ተስፋ ያጫረው የወባ ክትባት | ጤና እና አካባቢ | DW | 12.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ተስፋ ያጫረው የወባ ክትባት

ባለፈው ሳምንት የዓለም የጤና ድርጅት ለወባ በሽታ መከላከያ ክትባት እውቅና ሰጥቷል። ክትባቱ ለሦስት አስርት ዓመታት ምርምርና ሙከራ ሲደረግበት የቆየ ሲሆን በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራትም መፈተኑ ተገልጿል። በሳይንሱ ምርምር አንድ ስኬት ነው የተባለለት ይኽ የወባ ክትባት በመቶ ሺህ የሚገመቱ ሕጻናት በየጊዜው ለሚያልቁባት አፍሪቃ ተስፋ ነው ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:40

«ባሉት የወባ መከላከያ ዘዴዎች ላይ ተጨማሪ አቅም ይሆናል»

«ይኽ እጅግ አክብሮት የሚገባው መልካም ዜና ነው፤ እናም ይኽ የተገኘው ለውጥ ወደፊት ይበልጥ የሚያራምደን ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ክትባቱን በማበልጸጉ ረገድ የካበተው እውቀት ከዚህ የተሻለ ውጤት የሚያመጣ ክትባት ለማዘጋጀት ለተመራማሪዎቹ ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብዬም አስባለሁ።» የአፍሪቃ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኤን ኔኬንጋሶንግ ፤ ለ30 ዓመታት በምርምር እና ሙከራ ላይ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በዓለም የጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠውን የወባ በሽታ መከላከያ ክትባትን አስመልክተው የተናገሩት ነው። ሦስት አራተኛው የግዛቷ ክፍል ለወባ ትንኝ መስፋፊያ አመቺ መሆኑ በሚነገርባት ኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለወባ በሽታ የተጋለጠ እንደሆነ መረሃዎች ያሳያሉ። ውጤታማ ክትባት ለወባ መገኘቱ በተለይ በየዓመቱ ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት ለሚሞቱባቸው ከሰሃራ በስተደቡብ ለሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ግኝቱ ትልቅ ዜና ነው።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የዓለም የጤና ድርጅት ከፍተኛ ስኬት መሆኑን ጠቅሶ እውቅና የሰጠው የወባ መከላከያ ክትባት ለ30 ዓመታት በምርምር እና ሙከራ ላይ የቆየ መሆኑ ነው የተሰማው። ክትባቱ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው የዛሬ ስድስት ዓመት ነበር። በተለይም ከጎርጎሪዮሳዊው 2019 ዓ,ም ጀምሮ በጋና፣ ኬንያ እና ማላዊ በስፋት የክትባቱ ሙከራ ሲከናወን ቆይቷል። በዚህ የሙከራ የወባ ክትባት መርሃግብር ሥር ከ800 ሺህ የሚበልጡ ሕጻናት ቢያንስ አንድ ጊዜ የተከተቡ ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በክትባቱ ምክንያት አስጊ ነገር አላጋጠመም። የክትባቱም ፍቱንነት በተመለከተ የወጣው መረጃ እንደሚለው ከተከተቡ 40 በመቶውን ከወባ በሽታ ሲከላከል፤ 30 በመቶ የሚሆኑ እና በጠና ታምመው የነበሩ ደግሞ እንዲያገግሙ ረድቷል። የዓለም የጤና ድርጅት ለክትባቱ እውቅና በሰጠበት ባለፈው ሳምንት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የብዙዎችን ሕይወት ለማትረፍ ያስችላል በሚል ክትባቱ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ድርጅቱ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።

Kenia | Impfung gegen Malaria

አዲሱ የወባ ክትባት

«ዛሬ የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም የመጀመሪያው የወባ ክትባት በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውል ወስኗል። ውሳኔውም በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ በመካሄድ ላይ ባሉት የሙከራ የክትባት መርሃግብሮች ውጤት ላይ መሠረት ያደረገ ነው። ክትባቱ ከ2019 ዓ,ም ጀምሮ ከ800 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት ተዳርሷል። ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ይኽ የወባ ክትባት ለሳይንስ፣ ለልጆች ጤና እና ወባን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ስኬት ነው። ይኽ ክትባት እስካሁን ካሉት የወባ መከላከያ ዘዴዎች ጋር ተዳምሮ በየዓመቱ በሺህ እና አስር ሺህዎች የሚገመቱ የወጣቶችን ሕይወት ሊያተርፍ ይችላል።»

ለወባ ክትባት ተገኘ ማለት ሌሎች ከዚህ ቀደም ወባን ለመከላከል ይደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ቀሩ ማለት አይደለም። ለወባ ትንኝ መራቢያ የሚሆኑ ውኃ የሚያቁሩ አካባቢዎች ማድረቁ፣ መድኃኒት የተነከሩ የመኝታ አጎበሮችን መጠቀሙም ሆነ የወባ ትንኝን ሊያጠፉ የሚችሉ መድኃኒቶችን ሳያሰልሱ መጠቀም ሊዘነጋ የማይገባው ተግባር ነው። ክትባቱ ለልጆች የታቀደ ሲሆን ከሁለት ዓመት በታች ላሉት ከሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል አቅም ከሚሰጡ ክትባቶች ጎን ለጎን እንዲሰጥ ነው የታቀደው። ለዚህም ኅብረተሰቡን ከማስተማር እና ከማስገንዘብ በተጨማሪ ለጤና ባለሙያዎችም ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ ነው የተገለጸው። በዓለም የጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠው የመጀመሪያው የወባ ክትባት ምዕራብ ኬንያ ውስጥ ትልቅ ውጤት እያስገኘ መሆኑ ነው የተሰማው። ኪሲሙ በሚባለው የሀኬንያ አውራጃ በሚገኝ ሃኪም ቤት የሚገኙት ነርስ ሳሎሚ ሲቱማ ክትባቱ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ይላሉ።

«አዎ ክትባቱ በጣም ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ቀደም ባሉት ዓመታት በዚህ ወቅት ከሀኪም ቤታችን አልጋዎች 70 በመቶው በወባ ታማሚዎች ይሞሉ ነበር። በተቃራኒው አሁን ከ16 አልጋ ሦስት ቢሆኑ ነው የወባ ታማሚዎች። ያ በመቶኛ ሲሰላ ደግሞ ደግሞ በጣም ዝቅተኛው ነው።»

Kenia Kind schäft unter Moskitonetz Malaria

በወባ የታመሙ የኬንያ ሕጻናት

የወባ ክትባቱ እውቅና ማግኘት እጅግ ካስደሰቷቸው ቀዳሚው የአፍሪቃ ሕብረት ነው። በተለይም ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉት የአፍሪቃ ሃገራት ወባ በየዓመቱ የሚያደርሰው የሰው ሕይወት ጥፋት በመላው ዓለም ከሚያደርሰው እጅግ የበዛ በመሆኑም የአፍሪቃ የበሽታዎች መከላከያ ኮሚሽን ክትባቱ በብዛትና በቶሎ እንዴት እንደሚገኝ ጥያቄውን አቅርቧል። የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኤን ንኬንጋሶንግ የክትባቱ መገኘት በየዓመቱ ከቲቢ እና ኤች አይቪ ጋር ተዳምሮ በሚሊየን የሚገመት የሰው ሕይወትን አፍሪቃ ውስጥ በሚቀጥፈው ወባ ላይ የሚደረገውን የመከላከል ዘመቻ ውጤታማ ያደርገዋል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

«ስለወባ ክትባት ስኬት የሰማነው ዜና በእርግጥም ጨዋታውን የሚለውጥ ርምጃ በመሆኑ ሊደነቅ ይገባል። እንደሚታወቀው ወባ አፍሪቃ ውስጥ ከፍተኛ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች አንዱ ነው። ወባ፤ ቲቢ እና ኤች አይቪ በጋራ ሆነው በየዓመቱ በሚሊየን የሚገመት ሕይወት እንደዋዛ ይቀጥፋሉ። ወባን ብቻ እንኳ ብንመለከት በአብዛኛው አፍሪቃ ውስጥ የሚሞቱት ለጋ ወጣቶች ናቸው። በልጆች ላይ የከፋ ህመምም ሆነ ሞት ለሚያስከትለው ወባ ውጤታማ ክትባት መገኘቱ ብዙዎችን ለማዳን ስለሚያስችል ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ከወባ ጋር እንደመኖራችንም እንደወሳኝ ስኬት ሊከበር ይገባዋል እላለሁ።»

Insektizid DDT gegen Malaria-Erreger versprüht

ወባን ለመከላከል የሚካሄደው የመድኃኒት ርጭት

ክትባቱ ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ነገር መሆኑን የገለጹልን በፌደራል ጤና ሚኒስትር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰሎሞን እስካሁን ባሉት ወባን የመከላከያ ዘዴዎች ተጨማሪ ይሆናል ባይ ናቸው።

ለወባ ክትባት መገኘቱ አዎንታዊ ዜና ቢሆንም ክትባቱን በብዛት አምርቶ በሽታው የከፋ ጉዳት ለሚያደርስባቸው ሆኖም በቂ የምርምር ዘርፍም ሆነ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው እንደ አፍሪቃ ላሉት አካባቢዎች በበቂ መጠን ማቅረብ ዋና ጥያቄ ነው። ክትባቱን ያዘጋጀው የእንግሊዙ የመድኃኒት ኩባንያ ግላስኮ ስሚዝ ክላይን ሙከራውን ለማካሄድ 10 ሚሊየን ክትባት አቅርቧል። ለመግዛት ለሚፈልግም ክትባቱን ባዘጋጀበት ወጪ ላይ አምስት በመቶ ብቻ ጨምሬ ለገበያ አቀርበዋለሁ እያለ ነው።  ለሰጡን ማብራሪያ በፌደራል ጤና ሚኒስትር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰሎሞንን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች