ተስፋ ያጡት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች | አፍሪቃ | DW | 28.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ተስፋ ያጡት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች

ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች፤ የገቡት የተኩስ አቁም ስምምነት ገቢራዊ መሆኑ አጠያያቂ እየሆነ ነዉ። የደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማፅያን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ሲሆን ፤ ጦርነቱን ፈርተዉ ወደ ጎረቤት ሃገራት የተሰደዱት የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች፤ በሃገራቸዉ ሰላም ይመጣል የሚል ተስፋ የላቸዉም።

አንድ ጦርነቱን ሸሽተዉ በቅርቡ ከነቤተሰቦቻቸዉ ዩጋንዳ በሚገኘዉ መጠለያ ጣብያ የገቡ አባት፤ ጦርነቱ ዳግም ተፋፍሞ እንዳይቀጥል እፈራለሁ ሲሉ ስጋታቸዉን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።
ደቡብ ሱዳናዊዉ የቤተሰብ አስተዳዳሪ አባት፤ የሃገራቸዉን የርስ በርስ ጦርነት በመሸሽ፤ ቤተሰቦቻቸዉን ይዘዉ ዩጋንዳ መጠለያ ጣብያ የገቡት በቅርቡ ነዉ። ለስድስት ሳምንታት የዘለቀዉ ጦርነት ቆሞና፤ ሰላም ሰፍኖ ወደ ሃገሬ በቅርቡ እመለሳለሁ የሚል ተስፋም የላቸዉም።
«የደቡብ ሱዳን መንግሥት አማጽያኑ ላይ ከባድ ዱላዉን እሰነዘረ ነዉ። በርግጥ ስልጣኑን ይዞ መቆየት ስለሚሻ በአዲስ ተደራጅቶ፤ እንደገና አማፅያኑ ላይ ጥቃት ለመጣል እየሞከረም ነዉ»

በርግጥም ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ባለፈዉ ሳምንት ሃሙስ ምሽት አዲስ አበባ ላይ የገቡት የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆኑን፤ ታዛቢዎች በጥርጣሪ ነበር ያዩት። በደቡብ ሱዳን መንግስት፤ በዓማጽያኑ መካከል ጦርነቱ መቀጠሉ የተሰማዉ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፊርማ ሳይደርቅ በማግስቱ አርብ ምሽት ላይ ነበር። በዚህም ምክንያት በርካታ ደቡብ ሱዳን ዜጎች የተኩስ አቁም ዉሉ ገቢራዊ መሆኑን በመጠራጠር ነፍሳቸዉን ለማዳን ሀገሪቱን በመልቀቅ በገፍ በመሰደድ ላይ ናቸዉ። በኡጋንዳ በሚገኘዉ መጠለያ ጣብያ ብቻ እስካሁን 47,000 የደቡብ ሱዳናዉያን ስደተኞች ይገኛሉ፤ ከነዚህ መካከል 38,000 የሰሜናዊ ዩጋንዳ አዋሳኝ ከሆነችዉ ከደቡባዊ ሱዳንዋ ፤አጁማኒ አካባቢ የፈለሱ ናቸዉ። በዚህም ኡጋንዳ የደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ከሆኑት ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ በበለጠ በርካታ የደቡብ ሱዳንን ስደተኞች ተቀብላለች። ይህ በገፍ ወደ ዩጋንዳ የሚፈልስ ስደተኛ ችግሩ ሊቀረፍለት የሚችለዉ፤ በመንግስት የእርዳታ ድርጅቶች ሽፋን ሳይሆን፤ በተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በ UNHCR ብቻ መሆኑ ነዉ የተመለከተዉ።
በደቡብ ሱዳን በሚገኝ መጠለያ ጣብያ ያሉ ስደተኞችም ቢሆኑ ስጋታቸዉ ተመሳሳይ ነዉ። እስከቅርብ ግዜ ጦርነት ይካሄድባት በነበረዉ በቦር ከተማ በሚገኘዉ የተመድ መጠለያ ጣብያ፤ 10,000 ስደተኞች ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት ጣብያዉ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ በስደተኞች በመጣበቡ እና አስፈላጊዉ ነገር ባለመሟላቱ 30 ህጻናት ሞተዋል። በዚህም ለሶስት ቀናት ጉብኝት ትናንት ሰኞ ደቡብ ሱዳን የገቡት የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሃፊ ቫለሪ አሞስ፤ በደቡብ ሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ገፈት ቀማሹ የሲቪሉ ማህበረሰብ ይበልጥ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ መፈለጋቸዉን ገልፀዋል። እንደ ምክትል ዋና ፀሃፊ ቫለሪ አሞስ በደቡስ ሱዳን ስደተኞች በተጠጉባት ዩጋንዳ በሚገኘዉ መጠለያ ጣብያም ወረርሽኝ ይነሳል የሚል ሥጋት አለ። ለ 400 ሰዎች ብቻ እንዲሆን ታቅዶ የነበረዉ፤ ከደቡብ ሱዳን ድንበር ትንሽ ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ የሚገኘዉ ዲዛፒ መጠለያ ጣብያ በደቡብ ሱዳን መንግሥት ወታደሮች እና በዓማፅያን መካከል ታህሳስ አጋማሽ ላይ ከተቀሰቀሰዉ የርስ በርስ ጦርነት በኃላ ፤ ራሳቸዉን ለማዳን በገቡ 20,000 ደቡብ ሱዳናዉያን ተጣብዎአል። በዚህ መጠለያ የሚገኙት ደቡብ ሱዳናዉያን የዩጋንዳ መንግስት በሃገሪቱ ለስደተኞች ወደ አቋቋመዉ ሶስት ቦታዎች መሄድ እንጂ፤ ወደ ደቡብ ሱዳን መመለስ አንድም ስደተኛ እንደማይፈልግ፤ አሞስ ገልፀዋል።


ታህሳስ አጋማሽ በደቡብ ሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ፤ በአማካኝ በቀን 1000 ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ፤ ድዛፒ መጠለያ እንደሚገቡ ተመልክቶአል። በደቡብ ሱዳን ና ዩጋንዳ ድንበር ላይ፤ በተመድ መኪና፤ ለስደተኞች ርዳታ የሚሰጡት በተመድ የዶቼ ቬለ የስደተኞች እርዳታ አቅራቢ ቃል አቀባይ ፤ ሉሲ ቤክ እንደገለፁት የደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ በኃላ ወደመጠለያዉ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር በጥቂቱም ቢሆን ቀንሶአል።
« ትናንት 197 የሚሆኑ ስደተኞች ብቻ ናቸዉ የደረሱት፤ ግን ነሱም ቢሆኑ እጅግ አድካሚ በሆነዉ የእግር ጉዞ በጣም ተጎሳቁለዋል»
በሚቀጥሉት ቀናቶችም እንዲሁ በርካታ ስደተኞች ወደ ዩጋንዳ መግባታቸዉ እንደማይቀር፤ ሉሲ ቤክ ሳይገልፁ አላለፉም። በሌላ በኩል «Ärzte ohne Grenzen» ድንበር አያግዴዉ የሃኪሞች ድርጅት ባልደረባ ፍሬድሪክ ዱሞንት፤ በገፍ ወደ መጠለያ ወደ ሚገባዉ የስደተኛ ቁጥር ላይ ስጋት እንደላቸዉ ይገልፃሉ።
«የርዳታ ድርጅቶች ለበርካታ ሰዎች ለመጀመርያ ግዜ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ነዉ የሚለግሱት። ግን ለስደተኛዉ ከሚደርሱት የመጀመርያ ርዳታ ቁሳቁሶች መካከል ደግሞ የመጠጥ ዉሃ፤ የመድሃኒት እና የምግብ እጥረቶች ጎልተዉ ይታያሉ። እኛን ስጋት ላይ የሚጥለን በአንድ ግዜ የሚመጣዉ ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ነዉ»
በዚህም ምክንያት የተመድ የስደተኞች መርጃ ቢሮ ለተጨማሪ ገንዘብና፤ ለርዳታ ሥራ አጋር የሚሆነዉን በመፈለግ ላይ ነዉ። በቅርቡ «ረሃብን ለመዋጋት» የተሰኘ፤የፈረንሳይ የርዳታ ድርጅት በኡጋንዳ በሚገኘዉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ ጣብያ የእርዳታ እጁን መዘርጋት መጀመሩ ተመልክቶአል።


አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ
Audios and videos on the topic