ተስፋ ቢሱ የደቡብ ሱዳን ድርድር | አፍሪቃ | DW | 12.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ተስፋ ቢሱ የደቡብ ሱዳን ድርድር

ከአዲስ አበባ እስከ ታንዛኒያዋ አሩሻ ከተማ በዘለቀው የደቡብ ሱዳን የአንድ ዓመት የድርድር ሂደት የተኩስ አቁም ለማድረግ እና የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተደረጉ ስምምነቶች ተግባራዊ መሆን አልቻሉም። በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለ ስልጣን- ኢጋድ የሚመራው ድርድር በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደገና ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ለአምስት አስርት ዓመታት ነጻነት ፍለጋ የታገሉት የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ (Sudan People's Liberation Movement) ታጋዮች ሰላም ከራቃቸው ከአንድ ዓመት በላይ አለፈ። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና የቀድሞው ምክትላቸው እና የዛሬ ተቃዋሚያቸው ሪክ ማቻር መነጋገር እና ልዩነትነቶቻቸውን መፍታት ተስኗቸዋል። በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ «የሁለቱ ወገኖች ልዩነት እጅግ እየሰፋ የመጣባቸው ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሽግግር መንግስቱ ጉዳይ ነው። የሽግግር መንግስቱ ጉዳይ በፕሬዝዳንት እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ባለፈው ነሃሴ በተደረገው ስምምነት የተደረሰ የጋራ ስምምነት ነበር። አሁን አሁን የሚታዩት ነገሮች የሚያመለክቱት ሁለቱም ወገኖች ከዚህ ድርድር እያፈገፈጉ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በዋንኛነት መንግስቱ ቀጥሎ ደግሞ የተቃዋሚው ወገን የየራሳቸው የሆነ መግለጫ አውጥተዋል። ከድርድር ጽንሰ-ሃሳቡ ያፈነገጠ ነው። በአሁኑ ድርድር በቅርብ ጊዜ እየሰፋ ያለውን ልዩነት አጥብበው ወደ ስምምነት ይመጣሎ በትክክል የሚገምት ሰው ያለ አይመስለኝም። » ሲሉ ልዩነቱ እየሰፋ መምጣቱን ያስረዳሉ።


የሁለቱ ወገኖች ልዩነት መስፋት ችግር የፈጠረው ድርድሩን ለሚመራው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን- ኢጋድ ጭምር ነው። ኢጋድ የሚመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሲጀመር በሃገሪቱ ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ማበጀት ይልቅ በልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ላይ እንደሚያተኩር አቶ አቤል አባተ ይናገራሉ።
«የኢጋድም አደራዳሪዎች በእርግጠኝነት ይህን መናገር የሚችሉ አይመስለኝም።ቢያንስ አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ድርድር የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖችን በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ልዩነት የማጥበብ ተስፋ አለ።»


ከስልሳ በላይ ጎሳዎች ያሏት ደቡብ ሱዳን እምብዛም ራሷን የማስተዳደር ልምድ የላትም። በአሁኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር መካከል ያለው ልዩነት የዲንካና ኑዌር ጎሳዎችንም አቃቅሯል።በነዳጅ ዘይት ንግድ ላይ የተንጠለጠለው የሃገሪቱ ኢኮኖሚም በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቱ ተሰምቷል። በዝናባማው ወቅት ጋብ ያለው የርስ በርስ ግጭት ከወቅቱ መለወጥ ጋር ዳግም እንዳያገረሽ አሁን የተጀመረው የድርድር ሂደት ፍሬ ማፍራት ይጠበቅበት ነበር። የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ አቤል አባተ የድርድር ሂደቱ በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን- ኢጋድ አደራዳሪዎች ቀጣይ እርምጃ ቢሆን በግልጽ አይታወቅም።


«ሁለቱ ወገኖች የማይስማሙ ከሆነ ለሚመለከታቸው አካላት በዋንኛነት ለኢጋድ ቀጥሎ ለአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማዞር አዝማሚያ አለ። ብለው ብዙ ሚዲያዎች ይዘግባሉ። ብዙ ሰዎች የሚጠብቁት ስምምነት ላይ ይደረሳል አይደረስም የሚለውን ሳይሆን የኢጋድ አደራዳሪዎች ያላቸውን ችግር ለአፍሪካ ሕብረት እና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳውቀው ከሰላም ስምምነቱ ገሸሽ በሚሉ አካላት ላይ አስፈላጊ ቅጣት ሊያስጥሉባቸው ይችላሉ ወይስ በዚህ በድርድር ሁለቱ ወገኖች ተስማምተው ወደፊት መቀጠል ይችላሉ የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው።ስለዚህ የዚህ የሰላም ስምምነት በአሁን ሰዓት ብዙ ተስፋ የሚያጭሩ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚካሄድ ነው»


በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለህልፈተ-ህይወት ሲዳረጉ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በሀገሪቱ የሚሰሩ የእርዳታ ድርጅቶች ዛሬ የተሰደዱት ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ማምረት ካልጀመሩ ርሃብ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።


እሸቴ በቀለ
ተክሌ የኃላ

Audios and videos on the topic