ተቃዋሚዎች ለኬንያ መንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ | አፍሪቃ | DW | 26.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ተቃዋሚዎች ለኬንያ መንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ

የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መንግሥት ጥያቄአቸውን እንዲቀበል ያቀረቡት ጥሪ በጎ ምላሽ ካላገኘ በሃገሪቱ የሰፈነው ውጥረት ሊባባስ እንደሚችል አንድ የፖለቲካ ተንታኝ አስታወቁ ።

ደቡብ አፍሪቃ ፕሬቶሪያ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሪውስ አታ አሳሞህ የኬንያ ተቃዋሚዎች ብሄራዊ ውይይት እንዲካሄድ ያቀረቡትን ጥያቄ መንግሥት ካልተቀበለ ተቃውሞ ማስከተሉ ስለማይቀር በኬንያ ሁኔታዎች ወደ ባሰ ደረጃ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል ። ሆኖም እንደ ተንታኙ እንደ ከዚህ ቀደሙ የከፋ ብጥብጥ ይነሳል ተብሎ አይጠበቅም ።

የኬንያው ተቃዋሚዎች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት በደረሰባት በኬንያ ብሄራዊ ውይይት እንዲካሄድ የጊዜ ገደብ አስቀምጠው ጥሪ አቅርበዋል ። የብርቱካናማው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ውይይቱ በጎርጎሮሳውያኑ እስከ ፊታችን ሐምሌ 7 ወይም ሰኔ 30 2006 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ነው የጠየቁት ።መንግሥት በበኩሉ የሃገሪቱ ተቋማትም ሆኑ ህገ መንግሥታዊው ስርዓት ተግባር ባለመቋረጡ ብሄራዊ ውይይት የሚካሄድበት መሠረት የለም ሲል ኦዲንጋ ያቀረቡትን ጥሪ አጣጥሏል ።

መንግሥት የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኦዲንጋን ወደ ፖለቲካው ማዕከል ለመግባት ቀውስ እየፈጠሩ ነው ሲልም ከሷል ። የብሄራዊ ውይይት ጥሪ ያቀረቡት ኦዲንጋ መልስ ካላገኙ ህዝቡን ያስጨንቃሉ ያሏቸውን የፀጥታ ጥበቃ ክፍተትን ሙስናንና የኑሮ ውድነትን በመቃወም በመላው ኬንያ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድም አቅደዋል ። ደቡብ አፍሪቃ ፕሬቶሪያ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሪውስ አታ አሳሞህ የታቀደው የተቃውሞ ሰልፍ ሊያመጣ የሚችለው መፍትሄ አልታየቸውም ። ይልቁንም በርሳቸው አስተያየት ተቃውሞው በሃገሪቱ የሰፈነውን ውጥረት ሊያባብስ ይችላል ።

« እንደታቀደው ሰላማዊ ሰልፉ ከተካሄደ ያ ማለት መንግሥት ተቃዋሚዎች ላቀረቡት ጥያቄ ትኩረት አልሰጠም ማለት ነው ። እናም የሰላማዊ ሰልፉ መደራጀት በርግጥ በሃገሪቱ የተፈጠረውን ውጥረት ያባብሰዋል ። ምክንያቱም የተሃድሶና ዲሞክራሲ ህብረት በምህፃሩ ኮርድ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ አንዳንድ መሪዎች የሚያወጡትን መግለጫ ስንመለከት መንግስት ጥያቄውን የማይመለከተው ከሆነ የራሳቸውን ፕሬዝዳንት እንደሚሰይሙ አስታውቀዋል ። እነዚህ ሁኔታዎችን በጣም የሚያቀጣጥሉ መንግሥትን በመቃወም የሚወጡ መግለጫዎች ናቸው ።ስለዚህ ተቃውሞው የሚቀጥል ከሆነ እየተባባሰ የሄደውን ውጥረት አያረግብም ። እንዲያውም ይበልጥ ያባብሰዋል ።»

ኦዲንጋ ላቀረቡት ጥያቄ መንግስት መልስ ባይሰጥ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱ አልተናገሩም ። ሆኖም ከግንቦት 23 የጀመሩትን የተቃውሞ ሰልፍ በመላ ሃገሪቱ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ። በቅርቡ በኬንያዋ ምፔኬቶኒ በደረሱት ጥቃቶች ሰዎች መገደላቸው ውጥረቱን አባብሷል ።የጎሳ ግጭት ባየለባት በዚህች ከተማ የደረሰው ጥቃቱ ክፍፍሉን አስፍቷል ። ይህ ተባብሶ ወደ ሌላ ደረጃ እንዳይሸጋገር እያሰጋ ነው ። አሳሞህ እንዳሉት ተቃዋሚዎች ብሄራዊ ውይይት የጠሩበት ምክንያትም ይኽው ነው ።

«የጎሳ ጥያቄ አሁን የለም ማለት አከራካሪ ይመስለኛል ። እንደሚመስለኝ ከ2007 ዓምህረቱ የኬንያ ምርጫ በኋላ የተከተለው ብጥብጥ ያስነሳው ዋነኛው ምክንያት የጎሳ ጉዳይ ነበር ምክንያቱም ፀቡ ከፖለቲካው ወጥቶ ወደ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት እንዲሁም ወደ ጎሳ ግጭት ተቀይሯልና እነዚህ አሁንም እንዳሉ ነው ። ከዚህ በኩል ስንመለከተው አሁንም ቢሆን በገሃድ የሚታይ ውጥረት አለ ። ለዚህም ነው ኮርድ ብሄራዊ ውይይት እንዲካሄድ የጠየቀውl ፤ ቢያንስ አሉታዊ ሂደት በሚታይበት የጎሳዎች መቀናቀን እንዲሁም በፀጥታ ክፍተት በወጣት ስራ አጥነትና በኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ ነበር የጠየቀው ። ጉዳዩ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት ።»

የኬንያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች መንግሥትንም ሆነ ተቃዋሚዎችን በእሳት እየተጫወቱ ነው ሲሉ ይወወቅሷቸዋል ።የ2007 2008 ቱ ጎሳ ግጭት ጠባሳ ሙሉ በሙሉ ባልሻረባት በኬንያ ሁኔታዎች በጥንቃቄ ካልተያዙ ወደ ቀደመው ዓይነት ብጥብጥ ይሸጋገራል የሚል ስጋት አለ ። የጎሳ ጥያቄ አሁንም ያለ ቢሆንም እንደ 2007 ቱ ያህል አያሳስብም ይላሉ አሳሞዋ ።

« የጎሳ ጥያቄ እስካለ ድረስ ብጥብጥ የመነሳቱ እድል አሁንም ከፍተኛ ነው ። ሆኖም በተቋማት ደረ

ጃና በሌሎች ሁኔታዎች የተለወጡ ብዙ ነገሮች አሉ ። እነዚህ ችግሮቹን ለመቅረፍ የተወሰዱ አስታራቂ እርምጃዎች ናቸው ። የወደፊቱን ስንመለከት በ2007 ዓም የተከሰተው ዓይነት ላቅ ያለ ብጥብጥ ይነሳል ብለን አንጠብቅም ።»

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic