የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት የገጠመው ፈተና
ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017የመንግሥታቱ ድርጅት በአማራ ክልል በረድዔት ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ጥቃት ተከትሎ መሠረታዊ የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የሚያቀርበውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቋረጥ ውጥን መያዙን ዘገባዎች አመለከቱ።
ድርጅቱ ከጥር ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት አሥር የረድዔት ድርጅት ሠራተኞች አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው እና 11 ያህል ደግሞ መታገታቸውን አመልክቷል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን "መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራባቸው ባሉ ቦታዎች "አንዳንድ ነገሮች ሊያስቸግሩ ይችላሉ" ሲል የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞችን ነጥሎ ከጉዳት ለመከላከል የሚያስቸግር ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል አመልክቷል።
በሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት በኩል "ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ናት ብሎ ዓለም አቀፋዊ ድምዳሜ የመስጠት" ፍላጎት እንዳለ አንድ የተቋሙ የሥራ ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ የተባበሩት መንግሥታትአዘጋጀው በተባለ ምክረ ሐሳብ ድርጅቱ በአማራ ክልል የሚያካሄደውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ለጊዜው የማቆም ውጥን ይዟል። ሆኖም ይህ እቅድ በሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት እና አጋሮች በበጎ እንዳልታየ ይልቁንም ተቃውሞ እንደገጠመው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት እንዳስጠነቀው የሚሰጠውን የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያቋርጥ ከሆነ በክልሉ ውስጥ ድጋፍ የሚደረግላቸውን 2.3 ሚሊዮን ሰዎች የሚጎዳ ስለመሆኑም ተዘግቧል።
ካለፈው ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ 8 የረድዔት ሠራተኞች መገደላቸው
በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ካለፈው ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ8 የረድዔት ሠራተኞች መገደላቸውን እና 20 ያህል ደግሞ መታገታቸውን ከሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር።
የፀጥታ ሥጋት ያለበት አማራ ክልል ለሥራቸው ትልቅ እንቅፋት ከገጠማቸው አካባቢዎች ዋናው መሆኑንም ኃላፊው በወቅቱ ጠቅሰው ነበር።
በጉዳዩ ላይ ለዶቼ ቬለ ምላሽ የሰጡት በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ አታለል ይባዝን "የሀገሪቱን ፖሊሲ አክብሮ የሚሠራ የትኛውንም ረጂ ተቋም የኢትዮጵያ መንግሥት ከልክሎ አያውቅም" ብለዋል።
"በየትኛውም አካባቢ የሰላም ችግሮች አንዳንድ ቦታዎች ይከሰታሉ። የእነሱ [የድርጅቶች ሠራተኞች] የተለዩ ሰዎች ሆነው በዚህ ውስጥ እንደ ሰው የማይነኩበት ነገር ላይፈጠር ይችላል"።
የዓለም ምግብ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ተወካይ ዝላታን ሚልሲክ ከሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ሥራ ፈታኝ መሆኑን፣ በረድዔት ሠራተኞች ላይ ግድያ፣ እገታ፣ ዝርፊያ እና ሌሎች ጥቃቶች እንደሚደርሱ ገልፀው ነበር። ያም ሆኖ ግን "እርዳታን የማቆም እቅድ የለንም" ማለታቸውን በወቅቱ ዘግበን ነበር።
"ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለይም በአማራ ክልል እየጨመረ የመጣው የጸጥታ ችግር ድጋፍ ለሚሹት ለመድረስ እንቅፋት እየሆነብን ነው። ሥራዎቻችን ከፍተኛ የፀጥታ እና የደህንነት ሥጋቶች ያጋጥማቸዋል። በዚህ ዓመት የ8 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። እንዲሁም ባለፈው ዓመት ከ20 በላይ ሠራተኞች ታፍነው ተወስደዋል። ለዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብአዊ ሰራተኞች ደህንነት በጣም አስፈላጊ ነው። እናም የደህንነት ሥጋቶችን ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በቋሚነት ለማሻሻል ከአጋሮቻችን ጋር እየሰራን ነው። ሁሉም አካላት የሰብአዊነት ሠራተኞችን ጨምሮ የዜጎችን ደህንነት እና ጥበቃ ማረጋገጥ አለባቸው"።
ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም መመለስ አለባቸው የሚል አቅጣጫ ወርዷል - መንግሥት
የተባበሩት መንግሥታት እንዳለውም የሰብዓዊ ድጋፍ ወደማቋረጡ ቢገባ የመንግሥት እርምጃ ምን ይሆናል የሚለውን በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ለሆኑት ለአቶ አታለል ይባዝን ጥያቄ አቅርበናል።
"ይህ እርምጃ የሚወሰድ ከሆነ መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ንቅናቄ ፈጥረን ከባለፈው መጋቢት - ሚያዝያ ጀምሮ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የአደጋ ሥጋት ፖሊሲ አፀድቋል። ፖሊሲውን መነሻ በማድረግ የአደጋ ሥጋት ምክር ቤት ተቋቁሟል። ከዚህ መነሻ ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም መመለስ አለባቸው የሚል አቅጣጫ ወርዷል"።
የዓለም ምግብ መርሐ ግብር ባለፈው ዓመት የእርዳታ ምግብ ስርቆት መከሰቱን በመግለጽ በኢትዮጵያ ይህንን ድጋፍ አቋርጦ ቆይቶ ዳግም ከዓመት በፊት መጀመሩ ይታወሳል።
ሰለሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