ተሰፋ እያጣ የመጣዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር | ኢትዮጵያ | DW | 04.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ተሰፋ እያጣ የመጣዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር

በኢህአዴግና በ 21 ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ይደረጋል የተባለዉ «ድርድር» ከተጀመረ ሁለት ወር ሊያስቆጥር ጥቂት ቀናቶች ይቀሩለታል። በዚህ ጊዜ ዉስጥ ሰባት የዉይይት መድረኮች የተዘጋጁ ሲሆን «መድረክ» ፓርቲ ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ ዉይይት ብቻ እንደሚፈልግ አቋሙን በመግለጽ ራሱን ከድርድር አግልሏል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:17

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር

በስድስተኛ ዙር ላይ ከ21 ፓርቲዎች 20ዎቹ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ እንደሚያስፈልግ ቢስማሙም ኢህአዴግ ግን ድርድሩ «በዙር» ይሁን የሚል ሃሳብን አቅርቦ እንደነበር ተዘግቦአል።  ይሁን እንጅ ባለፈዉ ረቡዕ በተደረገዉ ሰባተኛ ዙር ዉይይት «ኢህአዴግ አደራዳሪ የሚባል ነገርን አይሞክርም» የሚል አቋምን ይዞ እንደነበር በስብሰባዉ ላይ የተሳተፉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ለዶይቼ ቬሌ ተናግዋል።

ሰማያዊ ፓርቲም «ድርድር ያለ አደራዳሪ ዉጤት አያመጣም» በሚል መለያየታቸዉንም አቶ የሽዋስ ተናግረዋል።

ኢህአዴግ «ገለልተኛ አደራደር» አያስፈልግም ብሎ አቋም ስይዝ «ገለልተኛ የሚባል ወገን የለም፤ ወይ ኢህአዴግን ወይ ተቃዋሚን የሚደግፍ ብቻ እንጂ" የሚል ማብራርያ መስጠቱን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ኢህአዴግ አቋሙን ይለዉጣል የሚል ብዙም እምነት እንደሌላቸዉ የሰማያዊ ፖርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል።

ሰማያዊ ፓርትን ጨምሮ አምስት የፖለቲካ ፓርትዎች "ድርድር ያለ አደራዳሪ አይሆንም" የሚል ተመሳሳይ አቋም መያዛቸዉም አቶ የሸዋስ ተናግረዋል። ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በሚካሄደዉ ቀጣዩ ዉይይት ዙር ላይም ፓርቲዎቹ በድርድር መሳተፍ ወይም አለመሳተፍቸዉን ይገልፃሉ ተብሎም ይጠበቃል። በኢህአዴግ በኩል የበለጠ ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነዉ ሙከራ ለዛሬ አልተሳካም። 

መርጋ ዮናስ 
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic