ተቃውሞ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ | ዓለም | DW | 02.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ተቃውሞ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 12 ደርሷል፡፡ ተቃውሞው ከስልጣናቸው ለመውረድ አሻፈረኝ ባሉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ካቢላ ከመንበራቸው በመልቀቅ ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ሆኖም ምርጫው ወደ ታህሳስ 2018 መገፋቱ ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29

ተቃዋሚዎች ካቢላ ስልጣን እንዲለቅቁ ጠይቀዋል

በኪንሻሳ ከሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ ባለፈው እሁድ ረፋድ ላይ የተለመደ ዝማሬ ሲሰማ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች በኃላ ግን ዝማሬውን ወደ ዋይታ ፣ የምዕመናኑን ጥሞና ወደ ነፍስ አውጭ ትርምስ የሚከት ክስተት ተከተለ፡፡ የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ አዳራሹን በጭስ አፈነው፡፡

በዋዜማው የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የካቶሊክ ቤተክርስቲያናት ህብረት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ላለፉት 17 ዓመታት በስልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዘዳንት ጆሴፍ ካቢላ ስልጣናቸውን ያስረክቡ ዘንድ ጠይቀው ነበር፡፡ የሀገሪቱ ዜጎች እሁድ ዲሴምበር 31 ቀን 2017 የቤተክርስቲያን ስርዓት ካለቀ በኋላ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ 160 የሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ጥሪውን ተቀላቅለዋል ፡፡

የሀገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ግን በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ የሚገኙ አብያተ ክርስቲየናት ምዕመናን በዕለቱ ለመበተን በወሰዱት የሃይል ርምጃ በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸውን፣ በርካቶች መቁሰላቸውን እና123 መታሰራቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ቃል አቀባይ ፍሎረንስ ማርቻል አስታውቀዋል፡፡ ከክስተቱ በኃላ መርቲን ፋዩሉ የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛ ስሜታቸውን እንዲህ አጋርተዋል፡፡ ‹‹በዓለም ላይ የሚገኝ እያንዳንዱን  ሰው  የምንነግረው ይሄ ሰው ስልጣን መልቀቅ እንዳለበት ነው፡፡ይሄ ሰው ኮንጎን አይወድም ፣ይሄ ሰው ከኮንጎ ጋር አንዳች ነገርም የለውም፡፡የእሱ ሰዓት አልቋል›› ብለዋል፡፡

በስልጣን ላይ ያሉት ካቢላ በዲሴምበር 31 ቀን 2016 በካቶሊክ ቤተክርስቲያን አሸማጋይነት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበረ ስምምነት ስልጣን የሚያስረክቡበትን ሁኔታ አሳውቀው ነበር፡፡ ስምምነቱን ያነበቡት በኮንጎ የካቶሊክ ቤተክርስቲያ መሪ ማርሴል ኡተንቢ ነበሩ፡፡ ‹‹በዲሴምበር 19 ቀን 2016 የተጠናቀቀው ሁለተኛው እና የመጨረሻው የፕሬዘዳንትነት ዘመን አይታደስም፡፡ ፕሬዘዳንቱ ሶስተኛ የስልጣን ዘመን አይጠይቁም፡፡ ብሄራዊ እና አከባቢያዊ ምርጫዎች ከዲሴምበር 2017 በፊት ይደረጋል›› ሲሉ የስምምነቱን ዝርዝር አሳውቀዋል፡፡

ስምምነቱ ይሄን ይበል እንጂ ከሰሞኑ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን እስከ ጎርጎሮሳዊው ዲሴምበር 2018 ድረስ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደማይደረግ ማሳወቁን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ካቢላ በስልጣን ላይ ለመክረም የዘረጉት ስልት ነው በሚል ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ክስተቱ በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና የሀገሪቱ መንግስትና የጸጥታ ሃይሎች የህዝቦችን የመናገር እና የመናገር ነጻነት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መላው የሀገሪቱ የፖለቲካ ተዋናያን በዲሴምበር 2016 የተፈረመውን ስምምነት ምርጫ ለመከወን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ብቸኛው ተስማሚ መንገድ መሆኑን አስታውሰው እንዲከበር አሳስበዋል፡፡

ሀብታሙ ስዩም

ሸዋዬ ለገሠ 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች