ተወዳጁ የኬንያ የስላቅ ትርዒት | አፍሪቃ | DW | 20.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ተወዳጁ የኬንያ የስላቅ ትርዒት

በሌሎች አህጉራት እንደሚስተዋለው ሁሉ በአፍሪካም ቀልድ እና ስላቅ ተኮር የሆኑ ዝግጅቶች ተወዳጅነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ“ትኩረት በአፍሪካ” የኬንያው ስላቃዊ መሰናዶን “XYZ”ን ዳስሰናል፡፡ በአፍሪካ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች የምትገኘው ቻይና ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ይፋ ያደረገችውን አዲስ ዕቅድም እንመለከታለን፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

የቻይና አዲስ ዕቅድ አፍሪካንም ይጨምራል ተብሏል

ኬንያዊው ኤድዋርድ ካሂምባ በሀገሩ በቴሌቪዥን በሚተላላፍ የስላቅ ዝግጅት የ93 ዓመቱን የዚምባቡዌን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን አስመስሎ ይናገራል፡፡ “XYZ” በሚል ስያሜ የሚጠራው መሰናዶ ከአዘጋጆቹ አንዱ ነው፡፡ በመሰናዶው ካቀረባቸው የሙጋቤ ንግግሮች አንዱ ፕሬዝዳንቱ ስልጣን ላይ ረጅም መቆየትን አስመልክቶ የእንግሊዝን ንግስት በነገር ሸንቆጥ ሲያደርጉ በስላቃዊ መልኩ የሚያሳይ ነው፡፡ “ንግስቲቷን ጠይቅ፡፡ በእንግሊዝ ንግስት ሆነው ምን ያህል ቆይተዋል? - ያው ለዝንተዓለም፡፡ እና እኛ አፍሪካውያን ትንሽ ረዘም ላለ ጊዜ ብንቆይ ለምን ታሳጡናላችሁ፡፡”  

ካሂምባ እንዲህ አይነት በሁለት በኩል የተሳሉ ስላቆችን ከባልደረቦቹ ጋር ለሚያቀርብበት የቴሌቪዥን መሰናዶ ራሳቸው ሰዎቹን የመሰሉ አሻንጉሊቶችን ይጠቀማል፡፡ የዚያን ሰው ቁመና እና ግዝፈት ያህል የሆኑት አሻንጉሊቶች ትንሽ ግነት ጣል ቢደረግባቸውም ቁርጥ ባለቤቶቻቸውን ናቸው፡፡ ከዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ እስከ ኬንያው ኡሀሩ ኬንያታ እና የሀገራቸው ፖለቲከኞች ድረስ እነርሱን መሳይ አሻንጉሊት ተሰርቶላቸው በሳቅ ፍርስ የሚያደርጉ ንግግር ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፤ ይታያሉ፡፡ የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕም አልቀሩ፡፡

ፖለቲካ በተጫነው በዚህ ዝግጅት መሪዎች ይብጠለጠላሉ፤ ይወረፋሉ፡፡ ሀብታሙ ስዩም ከዝግጅቱ ተከታታይ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው፡፡ ዝግጅቱን ከተመቸው በኬንያ ቴሌዥን ጣቢያ ካለፈው ደግሞ በዩ-ቲዩብ ይመለከተዋል፡፡ አስተያየቱን ጠይቄው ነበር፡፡ “በጣም የሚገርም እና የሚያስደስት ትርዒት ነው፡፡ ለእኔ እጅግ ስሜት የሚሰጠኝ ምክንያቱ በአፍሪካ ውስጥ ልተለመደ ፖለቲካዊ ስላቅን ኪነጥበባዊ ጣዕም ባለው ሁኔታ የሚቀርበብት ትርዒት ስለሆነ ሁሌ እከታተለዋለሁ፡፡ የሚዳሰሱ ጉዳዮች ከፖለቲካ እስከ ሙስና፣ ከማህብረሰብ እስከ ጾታ ጉዳዮች ድረስ አስቂኝ በሆነ በሚያምር መንገድ የሚቀርቡበት ትርዒት ስለሆነ ሁሌ ነው የምከታተለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ብዬ የማስበው ትዕይንት ነው” ይላል ሀብታሙ፡፡

በዚህ የቴሌቪዥን መሰናዶ በእያንዳንዱ ክፍል ሸንቋጭ ሽሙጥ እና ስላቆች አይቀሩም፡፡ የዝግጅቱ አጋር መስራች የሆነው ጎድፍሬ ሞፔምባ በዕለት ተዕለት ስራው ሳይቀር ይህንኑ አካሄድ ይጠቀማል፡፡ ጋዶ በተሰኘ የአርቲስት ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ሞፔምባ በኬንያ ጋዜጦች ላይ በሚያወጣቸው ተቺ የካርቱን ስዕሎቹ የሚበሳጩ ባለስልጣናት አሉ፡፡ ጋዶ ስለስላቅ ያለውን አተያይ ሲያስረዳ “የእኔ አስተያየት ሁሌም ቢሆን ስላቅ መሄድ እስከሚችልበት ርቀት መሄድ አለበት ነው፡፡ ይህ ግን እንደሚሰራበት ርዕሰ ጉዳይ ይወሳናል፡፡ እያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ እንደየብጤው መያዝ አለበት፡፡ እኔ እንደማስበው ስላቅ ወሰኖችን እስከቻለው ድረስ መግፋት አለበት” ይላል፡፡

ኬንያ በንግግር ነጻነት የተሻለ ቦታ መገኛቷ በጀ እንጂ ይህ የጋዶ አስተያየት ብዙ ጦስ ያመጣ ነበር፡፡ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ የዛሬ 15 ዓመት ግድም አይደለም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ወጥቶ መሳለቅ ስለ ኬንያ ፕሬዝዳንት ቀልድ መናገር ራሱ አዳጋች ነበር፡፡ እንዲህ ሲባል ግን አሁንም ገደቦች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በሀገሪቱ በምርጫ ጦስ ከደረሰው ብጥብጥ እና የአልሻባብ የሽብር ጥቃቶች በኋላ የኬንያ መንግስት መገናኛ ብዙሃንን መቆጣጠሪያ አዲስ ህጎች አውጥቷል፡፡

የ “XYZ” መሰናዶ ዋናዋ የቃለ ተውኔት ጸሀፊ ሎይ አዋት ዝግጅቱ ሲጀመር “የተጓዘውን ያህል ይሂድ” በሚል እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ነገሮች እንዴት እየተወጡ እንደመጡም ታብራራለች፡፡ “ባለፈው ዓመት ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ በኩል፣ ለሰብዓዊ መብት ተከላካዮች እና የሲቪክ ማህብረሰብ ስራዎች ለሚሰሩ ሰዎች አስጨናቂ ነበር፡፡  ከፍ ያለ ውጥረት ነበር፡፡ ሰዎች ተጎድተዋል፣ ተገድለዋል፣ ጠፍተዋል፡፡ በእኛ መሰናዶ በኩልም ቢሆን ነገሮች ከባድ ነበሩ፡፡ ራሳችንን ሳንሱር የማድረግ ስሜት ነበር፡፡ በጸሀፊያን መካከል ሳይቀር ይህን መናገር እንችላለን? ይህን መናገር እንፈልጋለን? እያልን የምንከራከርባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው” ትላለች፡፡

Cartoon Karikatur Gado Obama

እንዲያም ሆኖ አሁንም ሀሳባቸውን ከማቅረብ አልታቀቡም፡፡ እንደእነርሱ አይነት ዝግጅት እንደ ደቡብ አፍሪካ በመሰሉ ጥቂት ሀገራት ካልሆነ በስተቀር በአፍሪካ ምድር አሁንም ብርቅ ነው፡፡ የፕሬዝዳንት ሙጋቤ ሀገር በሆነችው ዚምባቡዌ  አይደለም በቴሌቪዥን የተነገረ፣ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ፌስ ቡክ እና ትዊተር ላይ የተጻፈ የግል አስተያት ሳይቀር ያስከስሳል፡፡ ኢትዮጵያም ተመሳሳዩን መንገድ ተያይዛዋለች፡፡ እንዲያም ሆኖ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለስላቅ እና መሰል መሰናዶዎች ያለው አቀባበል ከኢትዮጵያ የተሻለ እንደሆነ ሀብታሙ ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ እያለ በ“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጽሁፎችን ለንባብ ያበቃ የነበረው ሀብታሙ በኬንያ እና ሌሎች አፍሪካ ሀገራት የታዘበውን ከሀገሩ ሁኔታ ጋር ያነጻጽራል፡፡

 “ከኬንያ ጋር ራሳችንን ካወዳደርን ወጣን የሚለው ነገር ሁሉ እኛን አይገልጽም፡፡ እጅግ ወደ ኋላ ቀርተናል፡፡ በቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸው የስላቅ ብቻ ሳይሆን ቀጥታ የፖለቲካ ትችት የሚያቀርቡበት፣ በእኛ ህግ ውስጥ ዘለፋ ነው ብለህ ፍርድ ቤት ብትወስዳቸው ሊያስቀጣ የሚችሉ ጉዳዩች ሁሉ እዚህ እንደተለምዷዊ የመናገር ነጻነት ተቆጥረው ሲንሸራሸሩ ታያለህ፡፡ ሰዎች ከሞላ ጎደል ሙሉ ነጻነት አላቸው፡፡ ከስላቅ እና ከመዝናኛ ትርዒቶች ውጭ በርካታ ነገሮችን የመናገር መብቱ፣ አቅሙ አላቸው፡፡ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ይሄ ይሄ በጣም ያስቀናል፡፡ በጣም ይገርማል፡፡ ከአፍሪካ አንጻር ከብዙ አፍሪካውያን ጋር ስንወዳደር ከኋላ ሆነን እየነዳን ያለን እንጂ ከፊት ሆነን እየመራን ያለን ህዝቦች አይደለንም ብዬ አስባለሁ” ይላል ሀብታሙ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች