዋ እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው ስደተኞቹን ሊረዷቸው ከሚፈልጉ ሃኪሞች ጋር ያገናኟቸዋል ። ችግሩ ትኩረት እንዲሰጠውም የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ ።

«የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውም ሰዎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንፈልጋለን ። ከዚሁም ጋር ተያይዞ ም በፖለቲካው ስራችን የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ኣርዳታ የማያገኙበት አሳፋሪ ድርጊት እንዲታወቅ ማድረግ እንሻለን »

ድርጅታቸው የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ያለ አንዳች ውጣ ውረድ በነፃ ነው ። የዛሬ 11 ዓመታት ሲመሰረት ይህን ያህል እድሜ ይኖረዋል የሚል ግምትም አልነበረም ። ሆኖም ችግሩ እስካሁን በመቀጠሉ ድርጅቱ ሥራውን አላቆመም ። በግብረ ሰናዩ ድርጅት ስር በልዩ ልዩ የህክምና ዘርፎች አገልግሎት የሚሰጡ 80 ዶክተሮች ታቅፈዋል ። እነዚህ ሃኪሞች የጤና ኢንሹራንስ የሌላቸውን ሰነድ አልባ ስደተኞች ያክማሉ ። የድርጅቱ ምክትል ሃላፊ ኡልሪሽ ኮርትማን እንደሚሉት አንዳንዴ የስደተኞቹ የጤና ችግር ከባድ ከሆነ መንግስት አስተያየት ሊያደርግላቸው ይችላል ።

«በተግባር እስካሁን እንደታየው ከባድ ህመም ያለባቸው ሰዎች ከሃገር እንዲወጡ አይገደዱም ። ይህ አጋጥሞ አያውቅም ። በሽተኞችም በሽታውም በግልፅ የሚታይ ሊመሰከር የሚችል ነው እነዚህ ህሙማንም ህገ ወጥ ተብለው አይታሰቡም ተገን ጠያቂዎችን ከሚመለከተው ደንብ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ድጋፍም ይደረግላቸዋል»

ራድዮ ጣቢያችን በሚገኝበት በቦን ብቻ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው 4ሺህ የሚደርሱ የውጭ ዜጎች እንዳሉ ይገመታል ።እነዚህ ስደተኞች በአንድ አጋጣሚ በተቆጣጣሪዎች እጅ ከወደቁ የማርያ እጣ ሊገጥማቸው ይችል ይሆናል ።

የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል ። አድማጮች ለአውሮፓና ጀርመን ዝግጅት ጥቆማ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ በSMS በፌስቡክ በኢሜል ፃፉልን ፤ የድምፅ መልዕክት በምንቀበልበት ስልካችንም ላይ መልዕክታችሁን ተዉልን ። የSMS መልዕክቶቻችሁን በ 0049-172-2666944 ፃፉልን ኤሚላችን amharic@dw.de ነው በስልክ መልዕክት መተው የምትፈልጉ ደግሞ ቁጥራችን 0049-228-429-16-4995 ነው ። ሳምንት በሌላ ቅንብር እጠብቃችኋለን ደህና ቆዩን ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic