ተቃውሞ በጋምቢያ፤ የMONUSCO ቆይታ በኮንጎ | አፍሪቃ | DW | 21.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ተቃውሞ በጋምቢያ፤ የMONUSCO ቆይታ በኮንጎ

የጋምቢያ ፕሬዝደንት የሥልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ማሰባቸው ዜጎችን አላስደሰተም።በሌላ በኩል የተመድ የፀጥታው ምክር  ቤት ከሰሞኑ በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ያሰማራውን የፀጥታ አስከባሪ ኃይል በምህፃሩ MONUSCO የቆይታ ጊዜ በአንድ ዓመት አራዝሟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:30

ትኩረት በአፍሪቃ

የጋምቢያ ፕሬዝደንት የሥልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ማሰባቸው ዜጎችን አላስደሰተም።  በዚህም ምክንያት ሰሞኑን ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ገልጿል። በጎርጎሪዮሳዊው 2017 አዳማ ባሮው  ወደ ፕሬዝደንትነቱ የሥልጣን  መንበር ሲመጡ በቀዳሚያቸው ያህያ ጃሜህ የ22 ዓመት ጭካኔ የተላበሰ  አመራር ለተጎሳቆለው ሕዝብ እፎይታ ይሰጡታል የሚል ተስፋ ነበር። እሳቸውም በወቅቱ የሕዝቡን የኑሮ ሁኑታ ለማሻሻል፤ ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን እንደሚያመጡ እንዲሁም የተከፋፈለችውን ሀገር ጉዳት የሚጠግን የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽን እንደሚያቋቁሙ ቃል ገብተው ነበር። በዚህ ብቻም አላበቁም በሦስት ዓመት ውስጥ የፕሬዝደንትነቱን መንበር ለመልቀቅም እንዲሁ ቃላቸውን ሰጥተዋል። ሆኖም በቅርቡ የሥልጣን መንበር ቆይታቸውን የማራዘም ፍላጎታቸውን ይፋ አድርገዋል። በምክንያትነት ያቀረቡትም የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ለፕሬዝደንት የሚሰጠውን የሥልጣን ጊዜ አላጠናቀኩም የሚል ነው።

አዳማ ባሮው ወደ ሥልጣን የመጡት በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም በተካሄደው ምርጫ በሀገሪቱ የተመሠረተው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅንጅት መሪ ሆነው ነው። በወቅቱም ፓርቲው ፕሬዝደንት የሚሆነው መሪው ሥልጣን የሚይዘው ለሦስት ዓመት እንደሆነ እና በሽግግር ፕሬዝደንትነቱም ቀጣዩን ምርጫ የማደራጀት ኃላፊቱን እንደሚወጣ፤ በምርጫ ተፎካካሪነትም እንደማይቀርብ ተስማምቶ ነበር። ሆኖም ግን ይህ ስምምነት በሕግ የተደገፈ እንዳልሆነ ነው ተንታኞች የሚናገሩት። በዚሁ መሠረትም ባሮው በጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2021 በጋምቢያ ለሚካሄደው ምርጫ መዘጋጀት ጀምረዋል። የሕጉን ጉዳይ የሚተነትኑት ምሁራን ፕሬዝደንቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አምስት ዓመት በሥልጣን የመቆየት መብት እንዳላቸው ይናገራሉ። በዩናይትድ ስቴትሱ ማያሚ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት አብዱላይ ሳይኔ ግን፤ «ይህ  በፓርቲው  መሪዎች የተፈረመው  ስምምነት ምንም እንኳን ሕጋዊ ማሠሪያ የለውም ቢባልም የሞራል ጉዳይ በውስጡ እንዳለ አይዘንጋ።» ባይ ናቸው።

ወደ ሀገር መሪነት ከመምጣታቸው አስቀድሞ ትምህርት ላይ በነበሩባት ብሪታንያ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩት አዳማ ባሮው ቃላቸውን አጥፈዋል ከሚሏቸው መካከል ታዋቂው የጋምቢያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ማዲ ጆባርተ፤ ባሮው አግኝተውት የነበረው አጋጣሚ እንደባከነ ዕድል ይቆጠራል ይላሉ።

«የምንመለከተው ባሮው ቃላቸውን አጥፈው መንቀሳቀሳቸውን ነው፤ በዚያም ላይ ከቀድመው አገዛዝ የቀዷቸው ልማዶችም አሉ። እርግጥ ነው የዘፈቀደ እስራት እና ሰዎች ተገድደው መሰወራቸው ቀርቷል። ሆኖም የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ ግልፅነት መጉደል እና የሕዝብን ሀብት አላግባብ መጠቀም አለ።» ይላሉ።

Gambia Präsident Adama Barrow

ፕሬዝደንት አዳማ ባሮው

በጃሜህ ዘመነ ሥልጣን የምክር ቤት አባል እና የሲቪል ሰርቪስ ኃላፊ የነበሩት ሞሞዱ ሳባሊ በውጭ ፖሊሲ ረገድ ባሮ የተሻለ አቀራረብ እንዳላቸው ነው የሚናገሩት። እንደእሳቸው ከሆነም ባሮው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር አላስፈላጊ ፍጥጫ ውስጥ መግባትን አልፈለጉም፤ ይህ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። በሌላ በኩል በጃሜህ ዘመነ ሥልጣን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባዎች ጉዳይ በእውነት እና እርቀ ሰላም ኮሚሽኑ እንዲመረመር ቢታሰብም እስካሁን ተጎጂዎች ድርጊቱን በመፈፀም የተጠረጠሩ ከእስር ተለቀዋል በሚል ይተቻሉ። ሌላው በባሮው አስተዳደር ላይ የሚቀርበው ትችት ደግሞ የሀገሪቱን የኤኮኖሚ ይዞታ ይመለከታል። በአንድ ወገን አንዳንድ ለውጦች ታይተዋል ቢባልም የዋጋ ግሽበቱ በፍጥነት እየጨመረ፤ የምግብ ዋጋ በተለይም ደግሞ ለድሀ ጋምቢያውያን የሚቀመስ እንዳልሆነ ይነገራል። በዚያም ላይ የውኃ እና የኤሌክትሪክ ዋጋ እጅግ ተወዷል፤ ከዚህ አልፎም ያለው መቆራረጥ ህዝቡን አማርሯል። የኑሮ ውድነቱ መዘዝ መሆኑ በተገለፀው የሀገሪቱ ወጣቶች ስደት አለመቆምም በአዲሱ የጋምቢያ መንግሥት የሥራ  አፈፃፀም ያልተደሰቱ ወገኖች ፕሬዝደንት አዳማ ባሮው ከሥልጣን እንዲነሱ በገፊ ምክንያትነት ከሚያነሷቸው ይደመራል።

ከዋና ከተማ ባንጁል ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ በሺህዎች የተገመቱ ዜጎች ፕሬዝደንቱ ወደ ሥልጣን በመጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት አማካኝነት የገቡትን ቃል በማክበር መንበራቸውን እንዲለቅቁ ባሳለፍነው ሳምንት ጠይቀዋል። የተቃውሞው አስተባባሪዎች  በዚህ ጉዳይ ፕሬዝደንቱን ለማነጋገር መሞከራቸውን ሆኖም ግን አዳማ ባሮው የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እንዳሉ ነው የተናገሩት። ሽሪፍ ሲሴ ተቃውሞውን የሚያስተባብረውን ኮሚቴ  ካቋቋሙት አንዱ ሲሆኑ በተቃውሞው ዕለት ለመንግሥት ባለሥልጣናት  ባቀረቡት ሰነድ ውስጥ የተካተተውን እና የሕዝቡን ፍላጎት እንዲህ ይገልጻሉ።

«በጣም ቀላል መልእክት ነው፤ መግባቢያ ሰነድ ነው። ምክንያቱም ይህ ቅንጅት ሦስት ዓመት ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ አያደርግም፤ ይህ ደግሞ ቅንጅቱ ከተመሠረተባቸው መሠረታዊ ምሠሦዎች አንዱ ነው። በተጨማሪም ፕሬዝደንት ባሮው ከፓርቲያቸው ሊሰናበቱ እንዲሁም  በመግባቢያ ሰነዱ ውስጥ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል። እኛ ጋምቢያውያን ድምፅ የሰጠናቸው ለሦስት ዓመት ብቻ ነው፤ ከሦስት ዓመቱ እንዲያልፉ አንፈቅድላቸውም። ይህ የተሰበሰበ ፊርማ በጣም ቀላል መልክት ነው የያዘው። መልእክቱ እንዲህ ነው የሚጀምረው፤ ክቡር ፕሬዝደንት ቃልዎን ያክብሩ፤ ነገ መልካም  ታሪክ ይኖርዎታል።»  

ለተቃውሞ ከወጡት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ ሦስት ዓመት ይከበር ሲሉ ጮኸዋል። በእጃቸው ካነገቧቸው መፈክሮች አንዱም «ባሮው ጋምቢያን ያስቀድሙ!» ይላል። ፕሬዝደንት አዳማ ባሮው የጋምቢያ ፕሬዝደንት ሆነው መንበሩ ላይ ከተቀመጡ የፊታችን ጥር 10 ቀን 2012 ዓ,ም ሦስት ዓመት ይሞላቸዋል። የተቃውሞው አስተባባሪዎች ፕሬዝደንቱ  የሕዝቡ ጥያቄ ሰምተው በተጠቀሰው ጊዜ ሥልጣን ካልለቀቁ ተቃውሞ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

የተመድ የሰላም አስከባሪዎች በኮንጎ

የተመድ የፀጥታው ምክር  ቤት ከሰሞኑ በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ያሰማራውን የፀጥታ አስከባሪ ኃይል በምህፃሩ MONUSCO የቆይታ ጊዜ በአንድ ዓመት አራዝሟል። ምንም እንኳን ተልእኮው ቢራዘምም ድርጅቱ ያሰማራቸውን ወታደሮች ቁጥር ግን ቀንሷል። ቀደም ሲል በስፍራው የሚገኙት 15,900 ወታደሮች ሲሆኑ አሁን 1200ው ይቀነሳሉ ተብሏል። በአንፃሩ የፖሊስ መኮንኖች ቁጥር ይጨምራል። የፀጥታው ምክር ቤት የሰላም አስከባሪው ኃይል ከኮንጎ ቀስ በቀስ እንደሚወጣ በማመልከቱ የዴሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት ከመንግሥታቱ ድርጅት ጎን በመሆን በመውጣቱ ሂደት ላይ አብሮ ለመሥራት መዘጋጀቱን አስታውቋል። በርካታ የታጠቁ አማፅያን በሚያደርጉት ግጭት እና እንቅስቃሴ ለተወጠረችው ዴሞክራቲክ ኮንጎ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች እዚያ መቆየት ፀጥታውን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ጦር ሠራዊትም በማሻሻል ሂደት ድርሻ እንደሚኖረው የዶቼ ቬለው ጋዜጠኛ ትሬሶ ኪባንጉላ  ይናገራል።

«MONUSCO ኮንጎ ውስጥ የሚቆየው በቀውስ የተናጠውን አካባቢ ፀጥታ ለማስጠበቅ ብቻም አይደለም፤ የኮንጎን ጦር ኃይል ዳግም በማዋቀሩ ሂደትም ድርሻ እንዲኖረው ይፈለጋል። ምክንያቱም ግጭቱ በአንድ ጀንበር የሚያቆም አይደለም። ዛሬም ከአንድ መቶ የሚበልጡ የአማፂ ቡድኖች በአካባቢው መኖራቸውን እየቆጠርን ነው።»

ኪባንጉላ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተካተቱበት የኮንጎ ምርምር ቡድን አባል ነው። እሱ እንደሚለውም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ቢኖርም ባይኖርም በሀገሪቱ ያለው ቀውስ ይቀጥላል። ለዚህም ነው በመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ጊዜው እንዲራዘምበሙሉ ድምፅ ያጸደቀው። የMONUSCO የቆይታ ጊዜ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2019 የመጨረሻ ቀን ማለትም በመጪው ማክሰኞ ታኅሣስ 21 ቀን 2012 ዓ,ም ነበር የሚያበቃው። ምንም እንኳን ለሁለት አስርት ዓመታት ሰላም አስከባሪው ኃይል ኮንጎ ውስጥ ቢቆይም በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች  የሚንቀሳቀሱትን አማፅያን ቡድኖች ሊቆጣጠር አልቻለም። ከፍተኛ ወጪ እንደተመደበለት የሚገለፀው ይኸው የሰላም አስከባሪ ኃይል ባለበት በየጊዜው ሲቪሎች መገደላቸው ለትችት አጋልጦታል። ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃቶችን እንደጦር መሣሪያነት መጠቀም እንዲቆም ላበረከቱት አስተዋፅኦ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሰላም ኖቤል የተሸለሙት፤ የኮንጎ ዜጋ የሆኑት ዶክተር ዴኒስ ሙኩዌጌ የሰላም አስከባሪው ኃይል በሌለበት አሰቃቂው ድራማ ሊባባስ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

«MONUSCO ባለበትም አሁንም ቀውሱ መገታት አልቻለም። እነዚህ ባለሰማያዊ ባርኔጣዎች ከሌሉ ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ አሰቃቂ ይሆናል። ሰዎችን ይህን ከግምት ማስገባት ይኖርባቸዋል።»

በኮንጎ የሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ቃል አቀባይ ማቲያስ ጊልማን በበኩላቸው MONUSCO በነበረው ቆይታ አከናውኗል ያሉት እንዲህ ይጠቅሳሉ።

«የዛሬ ሃያ ዓመት የተመድ ወታደሮች ሲመጡ ሀገሪቱ ከመፈረካከስ ዳርቻ ደርሳ ነበር። የተመድ ተልእኮ ነው የአሁኑ የሀገሪቱ ድንበር መኖር እንዲችል አድርጓል። አሁን ያለንን ገንዘብ እና አቅም፤ የኮንጎ ጦር ሠራዊት ሀገር ለማረጋጋት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ላይ እናውለዋለን።»

ዴሞክራቲክ ኮንጎ አዲስ ፕሬዝደንት ካገኘች ወዲህ የአሠራር ለውጦች መታየት ጀምረዋል።ፕሬዝደንት ፊሊክስ ቼሼኬዲ ዓለም አቀፍ ድጋፍ በደስታ የሚቀበሉ አይነት ቢሆንም በሀገሪቱ የተሰማራዊ የተመድ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ግን እንዲወጡ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ተነግሯል። ፕሬዝደንቱ ደጋግመው ባካሄዷቸው ጉባኤዎች እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዞዎች በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል የሚንቀሳቀሱ አማፅያንን በተመለከተ የጋራ አቋም እንዲኖር በጎረቤት ሃገራት ጋር ሳይቀር ሰላም እንዲወርድ ጥረት አድርገዋል። ምክንያቱም አብዛኞቹ የኮንጎ አማፅያን መንቀሳቀሻቸውን በጎረቤት ሃገራት ያደረጉ ናቸው። ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሰላም ከሆነች ከተፈጥሮ ገፀ በረከቷ ጎረቤቶቿም ሊቋደሱ እንደሚችሉ በማሳመን የንግድ ትስስር ለማጠናከር የሞከሩት ፕሬዝደንቷ የምሥራቅ አፍሪቃ ትብብር ውስጥ ኮንጎም እንድትገባ እየሞከሩ ነው። ይህ ጥረታቸው በተመድ የታላላቅ ሐይቆች ሃገራት አካባቢ አምባሳደር ሁዋንጊ ሺያ ሳይቀር አበረታች ተቀባይነት አግኝቷል፤ በጥረቱም የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ነው። በአንጻሩ ግን  ምንም እንኳን የቼሼኬዲ ጥረት አዎንታዊነት ቢኖረውም በአጎራባች ሃገራት ማለትም በሩዋንዳ እና ዩጋንዳ፤ እንዲሁም በሩዋንዳ እና ቡሩንዲ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ውሎ አድሮ ወደኮንጎ ምድር ላለመዝለቁ ዋስትና እንደሌለ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ  የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል በቆየባቸው 20 ዓመታት የወታደዎቹን ሕይወት ገብሯል። በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር በጀት ያለው ይህ ተልእኮ ሲጀመር 16 ሺህ ወታደሮችን ነበር ያሰማራው። የሀገሪቱ ፖለቲከኞች የሰላም አስከባሪው ተልእኮ መቀነሱን ብሎም ፈፅሞ ከሀገሪቱ መውጣቱን ቢጠይቁ እና በጥያቄያቸው ቢገፉበትም በድርጅቱ ሥር የተቀጥጠሩ የሀገሬውን ሠራተኞች ግን ስጋት ላይ ጥሏል። ካለፈው ሰኔ መጨረሻ ጀምሮ ዴሞክራቲክ ኮንጎን ለማረጋጋት የተሰማራው የመንግሥታቱ ድርጅት ተልእኮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ቢሮዎቹን በመዝጋት ላይ ነው። 764 የሀገሬው ሲቪል ሠራተኞቹንም አሰናብቷል። በአንፃሩ 2,600 ገደማ ሲቪል የውጭ ዜጎች የተልእኮው ሠራተኞች መሆናቸው ቅሬታ አስነስቷል።

እንዲያም ሆኖ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የMONUSCO ተልእኮ  ቀስ በቀስ ከኮንጎ እንዲወጣ በፀጥታው ምክር ቤት ቢወሰንም አሁንም በዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የሚጫወተው እጅግ ጠቃሚ ሚና እንዳለ አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ 

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic