ተስፋና ጭንቀት፤ ሊቢያ በምርጫ ዋዜማ | አፍሪቃ | DW | 09.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ተስፋና ጭንቀት፤ ሊቢያ በምርጫ ዋዜማ

ከአርባ ዓመታት በላይ ከዘለቀ የአምባገነን አስተዳደር በኋላ ሊቢያውያን እሁድ ዕለት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አከናውነዋል። ውጤቱን ሊቢያውያን በጉጉት እየጠበቁት እንደሆነም ተዘግቧል።

ቤንጋዚ፣ የምርጫው ሂደት ሲጠናቀቅ

ቤንጋዚ፣ የምርጫው ሂደት ሲጠናቀቅ

ሊቢያውያን ታሪካዊና ዲሚክራሲያዊ የተባለለትን ምርጫ እሁድ፣ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ማካሄዳቸው ተሰምቷል። አርባ ዓመታት ግድም በአምባገነን መንግስት የማቀቁት ሊቢያውያን የትናንቱን ፌሽታ ለመቋደስ በርካታ መስዋዕትነትን መክፈል ግድ ብሏቸው ነበር። መስዋዕትነቱ የሺዎችን ህይወት ግብር ጠይቆ፤ የበላውን በልቶ ያደማውን አድምቶ አልፏል። ታዲያ የሊቢያውያን አብዮት ከጠየቀው የህይወት ግብር የተረፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ትናንት በደስታ ከአደባባይ ወጥተው መፈንጠዛቸው ተሰምቷል። የህክምና ተማሪው ወጣት ሜፍታህ ላህዌል ግን ከጎዳናው ይልቅ በአንድ ሻይ ቤት ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር መምከርን ነው የመረጠው።

ምርጫ እና ፌሽታ በሊቢያ

ምርጫ እና ፌሽታ በሊቢያ«ምርጫው በረዥሙ ጎዳና የመጀመሪያው ርምጃ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። የሂደቱ መጨረሻ ግን አይደለም። እስካሁን ምርጫውን ማካሄድ ነው የተሳካልን። ገና ብዙ ስራ ይጠብቀናል»

ሆኖም ወጣቱ የህክምና ተማሪ በሊቢያ ዲሞክራሲ መሰረት እንደሚይዝ ተስፋ ቢኖረውም ሂደቱ ግን ገና ብዙ ፈተና እንደሚጠብቀው ይሰማዋል። መላ ትሪፖሊ ትናንት በባንዲራ ደምቃ ነበር የዋለችው። ነዋሪው የአብዮቱን መዝሙር እየዘመረ በሲቃ ሲጨፍር አምሽቷል። የአውሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንደነበር ጠቅሷል። የታዛቢ ቡድኑ አባል እና የአውሮጳ ኅብረት እንደራሴው አሌክሳንደር ግራፍ ላምብስዶርፍ የምርጫ ሂደቱን «ታሪካዊ ርምጃ» ሲሉ አወድሰውታል። ወጣት ዋሴፍ
ሳሌም አልብድራይን እንደህክምና ተማሪ ጓደኛው የሊቢያ የወደፊት ዕጣ የተሻለ እንዲሆን ይመኛል።

ምርጫ በሊቢያ

ምርጫ በሊቢያ«ነገሩ በጣም ነው ያጓጓኝ። የሆነ ጥሩ ነገር እንደሚያደርጉ ተስፋ አለኝ። ህገ-መንግስታችን ዲሞክራሲያዊ ይሆን ይሆናል። ጠንካራ ዲሚክራሲያዊት ሀገርም መመስረት እንችላለን። ወይንም ደግሞ ፈፅሞ የተለየ ነገርም ሊከሰት ይችላል። ልክ እንደ ሌሎቹ አረብ ሀገራት ሁሉ ባህላዊ ህገ-መንግስት ያረቁ ይሆናል፤ ያኔ የሆነው ነገር ሁሉ ዋጋ አጣ ማለት ነው። »

የህክምና ተማሪው ሜፍታህም ሆነ ጓደኛው ሳሌም የግብፅን እና የቱኒዚያን የአብዮት ማግስት ካጤኑ በኋላ የሊቢያም ተመሳሳይ እንዳይሆን ሳይሰጉ አልቀሩም። ወጣቶቹ የሀይማኖት እና የጎሳ ጉዳይ በሊቢያ የወደፊት ዕጣ ላይ ታላቅ ስጋት እንደደቀነ ይሰማቸዋል። ታዲያ ህልማቸው ሁሉ የቀን ቅዠት ሆኖ እንዳይቀር በሠብዓዊ መብቶች ጉዳይ እና ዲሞክራሲ በተመለከተ ብዙ መስራት እንዳለባቸው ይገልፃሉ። ሊቢያ ከአራት አስርት ዓመት በኋላ ከአምባ ገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ጎዳና እያቀናች ነው። ለወጣቶቹ ግን የትናንቱ ምርጫ የአብዮቱ ስኬት ገና መንደርደሪያው መሆኑ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic