ተስፋና ስጋት የታከለበት የኦዴግና ኢሕአዴግ ዉይይት  | ኢትዮጵያ | DW | 14.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ተስፋና ስጋት የታከለበት የኦዴግና ኢሕአዴግ ዉይይት 

የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል፤ ብሎም በኢትዮጵያ  ዉስጥ ያለዉን የፖለቲካ ስርዓት ዴሞክራስያዊ ለማድረግ በአገር ዉስጥ እና በባህር ማዶ ካሉ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ከሦስት ወር በፊት መግለፁ ይታወሳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:29

የኦዴግና ኢሕአዴግ ዉይይት 

ይሄንንም ጥሪ በፍጥነት «በሙሉ ልቡ» የተቀበለዉ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን ዴሞክራስያዊ ለማድረግና ለማጠናከር ዝግጅትና ፍቃደኝነቱን በግዜዉ ባወጣዉ መግለጫ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይም የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦዴግ ተወካዮች ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ ዉይይት ማድረጋቸዉን፤ እንዲሁም ኦዴግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የሰላማዊ ትግል ለማድረግ መስማማታቸዉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ለመድረስ ወደ አምስት ዓመታት ገደማ ሙከራ እንዳደረጉ የሚናገሩት የግንባሩ ቃልአቀባይ ዶክተር በያን አሶባ ፓርቲያቸዉ መንግሥት የሚያደርገዉ ማሻሻያዎች አካል መሆን እንደሚፈልግም ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል።

ዉጭ አገር ያሉ የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዉስጥ ተሳትፈው የሚፈልጉትን ለዉጥ ማምጣት ስላልቻሉ አሁን መንግሥትና ኦዴግ የጀመሩት ዉይይት ጥሩ ጅማሮ መሆኑን በምሥራቅ አፍሪቃ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ መገርሳ ሌንጂሶ ይናገራሉ።

ኢሕአዴግ ከሌሎች ተቃዋም ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገዉ ድርድር ገለልተኛነት ይጎለዋል በማለት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ራሳቸዉን ማግለላቸዉ ይታዋሳል። አዲሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ከያዙ ወዲህ እነዚህን ፓርቲዎች ወደ ድርድሩ ለመመለስ በይፋ የተደረገ ሙከራ አልታየም። ከዚህ በመነሳትም መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የገጠማቸዉን ዓይነት ዕድል ኦዴግ እንዳያግጥመዉ የሚሰጉ አሉ።

ስጋቱን በተመለከተ «ያን ድልድይ ስንደርስበት እናቋርጣለን» የሚሉት የኦዴግ ቃልአቀባይ ዶክተር በያን አሶባ አገሪቱ አሁን ተስፋ እንደሚታይባት ገልፀዋል።

የኦዴግና የኢትዮጵያ መንግስት ቀጣዩ ዉይይት የሚካሄድበትን ቁርጥ ያለ ቀን መናገር ቃልአቀባዩ ዶክተር በያን ባይፈልጉም ከሁለት ሳምንት ባነሰ ግዜ ዉስጥ አዲስ አበባ ላይ ለማስቀጠል ከስምምነት መድረሳቸዉን ግን ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። የዉይይቱ ዋና አጀንዳም ድርጅታቸዉ ወደ አገር ቤት ተመልሶ፣ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ፣ በሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዉስጥ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነም ቃለቀባዩ አክለው ጠቁመዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ

ነጋሽ መሓመድ 

Audios and videos on the topic