ቬኔዙዌላ ነዳጅ ሃብቷን መቆጣጠሯና ከዓለም የገንዘም ተቋማት መውጣቷ | ኤኮኖሚ | DW | 02.05.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቬኔዙዌላ ነዳጅ ሃብቷን መቆጣጠሯና ከዓለም የገንዘም ተቋማት መውጣቷ

ቬኔዙዌላ በውጭ ኩባንያዎች ቁጥጥር ሥር የቆየ የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪዋን በመውረስ ከትናንትናው ምሽት ወዲህ የንብረቷ ባለቤት መሆኗን አረጋግጣለች። ላቲን አሜሪካይቱ አገር በነዳጅ ዘይት ሃብቷ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ታላላቅ አምራቾች አምሥተኛዋ ናት።

ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ

ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ

ይህ ብቻ አይደለም፤ ቬኔዙዌላ የሃያላን መንግሥታት መሣሪያዎች የምትላቸውን የዓለም ባንክንና ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቋም IMF-ን ለቃ የምትወጣ መሆኗንም ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል። ላቲን አሜሪካ ውስጥ ግራ አዘንባይ መሪዎች መበራከት ከያዙ ወዲህ ይህን መሰሉ ዕርምጃ ያልተጠበቀ ባይሆንም ቬኔዙዌላ የነዳጅ ዘይት ማውጫ ምድሯን ከታላላቁ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥጥር አላቃ መውረሷ በምዕራቡ ዓለም ላይ ብርቱ ተጽዕኖ፤ በተፈጥሮ ጸጋ ለታደሉ ለሌሎች ታዳጊ አገሮችም የተለየ መልዕክት የሚኖረው ነው። ኡጎ ቻቬዝ ከወራት በፊት የወሰኑትን ገቢር ሲያደርጉ በሌላ በኩል ደግሞ ዓይናችሁን ለአፈር ያሏቸው ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የዓለም ባንክና IMF በውስጣዊ ሽኩቻና በዓመኔታ እጦት ተወጥረው እንደቀጠሉ ነው።

“ዛሬ የተፈጥሮ ሃብታችን በሌሎች ዕጅ የነበረበት ዘመን አክትሞ አሁን የቬኔዙዌላ ሕዝብ ንብረት ሆኗል!” የቬኔዙዌላ ነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ በመንግሥት መወረሱ ዕውን ሊሆን መብቃቱን ባለፈው ምሽት ባሰሙት ንግግር በዚህ መልክ የገለጹት ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ ነበሩ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአገሪቱ ላብአደሮች በውጭ ኩባንያዎች ቁጥጥር ሥር ወደቆየው የነዳጅ ዘይት ማውጫ ምድር በመጉረፍ ከትናንቱ ግንቦት-1 የሠራተኛ ቀን እንዲገጥም ሆኖ የተወሰደውን የመንግሥት ዕርምጃ በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል።

ሠራተኛው በምሥራቃዊው ኦሪኖኮ አካባቢ ወደሚገኘው ስፍራ ከመጉረፉ ከእኩለ-ሌሊት በፊት የነዳጅ ዘይት ይዞታውን የተቆጣጠረው ቀደም ብሎ የተላከ የጦር ሃይል ቡድን ነበር። ለዘወትሩ በጦር ሃይል የሚጠበቁት ኩባንያዎች በጦር ሃይል ይዞታቸውን አስረከቡ። ኡጎ ቻቬዝ ቃልን-ገቢር አድርገዋል፤ ቁርጠኝነታቸውን አስመስክረዋል። ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ በውርሱ ዋዜማ አገራቸው የዓለም ባንክንና የምንዛሪውን ተቋም ለቃ እንደምትወጣ ማስታወቃቸውም ተዳምሮ ለምዕራቡ ዓለም፤ ለሞኖፖል ኩባንያዎቹም የጥፊን ያህል መሆኑ አልቀረም። ቻቬዝ ሁለቱን ዓለም አቀፍ ተቋማት የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አገልጋይ መሣሪያዎች፤ ጥቅም አስጠባቂዎች ሲሉ በተደጋጋሚ ወንጅለዋቸዋል። ቬኔዙዌላ ለነገሩ ቻቬዝ እጎ.አ. በ 1999 ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ከሁለቱ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት እየመነመነ ነው የመጣው። ካራካስ ውስጥ ይገኝ የነበረው የ IMF ቢሮ ባለፈው ዓመት ሲዘጋ ቬኔዙዌላ በዓለም ባንክና በምንዛሪው ተቋም ዘንድ የነበረባትን ዕዳ በሙሉ ከፍላለች።

መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና የቬኔዙዌላ ግንኙነት የፍቅር አልነበረም። በ 1989 ቻቬዝ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው አሥር ዓመታት ቀደም ሲል መሆኑ ነው፤ ተቋሙ ለቬኔዙዌላ የሚያቀርበውን በጀት በመቁረጡ ብርቱ የሕዝብ ቁጣን ማስከተሉ አይዘነጋም። ጉዳዩ የቀሰቀሰው ዓመጽ ጠንከር ባለ የፖሊስና የጦር ሃይል ጡንቻ እንዲገታ ሲደረግ 300 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው አሻራውን ጥሎ ያለፈ የጥላቻ ቅርስ ነው። አሁን የምናየው “የወጋ ቢረሣ የተወጋ አይረሣም” የሚል ምላሽ መሆኑ ነው። ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ አገራቸው ሁለቱን የገንዘብ ተቋማት ለቃ እንደምትወጣ ሲያስታውቁ በምትኩ በላቲን አሜሪካ አንድ አበዳሪ አካል ለመፍጠር የሚያቅዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በዚህ ዕርምጃ ደግሞ የቬኔዙዌላ የነዳጅ ዘይት ገቢ የዕቅዱ ምሶሶ ነው።

በላቲን አሜሪካ ግራ አዘንባይ መሪዎች መበራከት መያዛቸው ምዕራባውያን ኩባንያዎች የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ እንዳሻቸው የሚዝቁበት ጊዜ እያለፈ መሆኑን ማሣየት ይዟል። ባለፈው ዓመት የቻቬዝ የቅርብ ወዳጅ የቦሊቪያው ፕሬዚደንት ኤቮ ሞራሌስ በመጠኑ ከቬዙዌላ ቀጥሎ ሁለተኛው የሆነውን የአገሪቱን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የመንግሥት ንብረት አድርገው ማወጃችው ይታወሣል። የኤኩዋዶሩ ፕሬዚደንት ራፋኤል ኮሬያም በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለችው አገራቸው ከአውጪና ፈላጊ ኩባንያዎች ጋር ያላትን ውሎች መልሶ ለማጤን እንደምታቅድና አንዳንዶቹን ስምምነቶች ለመሰረዝ እንደምትችልም በበኩላቸው አስገንዝበዋል። የኤኩዋዶር መንግሥት ኮሬያ ፕሬዚደንት ከመሆናቸው በፊት ባለፈው ዓመትም አገሪቱ ከአንድ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የነበራትን ውል ስምምነቱን ጥሷል በሚል ማፍረሱ የሚዘነጋ አይደለም።

ዕርምጃው በዋሺንግተንና በኪኢቶ መካከል የሚካሄደው የነጻ ንግድ ውል ድርድር እንዲቋረጥ ምክንያት እስከመሆን ደርሶ ነበር። ግን ለምዕራቡ ዓለም ግፊት የተንበረከከ የለም። ወደ ቬኔዙዌላ እንመለስና በምሥራቃዊው ቬኔዙዌላ በኦሪኖኮ ወንዝ አካያ የሚገኘው 600 ኪሎሜትር ርዝመትና 70 ኪሎሜትር ስፋት ያለው የነዳጅ ዘይት ምድር በዓለም ላይ ሰፊውን የጥሬ ዘይት ሃብት ክምችት የያዘ መሆኑ ነው የሚታመነው። በቬኔዙዌላ መንግሥት አባባል ስፍራው አሁን አገሪቱ ካላት 80 ቢሊዮን በርሚል ጥሬ ዘይት ሲነጻጸር እስከ 370 ቢሊዮን በርሚል የያዘ ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም በዓለም ላይ አምሥተኛዋ ነዳጅ ዘይት አምራች አገር በሃብቷ ከቀደምቶቹ አንዷ መሆኗ ብዙም አያጠያይቅም።

ምዕራባውያኑ የውጭ ኩባንያዎች ይሄ ሁሉ ሃብት ከቁጥጥራቸው መውጣቱ በቀላሉ የሚዋጥላቸው እንደማይሆን አንድና ሁለት የለውም። ነዳጅ ሲያወጡበት የቆየውን ምድር ቁጥጥር የመንግሥት ይዞታ ለሆነው “ፔትሮሌዎስ-ዴ-ቬኔዙዌላ” የተሰኘ ኩባንያ ማስረከብ ሲገደዱ እንደ ማካካሻ የተሰጣችው ለዚያውም ጥቂት የጋርዮሽ የጆይንት-ቬንቸር ድርሻ ብቻ ነው። ይህን ደግሞ ወደዱም ጠሉ የአሜሪካን ኤክሶንና ሼቭሮንን፣ የፈረንሣይን ቶታል፣ የብሪታኒያን ብሪቲሽ-ፔትሮሊየምና የኖርዌይን ስታትኦይልን የመሳሰሉ ሃያ ኩባንያዎች ተቀብለውታል። ስምምነቱ ገና ያልተጠናቀቀው ከሌላው የአሜሪካ ኩባንያ ከ ኮኖኮ-ፊሊፕስ ጋር ብቻ ነው።

ዓለምአቀፉ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች በአራት ተጣመር ድርጅቶች ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ወዲህ በኦሪኖኮ ምድር የሚገኘውን ከባድ ጥሬ ዘይት ወደ ቀላልና ጥራት ወዳለው ምርት ለመቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ገቢር ለማድረግ ብዙ ገንዘብ አፍሰዋል። በየቀኑ 600 ሺህ በርሚል ዘይት ለማውጣትም ሲበቁ ሲሶውን ድርሻና በየበርሚሉ ደግሞ 50 በመቶ የገቢ ታክስ ይከፍላሉ። የሚያስገርም ሆኖ ቬኔዙዌላ ለውጭ ንግድ ከምታቀርበው ነዳጅ ዘይት ከግማሽ የሚበልጠው የሚሄደው የቻቬዝ ቀንደኛ የፖለቲካ ጠላት ወደሆነችው ወደ ዩ-ኤስ-አሜሪካ ነው።

ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ በውጭ ኩባንያዎች ዕጅ የሚገኙት የአገሪቱ ሃብትና ተቋማት፤ ነዳጅ ዘይት፣ ጋዝ፣ ቴሌኮሙኒኬሺንና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እንዲወረሱ ዕርምጃቸውን ያፋጠኑት በዚህ ዓመት ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን እንደጀመሩ ነው። መራጫቸው ደግሞ የ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ሶሻሊዝም ያሉትን ሥርዓት ለማነጽ የተነሱበትን ዓላማ እንዲያራምዱ ሰፊ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። እርግጥ በላቲን አሜሪካ የተያዘው ዕርምጃ ጸረ-ኢምፔሪያሊስት ርዕዮተ-ዓለም ብቻ የቀሰቀሰው ሆኖ ሊታይ አይችልም። ሃብቱን ሲያሟጥጡ የኖሩት የውጭ ኩባንያዎች አገሬው ሲራብ-ሲራቆት መደለባቸው፤ የጸጋው ባለቤት የረባ ጥቅም ሳያገኝ እነሱው በያመቱ በብዙ ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት ትርፍ ማጋበሳቸው ዋናው ምክንያት ነው።

ዓለምአቀፉ ኩባንያዎች የተፈጥሮ ሃብት በሚያወጡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተግባራችው ከሌሎች ውስጣዊ ምክንያቶች ተጣምሮ ለረባ የኤኮኖሚ ዕድገት የበጀበት ቦታ የለም። ስማችው ይበልጥ የሚነሣው የአካባቢን ተፈጥሮ በመበከልና በለየለት ብዝበዛ ነው። በላቲን አሜሪካ የተያዘው አዝማሚያ ውሎ አድሮ በአፍሪቃም ተከታይ ሊያገኝ ይችላል። ዛሬ የነዳጅ ዘይት ፍጆት መጨመር፤ በአንጻሩም ዋጋው እየናረ መሄዱ፤ በሌላም ቻይና በተለይ ለዚሁ የተፈጥሮ ሃብት በአፍሪቃ የያዘችው መስፋፋትና ከሩሢያ እስከ ማዕከላዊው እሢያ ነዳጅ ዘይትና ጋዝ የፖለቲካ ግፊት መሣሪያ በሆነበት ሁኔታ የምዕራቡ ዓለም ጥገኝነት ይበልጥ የሚጠናከር ነው የሚመስለው። እርግጥ ከባለሃብቶቹ አገሮች አኳያ ሃብቱን መውረሱም ሆነ በራስ ዕጅ ማስገባቱ መልካም፤ ሆኖም የሕዝቡን ማሕበራዊ ሁኔታ ለማሻሻል ሥራ ላይ ካልዋለ ግን ብዙም ጠቀሜታ አይኖረውም።

የፕሬዚደንቱ የፓውል ዎልፎቪትስ ወዳጃቸውን ለደሞዝ ጭማሪና ሹመት የማብቃት ዕርምጃ በውስጣዊ ቀውስ ላሽመደመደው ለዓለም ባንክና ለመንትያ አካሉ ለዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የራስ ምታት እንደሆነ ሳለ ቻቬዝ ከገንዘብ ተቋማቱ ገሸሽ የማለታቸው ያልተጠበቀ ዕርምጃም ዱብ ዕዳ ነው የሆነባቸው። ሁለቱ ተቋማት ከ 60 ዓመታት በፊት ሲቋቋሙ የተጸነሱበት ዓላማ የዓለም ኤኮኖሚ ተረጋግቶ እንዲራመድና ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል እንዲያግዙ ነበር። ሆኖም ግን ከጅምሩ በአሜሪካና በአውሮፓ መንግሥታት ሲደጎሙ የኖሩት ድርጅቶች በተለይ በታዳጊው ዓለም በጎ ስም አላፈሩም። የሃያላኑ ምዕራባውያን መንግሥታት ጥቅም ማራመጃ መሣሪያዎች በመሆን በተደጋጋሚ ይወቀሳሉ። ይህም ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት በደፈናው መሠረተ-ቢስ ክስ ነው ሊባል አይችልም።
የቬኔዙዌላው ፕሬዚደንት ኡጎ ቻቬዝ ባለፈው ሰኞ ከተቋማቱ እንደሚለዩ ሲያስታውቁ ድርጅቶቹ ቀውስ ላይ ወድቀዋል፤ IMF ግዴታውን ለማሟላት በቂ ገንዘብ እንደሌለው የሆነ ጋዜጣ ላይ አንብቤያለሁ ሲሉ ነበር ፌዝ በተመላበት ሁኔታ የተናገሩት። እርግጥ የቻቬዝ ፌዝ ፌዝ ብቻ አልነበረም። የቬኔዙዌላው መሪና የምንዛሪው ተቋም ግንኙነት ድርጅቱ በተለይ በ 2002 ዓ.ም. የተደረገባቸውን ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ከደገፈ በኋላ መሪር ጣዕም ያለው ሆኖ ነው የቆየው። ለነገሩ የወታደራዊው አገዛዝ ዕድሜ ከ 47 ሰዓታት በላይ አላለፈም፤ ቻቬዝም ወዲያው ወደ ሥልጣናቸው ይመለሳሉ። የቀረው ትዝብት ነበር። በምንዛሪው ተቋም ላይ ጥርሳቸውን የሚነክሱት የእጄንቲናንና የኤኩዋዶሩን ፕሬዚደንቶች ኔስቶር ኪርሽነርንና ራፋኤል ኮሬያን የመሳሰሉት የላቲን አሜሪካ መሪዎች ብዙዎች ናቸው።

ለምንዛሪው ተቋም ከላቲኖ አገሮች ያለው ግንኙነት መሻከር ወደፊት የገንዘብ ተጽዕኖም ይኖረዋል። ድርጅቱ ሰሞኑን እንዳስታወቀው በዚህ ዓመት 165 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱ የማይቀር ነው። ይህ ደግሞ የበጀት ቆፍጣናነትን ሲሰብክ ከቆየው ድርጅት ፍልሥፍና ጋር ባለመጣጣሙ እንቆቅልሽ መሆኑ አልቀረም። ሁኔታው በቅርብ የሚሻሻልም አይሆንም። በሚቀጥሉት ሶሥት ዓመታት እንዲያውም የገቢው ማቆልቆል 400 ሚሊዮን እንደሚደርስ ነው የሚጠበቀው። የምንዛሪው ተቋም በጀት ዛሬ በአጠቃላይ በአራት ዕጅ አቆልቁሏል። ታዛቢዎች እንደሚሉት የተቀረውም ጨርሶ መጥፋቱ የጊዜ ጉዳይ ነው። ሁለቱ የብሬተን-ዉድስ ጽንሶች የዓለም ባንክና የምንዛሪው ተቋም ለተመሠረቱበት ዓላማ ብቁ እንዲሆኑ ከጊዜው የተጣጣመ፤ ሚዛን የጠበቀ ለውጥ ማድረጋቸውና ከሁሉም በላይ ደግሞ ዓመኔታ ለማትረፍ መብቃታቸው ወሣኝ ነው። የእስካሁኑ ሚናቸው በተለይም ታዳጊውን ዓለም በማልማቱና ድህነትን በመታገሉ ረገድ የሚያኮራ አልነበረም።