ተማሪዎች ለአየር ንብረት ተግባር ጠየቁ | ጤና እና አካባቢ | DW | 19.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ተማሪዎች ለአየር ንብረት ተግባር ጠየቁ

በጎርጎሪዮሳዊው 1992 የዓለም መንግሥታት የቀረበላቸውን ሳይንሳዊ ትንታኔ ተመርኩዘው ሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ እንደሚገባቸው ተስማሙ። ያግባባቸው ሳይንሳዊው ትንታኔ ለአየር ንብረት ለውጡ መሠረታዊ ምክንያቶች፤ የዓለም የሙቀት መጠን መጨመሩ፤ ይህ ሊሆን የቻለውም ወደ ከባቢ አየር ከመጠን በላይ የሚለቀቀው የCO2 ክምችት ነው የሚለው ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

ከ100 በላይ ሃገራት ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል

በዚሁ መሠረትም በጎርጎሪዮሳዊው 1997 ዓ,ም በታኅሣስ ወር በጃፓንዋ የኪዮቶ ከተማ ሙቀት አማቂ ጋዞችን የመቀነስ ውሉ 192 ሃገራት ፈረሙ። ስምምነቱ እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓ,ም  ቆይቶ የጊዜ ገደቡ ሊያበቃ ሲቃረብ ድጋሚ ውይይቱ ቀጥሎ ለቀጣይ ዓመታት ተራዘመ። የውሉ ዋና ዓላማ ሙቀት አማቂ ጋዞች መቀነስ እንደመሆኑ በተለይም በኢንዱስትሪው ያደጉት ሃገራት ከባቢ አየርን በመበከል በታሪካዊ ኃላፊነታቸው ምክንያት ከእነሱ ብዙ ቢጠበቅም ዛሬም ከ50 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ የኃይል ምንጫቸውን ድንጋይ ከሰል ላይ ያደረጉት እነዚሁ ሃገራት መሆናቸው የሚቀርብባቸውን ትችት አልበረደም።

መንግሥታት በየጊዜ እየተሰባሰቡ የዓለም ሙቀት መጨመር አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በማውሳት በየግላቸው ሊወስዱት ስለሚገባው ርምጃ መነጋገር መግባባታቸው ቢነገርም ከንግግር የዘለለ ተግባር አለመታየቱን ብዙዎች እያነሱ ይተቻሉ። ባለፈው ሳምንት ናይሮቢ ኬንያ ላይ በተካሄደው መሰል ስብሰባ ላይም የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ከተቺዎቹ ጎራ ገብተው እንዲህ ብለዋል።

«ፈረንሳይ በዚህ ዓመት የቡድን ሰባት ሊቀመንበር ናት። ቡድን ሰባት ከእንግዲህ የአየር ንብረትን በተመለከተ በጋራ ሰነድ ላይ መግባባት የሚያቅተው መድረክ መሆን እንደሌለበት አስባለሁ፤ ከእንግዲህ ይህ ሊገባው የሚችል አይኖርም። ቡድን ሰባት ስለየአየር ንብረት የሚያስብ መሆን አለበት። የአባል ሃገራትን ሉአላዊ ምርጫ አከብራለሁ፤ ነገር ግን የመጨረሻ መግለጫ የሚባል ነገር አይኖርም፤ በቀላሉ ማንም አያነብባቸውም። ከዚህ ይልቅ ተጨባች ንቅናቄ እና የመጨረሻ ውጤታማ ርምጃዎች መወሰድ አለባቸው።»

የዓለም መሪዎች ዛሬም በዚሁ ጉዳይ ላይ በንግግር መጠመዳቸው የነገውን ዓለም በሚረከቡ ወጣቶች ዘንድ ጥርጣሬን የፈጠረ ይመስላል። ይህ ያሰጋቸው ከአንድ መቶ በሚበልጡ ሃገራት ባሉ 1700 በሚሆኑ ትላልቅ እና ትናንሽ ከተሞች የሚገኙ ተማሪዎች ለአንድ ቀን ትምህርታቸውን አቋርጠው መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ የሚያስችሉ ርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪ ሲያቀርቡ ውለዋል። ተማሪዎቹ የወደፊት ዕጣፈንታችንን ለስጋት ዳርጎታል ያሉትን የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር እና የብክለት መባባስ ከየራሳቸው ሃገራት መንግሥታት ጀምሮ ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው ሃገራት በሙሉ የየበኩላቸውን መፍትሄ ባስቸኳይ ለማበርከት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩም ጠይቀዋል። ወጣቶቹ በአንድ ቀን ያሉበት ርቀት ሲይገድባቸው ተጠራርተው አደባባይ በመውጣት ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረብ ያስቻላቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የተለዋወጧቸው መረጃዎች ናቸው። የተቃውሞው ዘመቻ ቀስቃሽ እና አነሳሽ ደግሞ የ16 ዓመቷ አዳጊ ወጣት ስዊድናዊት ግሬታ ቱዎንበርግ ናት። ታይም ሜጋዚን ባለፈው ጎርጎዮርዮሳዊ ዓመት ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩ 25 አዳጊ ወጣቶች መካከል የመደባት ግሪታ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር ቀርባ ግልጽ ባለ ቋንቋ የየሃገራቱን መንግሥታት መሪዎች ፊት ለፊት ተችታለች።

«ከምንም ነገር በላይ ልጆቻችንን እንወዳለን ትላላችሁ፤ ነገር ግን የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በዓይናቸው እያዩት ፊት ለፊት ትሰርቃላችሁ።»

Deutschland Hamburg Klima Demonstration | Greta Thunberg

የ16 ዓመቷ ስዊድናዊት ግሬታ ቱዎንበርግ

ስዊድናዊቷ ተማሪ ይህን የተናገረችው ባለፈው ኅዳር ወር ማለቂያ በፖላንዷ ካቶቪትሰ ከተማ በተካሄደው በ24ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባኤ ላይ ነው። የተማሪዋ ወላጆች ልጃቸው እንዲህ ያለውን ዘመቻ ስትጀምር ማን ሊሰማሽ ነው በሚል ተስፋ በማስቆረጥ ሊያስቆሟት ሞክረው ነበር። እንደማንኛውም ወላጅ ልጃቸው ትምህርቷ ላይ ብታተኩር ነበር የሚደሰቱት ውሎ አድሮ ግን ጥረቷ ያስገረማቸው ቤተሰቦቿ የአካባቢ ተፈጥሮን ለመጠበቅ የበኩሌን አደርጋለሁ በሚል የእንስሳት ተዋፅኦን አልመገብም ማለቷን ጭምር ተቀብለዋት ደግፈዋል። ቴድ ቶክ በተባለው መድረክ በቀረበችበት አጋጣሚ ኦውቲዝም ካለባቸው ልጆች አንዷ መሆኗን በማሳወቅ ዓለም በአፉ የሚናገረውን በተግባር ለማድረግ ይቸግረዋል ስትል ወቅሳለች።

«በተለይ የዘላቂነት ችግርን በተመለከተ ሁሉም ሰው የአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ ከፊታችን የተጋረጠ ስጋት እና ለሁላችን እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን እየገናገሩ፣ አሁንም ልክ በፊት እንደሚያደርጉት ማድረግ ቀጥለዋል።»

የ16 ዓመቷን ስዊድናዊት የተመለከቱ እና እሷን የተከተሉ የዕድሜ አቻዎቿ ባለፈው ዓርብ ትምህርታቸውን ትተው በተለያዩ ሃገራት ከተሞች አደባባይ በወጡበት ወቅት

«የአየር ንብረት እየተለወጠ ነው፤ እኛ ለምን አንለወጥም?» የሚለው ከያዟቸው መፈክሮች አንዱ ነበር።

በዕድሜ ከፍ ያሉት እና አዋቂዎች መዘናጋት የነገ ተተኪዎቹ ወጣቶችን አላስደሰተም። በርሊን፣ ኒውዮርክ፣ ሎንደን፣ ፓሪስ፣ ቶኪዮ እና ሌሎችም ከተሞችን ያጥለቀለቁት ተማሪዎች አየር ንብረት ለውጥ ተባብሶ ከቀጠለ ሕልውናቸውን አደጋ ላይ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። ጃፓናዊቷ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሃናይ ታካሀሺ ከእነዚህ አንዷ ናት፤

«ቤተሰቦቼ የሚኖሩት ቶኪዮ ውስጥ ካሉት ወንዞች አንዱ በሆነው በታማ ወንዝ አቅራቢያ በመሆኑ ከባድ ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ ቢያስከትል ይጎዳናል ብዬ እፈራለሁ።»

የ10ኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን የገለፀው የ15 ዓመቱ ሕንዳዊ ተማሪ አማን አሽማራ በበኩሉ በአየር ብክለት ምክንያት ለቀናት ከትምህርት ቤት የሚቀሩበት ጊዜ እንዳለ በመግለፅ፤ መንግሥት አንድ ነገር እንዲያደርግ ጠይቋል።

«ዴሊ ይህ ችግር መኖሩን ያውቃል ብዬ አስባለሁ፤ ስለዚህ ጉዳይ ደጋግመን መናገር አለብን፤ ብዙ ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩን እንደማያምኑ አውቃለሁ፤ ስለዚህ ማውራትም ሆነ መቀበል አይፈልጉም፤ ሌሎች ደግሞ አሉ፤ እንጸልይላችኋለን፤ በጎ ምኞታችን ከእናንተ ጋር ነው የሚሉ፤ ነገር ግን ጸሎት እና መልካም ምኞት ሳይሆን እኛ የምንፈልገው ተግባር ነው።»

  

በጀርመኗ ዋና ከተማ በርሊን በተካሄደው ተመሳሳይ ሰልፍ እስከ 10 ሺህ የተገመቱ ወጣት ተማሪዎች እና የተፈጥሮ አካባቢ ጥንቃቄ እንዲደረግለት የሚሟገቱ ወገኖች ተሳትፈዋል። አማራጭ ፕላኔት የለምን የሚል እና ሌሎች በርካታ መፈክሮችን ያነገቡት ልጆች በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት የነገው ዕጣ ፈንታችንን ለማስተካከል የበኩላችሁን አድርጉ ሲሉ ለሀገሪቱ መሪዎች ጥሪ አቅርበዋል። የ20 ዓመቷ ጀርመናዊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ካርላ ሬምትስማ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶች በተጠራሩበት ሰልፍ ላይ ተገኝተው መምረጥ የማይችሉ ወጣቶች ለፖለቲከኞች ድምፃቸውን ማሰማታቸው ወሳኝ መሆኑን ተናግራለች።

«አሁን በመላው ዓለም የሚገኙ ወጣቶች በአንድ ቀን አደባባይ ወጥተው ተግባራዊ ርምጃ የመውሰጃው ቀን ዛሬ ነው እያሉ ነው። ምንም እንኳን ዛሬ ያን ያህል ጉዳቱን ባናየውም የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን ይመለከታል፤ ነገ መላው ዓለም ላይ ተፅዕኖውን ያሳርፋል። መምረጥ የማይችሉ ወጣቶች እዚህ አደባባይ ሃሳባቸውን መግለፅ መቻላቸው በጣም አስፈላጊ ነው።»

እሷ እንዳለችው 50 በሚሆኑ የዋትስአፕ የቡድን ስብስቦች የሰልፉ ቅስቀሳ 30 ሺህ ለሚሆኑ ተማሪዎች ተዳርሷል። እሷም መልዕክቱን ካዳረሱት አንዷ ናት።

አንዳንድ ፖለቲከኞች ወጣቶቹ ትምህርታቸውን ትተው ለሰልፍ መውጣታቸው ተገቢ አይደለም ቢሉም፤ ተማሪዎቻቸው ስጋታቸውን ተረድተው ድምፃቸውን ሊያሰሙ መውጣታቸውን የደገፉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎችም ጥቂት አይደሉም። በበርሊኑ የሳይንስ ዩኑቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፎልከር ኳሸኒንግ፤

«እኛ የሙያው ሰዎች ተግባራዊ ርምጃ የመውሰጃው ጊዜ አሁን ነው እያልን ድምፃችንን ስናሰማ አስርት ዓመታት ተቆጠሩ፤ አሁንም መንወሳቀስ አለብን፤ እንዲህ ያለው ግፊትም ለእኛ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው እዚህ ያሉትን ወጣት ሰልፈኞች ከሙያው አኳያ የምንደግፈው።»

ኬንያን ጨምሮ 14 ገደማ በሚደርሱ የአፍሪቃ ሃገራት ተማሪዎችም በዕለቱ ተመሳሳይ ሰልፍ አካሂደዋል። ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሙቀት አማቂ ጋዞች በከባቢ አየር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት በተለያዩ ጥናቶች እየተደገፈ ቢቀርብም በቂ ርምጃ ባለመወሰዱ በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓ,ም የልቀት መጠኑ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ተመዝግቧል። በዚህ ቀጠለም ዓለም ለኑሮ አመቺ የመሆኗ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን ሳይንቲስቶች እያሳሰቡ ነው።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች