ተስፋ የተጣለባቸው አዲሶቹ የጤፍ እና ማሽላ ዝርያዎች | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 30.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ተስፋ የተጣለባቸው አዲሶቹ የጤፍ እና ማሽላ ዝርያዎች

የኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  የሀገሪቱን “የሰብል ልማት ታሪክ ሊቀይሩ” የሚችሉ ናቸው ያላቸው የጤፍ እና የማሽላ ዝርያዎች በምርምር መገኘታቸውን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። ዝርያዎቹ አንዴ ከተዘሩ በኋላ ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ከ10 እስከ 20 ዓመታት ምርት የሚሰጡ ናቸው ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:50

ዝርያዎቹ እስከ 20 ዓመት ያለማቋረጥ ምርት ይሰጣሉ ተብሏል

የኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የዛሬ ሁለት ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ነበር። ዶክተር ጌታሁን ወደዚያ የሄዱት የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ዘገባ ለማቅረብ ነበር። ለሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ናስር ካንሱ አንዱ ናቸው።

“ወደ ስራ የገቡ ወይም ሊገቡ የሚችሉ የምርምር ውጤቶች የፈጠራ ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣት አኳያ ትርጉም ያላቸውን [ለምን] በውጤት መለካት ለምን አልተቻለም?” ሲሉ ጠይቀዋል አቶ ናስር።

ለዚህ ጥያቄ በአሃዝ የተደገፈ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ በአጠቃላይ ሲታይ መስሪያ ቤታቸው የሚደግፋቸው የምርምር ፕሮጀክቶች አካሄድ ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል። ዶክተር ጌታሁን በምሳሌነት ለምክር ቤት አባላት ያነሱት አንድ የምርምር ውጤት ይበልጥ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። አንድ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ አንዴ ከተዘሩ በኋላ ከ10 እስከ 20 ዓመታት በተከታታይ ምርት መስጠት የሚችሉ የጤፍና የማሽላ ዝርያዎችን ማግኘታቸውን ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት ነግረዋቸዋል። የምርምር ውጤቱንም “የኢትዮጵያን የሰብል ምርት ታሪክ ሊቀየር የሚችል ነው” ሲሉ አሞካሽተውታል።

በሚኒስትሩ ሞገስ ያገኙት እኚህ ተመራማሪ አቶ ታለጌታ ልዑል ይባላሉ። ምርምራቸውን የሚያካሄዱት በግላቸው ነው። አቶ ታለጌታ በግብርና ምርቶች ላይ ላለፉት 30 ዓመታት ምርምር ማድረጋቸውን ይናገራሉ። የጤፍ እና የማሽላ ዝርያዎች አንዴ ከተዘሩ በኋላ ለተከታታይ ዓመታት ምርት ይሰጣሉ ሲባል እንዴት ነው? አቶ ታለጌታ ያስረዳሉ።

“እነዚህ የተለመዱት ዘሮችን ስንዘራቸው ወቅታቸው ወይም ዓመታዊ [ዑደታቸው] ሲያበቃ ያው ይደርቃሉ ማለት ነው።  ደግመው ህይወት መስጠት አይችሉም። እነዚህኞቹ ዝርያዎች ግን አንዴ ከተዘሩ በኋላ ሲታጨዱ ያው ውሃ በሚያገኙበት ጊዜ ራሳቸውን የማባዛት እና ወይም ደግሞ እንደገና አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛ፣ ስድሰተኛ ትውልድ እያሉ ይሄዱና በየ20 ዓመት የምታገኘውን ምርት ይሰጡሃል። ለምሳሌ አንድ የማሽላ ዘር አንድ ሆኖ መብቀል ሲችል ወይም ደግሞ ratton የሚባለው ቢበቅልም ምርት ሳይሰጥ ዋናው ሲሞት አብሮ ይሞታል ማለት ነው። እነዚህኛዎቹ ግን ዋናው ሲሞት ራሱ ዘሩን ከውስጡ አውጥቶ ሌሎችን ትውልዶች እየተካ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ [ናቸው]። 

እንዲያውም ሲመቻቸው፣ አመቺ ቦታ ላይ ከሆኑ፣ የሚፈልጉትን አየር፣ ውሃ እና የአየር ጸባይ ውስጥ  የበቀሉ ከሆነ እና ሰውም፣ እኛ እንክብካቤ ካደረግንላቸው አንዷ ፍሬ እስከ 80፣ 90፣ 100 ልታወጣ እንደምትችል በሙከራ አረጋግጠናል። ለምሳሌ አንድ ጤፍ ወይም አንድ ማሽላ ጥሬውን ዘራህ እንበል። አንዷን፣ ነጠላውን ዘራኸው ግን ያ ማለት በሚቀጥለው ላይ ሲበቅሉ አስር ሊሆን ይችላል፤ ሃያም ሊሆን ይችላል፤ ሰላሳም ይዞ ሊወጣ ይችላል። በሚቀጥለው ትውልድ ላይ ደግሞ 50፣ 60፣ 70 እንደሁኔታዎቹ  ሊይዝ ይችላል ማለት ነው። ይህ ማለት እንግዲህ እነዚህኝን ሰብሎች አንድ ገበሬ ሲጠቀም የሚሰጠው ምርት በዚያው ብዜት ልክ አባዝተህ የምታገኘውን ነው ማለት ነው” ይላሉ ተመራማሪው።  

አቶ ታለጌታ በምርምር አገኛኋቸው የሚሏቸው ዝርያዎች አንዴ ተዘርተው ከበቀሉ በኋላ መሬቱን ዳግም ማረስም ሆነ ሌላ ዘር መዝራት ሳያስፈልግ ምርት መስጠታቸውን የሚቀጥሉ እንደሆኑ ይናገራሉ። በየትኛው ሳይንሳዊ ዘዴ ተጠቅመው ለዚህ የምርምር ውጤት እንደበቁ ይናገራሉ።

Bildergalerie UN Jahr der Aussöhnung Uganda Flash.Galerie Bild 6

“በዚህ ሙከራ ውስጥ ባደረግነው የረጅም ጊዜ ጥረት በስተኋላ ሆኖ የተገኘው ሰብሎቹን አንዴ ከዘራናቸው በኋላ ሳያደግም፣ ምንም ዓይነት ዘር ሳያስፈልጋቸው ratton የተባለውን ዘረ-መል (gene) በመጠቀም ወደዘርነት በመቀየር ምርታማ የሚሆኑበት ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው። ስለዚህ ያ ማለት ዘር ሳያስፈልገው ከዘር በኋላ ዘር ሳያስፈልገው ራሱ በውስጡ ስውር ወይም negative የሆነ ዘር ስላለ እኛ rebiology science ንድፈ ሀሳብን ተግባራዊ በማድረግ eternal biology lifeን ወደ ምድር ለማምጣት ነው ዋነኛው ዓላማችን” ሲሉ ያስረዳሉ። 

ዶ/ር አስናቀ ፍቅሬ ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት በተመራማሪነት ሰርተዋል። አሁን በዓለም አቀፍ የደረቃማ አካባቢ ምርምር ተቋም ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛሉ። አቶ ታለጌታ እያካሄዱ ያሉትን ምርምር “ውሱን በሆነ ደረጃም” ቢሆን እንደሚያውቁት ይናገራሉ። ተመራማሪው እየተገበሩት ስላለው ሳይንሳዊ ዘዴ ማብራሪያ አላቸው። 

“አሁን ይሄ ትውልዱን የአንዱን አንዱ ከተዘራ በኋላ የራሱን ትውልድ በአንድ ቦታ ላይ ሆኖ ማቆየት ዘዴ በሌላም አለም ላይ የተወሰነ ጅምር ስር አውቃለሁ። እነታለጌታም የሞከሩት የዚህ አይነቱን ነው። ሀሳቡ ሳይንሱ፤ አዲስ ነው። የ rebiology ዓይነት የሚል ነገር ነው እነ ጋሽ ታለጌታ ያሰቡት። በአንድ ዘር ትውልዱን በአንድ ቦታ ላይ እያደሱ፣ እያደሱ [መሄድ ነው]። ልክ እንደዛፍ ቁጥቋጦ ማለት ነው። በቀላል አማርኛ ዛፍ ስትቆጠቁጠው እንደገና ክንፍ ያዋጣል፤ አሁንም ስትቆጠቆጠው እንደገና ያዋጣል። አንድ መነሻ ዘር ይዞ ማለት ነውና  ያንን ሀሳብ ለማራመድ ነው። 

ምናልባት ማሽላ ካወቅህ ይሄ አዲስ ነገር አይደለም። [ማሽላን] ዕድል ከሰጠኸው ቢያንስ አንድ ጊዜ መልሶ ይሰጣል። የመጀመሪያው ካረጀ፣ ዘር ከሰጠ በኋላ ከስር የሚያቆጠቁጡ ይመጣሉ። Ratton ይባላል በእንግሊዘኛ። እርሱን ማራዘም ነው እያደረጉት ያሉት። ያንን ratton ዘር ሰጥቲቶ እንደገና ሌላ ratton፣ ያም ዘር ሰጥቶ እንደገና ሌላ ratton እያደረጉ በአንድ መነሻ ዘር ላይ ትውልድን መደጋገም እንደማለት ነው። ያንን ነገር ለማድረግ የተወሰነ የሚከተሏቸው treatment አሏቸው። ሀሳቡ ይሄ ነው። የማሽላ ገበሬዎች ያውቃሉ ልክ ዘር ከሰጠ በኋላ ዋናው ግንድ ስትቆርጠው ወይም ሲቆረጥ በዚያው መነሻ ዘር ላይ ከስር ይመጣል ወይም ይበቅላል” ሲሉ በኢትዮጵያ ገበሬዎች ዘንድ ያለውን ሀገር በቀል ዕውቀት በደጋፊ ማስረጃነት ያነሳሉ። 

24112006 PZ TEFF.jpg

ዶ/ር አስናቀ በተመራማሪው እጅ አለ የሚሉትን መረጃ ተንተርሰው የምርምሩ ውጤት አንድ የማሽላ ዘር እስከ ሶስት ወይም አራት ትውልድ ድረስ ማሻገር መቻሉን ይናገራሉ። ምርምሩ በጤፍ ረገድ ያስመዘገበው ውጤት ውሱኑነት ይታይበታል ባይ ናቸው። ለ10 ወይም ለ20 ዓመታት ተከታታይ ምርት ማግኘት ይቻላል በሚል የወጣው መረጃም “ትንሽ መታየት እና ማጣራት የሚፈልግ ይመስለኛል” ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።  

“ይሄ ነገር ያለቀለት ሳይንስ አይደለም የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበትም አይደለም። በሙከራ ደረጃ ላይ ያለ ነው። ምናልባት ንሻጤ የፈጠረ ይመስለኛል። እንደ ሀሳብ፣ እንደ ጽንሰ ሀሳብ እዚያ ላይ መነሻ ተደርጎ ይመስለኛል መረጃዎች እየወጡ ያሉ የሚመስሉኝ እና እንደ ሳይንስ እንደምርምር እኔ የሚታየኝ ያለቀለት የተጠናቀቀ ስራ ስላልሆነ እንደ recommendation የምታውቀው ነገር የለም። ግን በሂደቱ ሽልማትም ለማግኘት፣ ፈንድም ለማግኘትም እንደ መነሻ ሀሳብ ተጠቅመውበት ስለሆነ ምናልባት እኔ ሳይንስና ቴክኖሎጂም ሀሳቡን እንደትኩረት ነጥብ ያየው ይመስለኛል። ግን አሁንም ጥናቱ ያለቀለት ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም” ሲሉ ምርምሩ ገና በሙከራ ደረጃ ስለመሆኑ አጽንኦት ይሰጣሉ።  

ዶ/ር አስናቀ ሽልማት ሲሉ የጠቀሱት ለአቶ ታለጌታ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያበረከተላቸውን የወርቅ ሚዳሊያ እና ዋንጫን ነው። መስሪያ ቤቱ ለተመራማሪው ሽልማቱን የሰጠው በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ውድድር አንዱ ተሸላሚ አድርጎ ከመረጣቸው በኋላ ነበር። ከሚኒስቴሩ ዕውቅና ለማግኘት ብዙ እንደለፉ የሚናገሩት አቶ ታለጌታ የምርምር ውጤታቸውን በተደጋጋሚ ለመስሪያ ቤቱ ሲያስገቡ ውድቅ ይደረግባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።  

