ቬስተርቬለ፣ማንነታቸው እና ህልፈታቸው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ቬስተርቬለ፣ማንነታቸው እና ህልፈታቸው

በቅርብ የሚያውቋቸው የተዋጣላቸው ፖለቲከኛ ፤አንደበተ-ርቱዕ ፣ያሉትን የሚያደርጉ ከምንም በላይ ለነፃነት የሚቆሙ ሲሉ ያወድሷቸዋል ፤ በ54 ዓመታቸው ባለፈው አርብ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የቀድሞ የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለን ።

10.01.2009 DW-TV Journal Interview Guido Westerwelle

አንዳንዶች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ስኬታማ ከሚባሉ ለዘብተኛ አቋም ካላቸው የጀርመን ፖለቲከኞች ተርታ ያሰልፏቸዋል ። በአንጻሩ ደግሞ እድለ ቢስ ፖለቲከኛ የሚሏቸውም አልጠፉም ። በእንግሊዘኛው ምህፃር FDP የሚባለውን የነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲያቸውን በርሳቸው አመራር ሳይጠበቅ ለከፍተኛ ደረጃ በማብቃት እንደመመስገናቸው በተቃራኒው ፓርቲው ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ለደረሰበት ከፍተኛ ሽንፈትም ተጠያቂ የሚያደርጓቸው ጥቂት አይደሉም ። በፖለቲካው ና በግል ህይወታቸው ፣ነፃነት ላይ ብቻ ያተኮረ ለዘብተኛ አስተሳሰብ ያራምዳሉ የሚሏቸውም አሉ ። በግል ህይወታቸው ግብረ ሰዶማዊ መሆናቸውን በይፋ የተናገሩ የመጀመሪያው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው ። የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ሊቀመንበር ክርስቲያን ሊንድነር ቬስተርቬለን ለብዙዎች አርአያ በተለይ ደግሞ በሥልጣን ዘመናቸው በሰሜን አፍሪቃ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የጣሩ ሲሉ አወድሰዋቸዋል ። ለዘብተኛ አቋም እንደያዘ ፖለቲከኛ መላውን ትውልድ አነቃቅተዋል ወይም አነሳስተዋል ።ጊዶ ቬስተርቬለ ጥርጣሬ የሌለበት በጣም ግልፅ የሆነ የፖለቲካ ኮምፓስ ነበራቸው ። ከርሳቸው ጋር ነው ፓርቲያችን ለዓመታት ያደገውና ለትልቅ ውጤት የደረሰው ። የተመሰከረላቸው የገበያ አዋቂ ና አውሮፓዊም ነበሩ ።በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የሥልጣን ዘመናቸውና ከዚያም በኋላ በአስቸጋሪው ወቅት ላይ አውሮፓ አንድ ሆኖ እንዲቆይ እንዲሁም በሰሜን አፍሪቃ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ የግል አጀንዳዎቻቸው ነበሩ »

Westerwelle / UN / Vollversammlung / New York

ቬስተርቬለ የህግ ባለሞያ ከሆኑት ወላጆቻቸው የተወለዱት በቀድሞዋ የምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ ቦን አቅራቢያ በምትገኘው ባድሆኔፍ በተባለችው ከተማ ነው ።10 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው በመለያየታቸው ከሶስት ወንድሞቻቸው ጋር አባታቸው ጋ ነው ያደጉት ። በትምህርት ቤት ያን ያህል ታዋቂ ባይሆኑም ብዙውን ጊዜ የመድረክ መሪ የመሆን ፍላጎት ነበራቸው ። ከዚሁ ጋር ደግሞ ስነ ስርዓት አክባሪ ና በራሳቸው የሚመኩና በሥራቸው እጅግ የሚኮሩ መሆናቸው ይነገራል ።

ጊዶ ቬስተርቬለ የነፃ ዲሞክራቶች ፓርቲ አባል የሆኑት የ19 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር ። ብዙም ሳይቆዩ የፓርቲው የወጣቶች ድርጅት ሊቀመንበር ሆኑ ። ቬስተርቬለ የህግ ትምህርት ተከታትለው በጥብቅና ቢያገለግሉም ልባቸው የፈቀደው ግን ፖለቲካ ነበር ። በ39 ዓመታቸው የፓርቲያቸው የFDP ሊቀ መንበር ለመሆን በቁ ። በዚሁ ሃላፊነት ከጎርጎሮሳዊው 2001 እስከ 2011 ለ10 ዓመት ሰርተዋል ። ፓርቲያቸውን በሊቀመንበርነት በመሩበት ዘመን የፓርቲውን አጀንዳ የሚቀርፁትና የፖለቲካውንም ትኩረት የሚቃኙት ርሳቸው ነበሩ ። በተለይ የወጣቱን ትኩረት ለመሳብ ቬስተርቬለ ከሌሎች ፖለቲከኞች የተለየ ስልት በመከተልም ስማቸው ይነሳል ። ከቬስተርቬለ የፖለቲካ ድሎች ትልቁ በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓም በጀርመን የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ነበር ። በዚያን ጊዜው ምርጫ ፓርቲያቸው ከዚህ ቀደም ባልተገመተ ሁኔታ ወደ 15 በመቶ ድምፅ በማግኘት ትልቅ ድል አስመዘገበ ። ይህ ውጤት FDP ከተመሠረተበት ከ1948 ዓም ወዲህ ፓርቲው አግኝቶት የማያውቀው ድል ነበር ።የቬስተርቬለ ፓርቲ ያኔ ሊያሸንፍ የቻለው የግብር ስርዓት ማሻሻያ ለማድረግ ቃል በመግባቱ ነበር ። ፓርቲው ፣ ለዜጎች ቀላል ፣የማያዳላ ፣ሁሉም የሚረዳው ያለውን የግብር ስርዓት ለመዘርጋት ቃል ከገባ በኋላ ከእህትማማቾቹ ከክርስቲያን ዲሞክራቶችና ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር በ 2009 ዓም ጥምር መንግስት ለመመሥርት ለሳምንታት በተካሄደው ድርድር ከዚያ ይልቅ ለሆቴሎች በተጨማሪ እሴት ታክስ ቅነሳ ላይ ብቻ መስማማቱ ለኋላ ውድቀቱ እንደ ዐብይ

Deutschland Bundestag Afghanistan Debatte Westerwelle und Merkel

ምክንያት ይነሳል ። ይህም ፓርቲው የፈፀመው ሊጠገን የማይችል ስህተት ተደርጎም ይወሰዳል ። ከዚህ በኋላም ጊዶ ቬስተርቬለ በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሁለተኛ ካቢኔ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኑ ። በዚሁ ሃላፊነት ለአራት ዓመታት የሰሩት ቬስተርቬለ ፣ ከጎርጎሮሳዊው 2009 እስከ 2011 የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥት ነበሩ ። ሜርክል ፣ ቬስተርቬለን ይበልጡን በንግግር ችሎታቸውና ታማኝነታቸው አስታውሳቸዋለሁ ይላሉ ።

«ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለን ከልብና ከራሳቸው በመነጨ ስሜት ለሰላምና ለሰብዓዊ መብት ባካሄዱት ትግል ፣ ወይም ደግሞ በጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ ውስጥ በምርጥ ተናጋሪነታቸው አስታውሳቸዋለሁ ።ጊዶ ቬስተርቬለ የሌሎችን ስሜት የሚረዱ አርቆ አሳቢ እና ቃላቸውን የሚያከብሩ እምነት የሚጣልባቸው ታማኝ ሰው ነበሩ ።በግሌ ከጊዶ ቬስተርቬለ ጋር ባካሄድኳቸው በርካታ ስብሰባዎችና ንግግሮች ክብር ይሰማኛል ። ከፖለቲካው ዓለም ከተገለሉም በኋላ ባደረኳቸው ውይይቶችም እንዲሁ »

ፓርቲያቸው የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህፃሩ FDP በመስከረም 2013 በተካሄደ አጠቃላይ ምርጫ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመግባት የሚያስችለውን 5 በመቶ የመራጭ ድምፅ ሳያገኝ በመቅረቱ ከፓርላማው ተሰናበተ ።በዚህ የተነሳም ቬስተርቬለ የሚኒስትርነት ሹመታቸውን ብቻ ሳይሆን የፓርላማ መቀመጫም ጭምር ነበር ያጡት ።ያኔ የ51 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ ።በጎርጎሮሳዊው መስከረም 2013 ዓም ቬስተርቬለ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ያሰሙት የመጨረሻ ቃል «ጀርመን በአውሮፓ ታማኝ አጋር ሆኖ ትቆያለች » የሚል ነበር ። ይህም የቬስተርቬለ የፖለቲካ ጉዞ ያበቃበት ወቅት ነው ። በቬስተርቬለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ዘመነ ሥልጣን ጀርመን በዙር ለሚደርሰው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባልነት ስትመረጥ ኒውዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቬስተርቬለ ባሰሙት በዚህ ንግግራቸው በውጤቱ መርካታቸውን ገልፀው ነበር ።

Der Kanzlerkandidat der FDP, Guido Westerwelle auf dem FDP-Bundesparteitag in Mannheim

«በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ግልጽ አሠራር እንዲሰፍን እንታገላለንን ።ከተባበሩት መንግሥታት አባል ሃገራት ጋር በሙሉ ግልፅ የሆነ ውይይት የምናደርግ ባልደረባ ሆነን እንቀጥላለን ። ለሰላም ለፀጥታ ለተፈጥሮ ጥበቃ ለልማት እና ለጦር መሣሪያ ቅነሳ እንዲሁም ዓለማችንን ከኒዩክልየር ነፃ ለማድረግ የቆምን በመሆናችን እንደሰታለን ። ጀርመን በምርትዋ ብቻ ሳይሆን በውጭ መርህዋም ለዓለም ትርጉም ያላት ሃገር በመሆንዋ በጣም ደስተኞች ነን ።ይህ ዓይነቱ ትርጉም ያለው አቋም እዚህ በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በሌሎች አገራትም ይንጸባረቃል የሚል ተስፋ አለን ። »

በ48 ዓመታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ቬስተርቬለ የጀርመን አጋር የሆኑት አሜሪካንና ብሪታንያ በጎርጎሮሳዊው2011 በሊቢያ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲፈቀድ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቬስተርቬለ ሃሳቡን በመቃወማቸው ከሃገር ውስጥ ሆነ ከውጭ በርካታ ትችቶች ተዥጎድጉደውባቸው ነበር ። በዚሁ ዓመት በፓርቲያቸው ውስጥ በተካሄደ አብዮት ከሊቀመንበርነት ሲወርዱ ምክትል መራሄ መንግሥትነቱንም ለተተኪያቸው አስረከቡ ። ፓርቲያቸው በ2013ቱ ምርጫ ከምክር ቤት ከተሰናበተ በኋላም ከፖለቲካው ዓለም ተሰናበቱ ። ብዙም ሳይቆይ በ2014 ፖለቲከኛው ቬስተርቤለ ድንገት በደም ካንሰር መያዛቸው ተሰማ ። በጎርጎሮሳው 2015 መጨረሻ አካባቢ ከበሽታው ጋር ስላደረጉት ትግል የጻፉበትን መፀሀፍ አወጡ ። ቬስተርቬለ ለብዙዎች መማሪያ ይሆናል ብለው ባሰተሙት በዚህ መፀሀፍ ተመስግነዋል ። በልዩ ተስጦአቸው በማራኪ ንግግራቸው የሚታወቁት ጠንካራው ፖለቲከኛ ቬስተርቬለ በዚሁ በሽታ ተሸንፈው ባለፈው አርብ አረፉ ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic