ተቃውሞ የተጠናከረባቸው የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ | አፍሪቃ | DW | 06.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ተቃውሞ የተጠናከረባቸው የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ

የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ የፊታችን ሰኞ፣ ነሀሴ ሁለት፣ 2016 ዓም ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ። ጎረቤት ሀገራት በሚያደርጉት ፀረ ሽብር ትግላቸው ላይ ዴቢን አስተማማኝ አጋር አድርገው ይመለከቱዋቸዋል። በሀገራቸው ግን የሕዝቡ ቅሬታ እያየለ መጥቶዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:15

ተቃውሞ በቻድ

በማዕከላይ አፍሪቃ ጠንካራ የሚባሉት የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ የፊታችን ሰኞ ቃለ መሀላ መፈፀም አዲስ አይደለም። የቀድሞው የጦር መኮንን ዴቢካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ ይገኛሉ። ምዕራቡ ዓለም ለቻድ ፕሬዚደንት ጥሩ አመለካከት ነው ያለው። መረጋጋት በተጓደለው የማዕከላይ አፍሪቃ አካባቢ ቻድ በንፅፅር የተረጋጋች ናት። ለዚህም በሚገባ የሰለጠነው ጠንካራው የሀገሪቱ የፀጥታ አውታር ከፍተኛ ሚና ተጫውቶዋል። የቻድ ጦር በጎረቤት ናይጀሪያ፣ ኒዠር እና ካሜሩን በሚሊሺያው ቡድን ቦኮ ሀራም አንፃር ችግሩ ከተስፋፋባቸው ሀገራት ጦር ጋር ባንድነት ትግል ያካሂዳል። በማሊ በተሰማራው የተመድርጅት ተልዕኮ ውስጥ ቻድ ከ1,000 የሚበልጡ ወታደሮች አሰልፋለች። የአውሮጳ መንግሥታት ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚፈልሱትን ስደተኞች የሚያልፉባቸውን መንገዶች በመቆጣጠሩ ጥረታቸው ላይ በቻድ ፕሬዚደንት ዴቢ ርዳታ ላይ ይተማመናሉ።


የቻድ ጦር ዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ አመለካከት ቢያተርፍም፣ የፕሬዚደንቱ የሀገር ውስጥ ፖሊሲ ብዙውን የቻድ ዜጋ ቅር እያሰኘ ነው። የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች በእስረኛ በተጨናነቁበት ባሁኑ ጊዜ፣ ፕሬዚደንት ዴቢ ለሰኞው የቃለ መሀላ ፍፀማ ስነ ስርዓት አዲስ የናጠጠ ሆቴል አሰርተዋል። የመንግሥት ሰራተኞች ካለፉት ብዙ ወራት ወዲህ ደሞዝ አልተከፈላቸውም። እንደ በቻድ የሚገኘው የጀርመን ካቶሊውያን ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ «ሚዜሬዎር» ባልደረባ ቨንሶ ሄንድሪክስ ግምት፣ ይህ ሁኔታ ይቀየራል የሚል ተስፋም የለም።
ተቃዋሚዎች ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኢድሪስ ዴቢ አንፃር በተፎካካሪነት ቀርበው የነበሩት ስድስት የቀድሞ ፕሬዚደንታዊ እጩዎች ሌላ መንግሥት የማቋቋም እቅድ እንዳላቸው አንዱ እጩ ሳሌህ ኬብዛቦ አመልክተዋል።
« የዴቢ ድል ሕጋዊ እና ትክክለኛ አልነበረም። እውነቱ እስኪያሸንፍ ድረስ ስልጣናቸውን መቃወማችንን እንቀጥላለን። የሕዝብን ደህንነት በሚያስቀድም መንግሥት እንታገላቸዋለን። እርግጥ፣ ዴቢ የጦር ኃይሉን፣ ፊናንሱን እና መንግሥቱን ይቆጣጠራሉ። ያም ቢሆን ግን እንቃወማቸዋለን። ጊዜው ሲያመችም ይህን መንግሥት እናቋቁማለን። »


ፕሬዚደንት ዴቢን ድል አሁንም ያልተቀበሉት ወደ ሀያ የሚጠጉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቋቋሙት አዲሱ የለውጥ ግንባር፣ በምህፃሩ «ፎናክ» በቃለ መሀላው አንፃር መዲናይቱን ንጃሜና ጨምሮ፣ በመላይቱ ሀገር ከዛሬ ጀምሮ የሶስት ቀናት የተለያየ ተቃውሞ እንደሚያደርግ የ«ፎናክ» አስተባባሪ መሀመድ አማድ አላቦ አስታውቀው ነበር።
« የጀመርነው ትግል ዓላማ በትዕይንተ ሕዝብ፣ ወይም በተቃውሞ ሰልፍ ወይም በስራ ማቆም አድማ ብቻ የሚወሰን አይሆንም። በምርጫ ስም መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶብናል። በሀገሪቱ ራሱን ፕሬዚደንት ብሎ የሚጠራ በሕገ ወጥ መንገድ ስልጣን የያዘ ግለሰብ ነው ያለው። ይህንን እንቃወማለን፣ ልክ እንደኛ ወይም ከዚያም በበለጠ ሁኔታ የዚሁ ድርጊት ሰለባ የሆነው የቻድ ሕዝብም በዚሁ ተቃውሞ ከኛ ጋር እንዲቀላቀል ነው የምንቀሰቅሰው። »
ይሁንና፣ የሀገሪቱ የፀጥታ ጥበቃ ሚንስትር አህማት ባሺር ተቃውሞው የሀገር ፀጥታን የሚያውክ ነው በሚል እንዳይካሄድ ከልክለዋል።
« እነዚህ የተሸነፉት እጩዎች የሕዝቡን ደህንነት እና የሀገሪቱን መረጋጋት ለማወክ በሕገ ወጥ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። በመሆኑም፣ «ፎናክ» በመላይቱ ሀገር ሊያካሂደው ያቀደው ትዕይንተ ሕዝብ፣ እንዲሁም፣ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይደረግ ለመከልከል ወስኛለሁ። »

Tschad N'Djamena Prozess Menschenrechtsaktivisten Protest

ሳሌህ ኬብዛቦ

ይህን ትዕዛዝ የማያከብር ጠንካራ ርምጃ እንደሚወሰድበት የፀጥታ ጥበቃ ሚንስትር አህማት ባሺር አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዚደንት ድሪስ ዴቢ ባለፈው ሚያዝያ 10፣ 2016 ዓም ያሸነፉበት ምርጫ ነፃ እና ትክክለኛ እንዳልነበረ ተንታኞች ይተቻሉ። ምርጫውን ተከትሎ በመንግሥቱ አሰራር አንፃር ትችት የሰነዘሩ ወገኖች ሰላማዊ ተቃውሞ ካደረጉ በኋላ ታስረዋል። የቻድ ጊዚያዊ ሁኔታ ከዚያን ጊዜ ወዲህ እየተካረረ መጥቶዋል፣ ብዙ የቻድ ዜጎች «ፌስቡክ፣ ትዊተር ወይም ዋትስአፕ»ን በመሳሰሉ የማህበራዊ ድረ ገፆች መጠቀም እንደማይችሉ የገለጹት «ገደብ የማያርፍበት ኢንተርኔት» የሚል መጠሪያ የያዘው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት፣ የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ ጁሊ ኦዎኖ አስታውቃለች።
« ጋዜጠኞች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ማግኘት አለመቻላቸውን፣ የተቋማት ባለቤቶችም በመላ ዓለም ካሉት ደንበኞቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን ገልጸውልናል። ይህ ቀላል ያልሆነ መዘዝ አስከትሎባቸዋል። በስዊትዘርላንድ የሚገኘው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ በያመቱ የሚያወጣቸው ዘገባዎች በኢንተርኔት የሚካሄደው የኤኮኖሚ ግንኙነት ምን ያህል ክፍተት እንዳለው አሳይቶዋል። በመድረኩ መዘርዝሮችም ውስጥ ቻድ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። »
በማህበራዊ ድረ ገፆች መጠቀም ላልተቻለበት ድርጊት የቻድ መንግሥት ቴክኒካዊ ምክንያቶችን ይሰጣል። የቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ከማል አፎኝ ግን ይህን የመንግሥቱን አባባል ይጠራጠሩታል።
« ሕዝቡ በማህበራዊ ድረ ገፆች እንዳይጠቀም ለማገድ ቴክኒኩ አለ። የቻድ መንግሥት ከ2016 ዓም መጀመሪያ ወዲህ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሰራተኞች የማህበራዊ ድረ ገፆች አጠቃቀምን እንዲገድቡ ትዕዛዝ ሰጥቶዋል። ስለዚህ የማህበራዊ ገፆች ገደብን በተመለከተ ቀጣይ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው። »
እርግጥ፣ ይህ ዓይነቱ የማህበራዊ ድረ ገፆች ገደብ ወይም እገዳ በሌሎች አፍሪቃውያት ሀገራትም በተለይ ከምርጫ በፊት ታይቶዋል፤ ግን፣ አዘውትሮ ካጭር ጊዜ በኋላ መነሳቱ አይዘነጋም።
ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ አምስተኛውን የስልጣን ዘመናቸውን በይፋ ሊጀምሩ ጥቂት ቀናት በቀራቸው ባሁኑ ጊዜ ሕዝቡ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ገደብ አርፎዋል፣ የኑሮው እና የስራው ሁኔታም አልተመቻቸም በሚል ቁጣውን በማሰማት ላይ ነው። ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት አጥቶዋል። በተመድ የሰብዓዊ ልማት መዘርዝር ላይ ቻድ 185ኛ ቦታ ላይ ትገኛለች።

Audios and videos on the topic