በሙያቸው የጥርስ ሀኪም የሆኑት ተመራማሪው በጤፍ፣ በማሽላ እና እንደ ባቄላ ባሉ ጥራጥሬዎች ላይ ምርምር ሲያካሂዱ የቆዩት በንባብ ባገኙት ዕውቀት እንደሆነ ይናገራሉ። በአጫጭር ስልጠናዎች እና የሌሎች ተመራማሪዎችን አሰራር በመመልከት ዕውቀታቸውን ሲያጎለብቱ መቆየታቸውንም ያስረዳሉ። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መሃል ሜዳ አካባቢ በምትገኝ አነስተኛ መንደር የተወለዱት አቶ ታለጌታ የቤተሰባቸው ሁኔታ እና እድገታቸው ወደዚህ ምርምር እንዲያዘነብሉ ምክንያት እንደሆናቸው ይገልጻሉ።

Bauer bei der Arbeit in Äthiopien

“በግብርና ህይወት ከሚኖሩ ደሃ ቤተሰብ ነው እና የተገኘሁት እና ያው በግብርና ህይወት ላይ አብሬ ኖሬያለሁ። ያው ስለግብርናው መቼም በተግባር ምናልባት እዚህ ጥናቱ ላይ በደንብ የታገዘ ባይሆንም በልምድ በግብርና ህይወት ላይ ብዙ ቆይቻለሁ። ያ ቤተሰቦቻችን እንግዲ ለፍተው ገበሬው በጣም ይጥራል፣ ይደክማል ግን የድካሙን ሳያገኝ በረሃብ መሞት፣ መቸገር ከዚያም አገር ጥሊሎ መሄድ፣ መሰደድ እነዚህ ሁሉ ይቆጩኝ ነበር እና እኔስ ምንድነው ለቤተሰቦቼ፣ ለኢትዮጵያ ገበሬ ህይወት ተቀይሮ መቼ ነው የማየው የሚለው በቃ ቀንም፣ ማታም፣ ለሊትም የሚያስጨንቅ ህልም ነበረኝ” ይላሉ አቶ ታለጌታ ቁጭት ባዘለ ድምጽ።

የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየር ያለሙት አቶ ታለጌታ ለምርምራቸው የገበሬውን ዕውቀት እና አገር በቀል ዘር በግብዓትነት ተጠቅመዋል። ምርምር ሲያደርጉባቸው ከቆዮባቸው የማሽላ ዝርያዎች በስድስቱ አጥጋቢ ውጤት አግኝቼያለሁ ይላሉ። ከዝርያዎቹ ውስጥ ቢጫማ፣ ነጭ፣ ጥቁሬ እና የዘንጋዳ ዝርያዎችን በስም ጠቅሰዋል። በጤፍ በኩል ነጭ፣ ቀይ፣ ጤፍ አጋይ እና ዝንጀሬ የሚባሉት አገር በቀል ዝርያዎች በተመሳሳይ ምርታማ መሆናቸው በሙከራ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል። እንዲህ በምርምር ያገኟቸውን ዝርያዎች አርሶ አደሩ እጅ መቼ ለማድረስ አስበው ይሆን? ምላሽ አላቸው።

“አሁን ዘሩ የታሰበው እንግዲህ ምንድነው እኛ ጋር ያለው ዘር ማሽላ እንደምታውቀው ይነቅዛል ያሉን ትንሽ በርከት ያሉ ነበሩ። አሁን ግን የተወሰኑ ተበላሽቷል ግን የተወሰነ አለን። ምርጥ በጥራት ዝርያዎች አሉንና እነኚህን አሁን ምናልባት መጠናቸው አነስ ከማለት ውጭ ግን ለተወነ ገበሬ ለመሞከሪያ፣ ለማየት ማከፋፈል ይቻላል።  ግን ሰፋ አድርጎ እንደው ለበርካታ ገበሬ በተለያዩ ቦታዎች ለማድረስ ግን እንግዲህ የማስፋቱ ነገር፣ እንደገና ዝርያዎችን የማባዛት ስራ ይጠይቃል ማለት ነው” ሲሉ ዘሩ መሰራት ስላለባቸው ነገሮች ተመራማሪው ያስረዳሉ።  

ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች