ቬልሄልም ፎን ሁምቦልት ማን ናቸዉ? | ባህል | DW | 30.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ቬልሄልም ፎን ሁምቦልት ማን ናቸዉ?

«ሁምቦልት ዩንቨርስቲ ማንኛዉም ሰዉ፤ ደኃ አለ ኃብታም፤ የንጉሳዊ ቤተሰብ ሆነ፤ ሰራተኛዉ ክፍል ዩንቨርስቲ ገብቶ መማር ይችላል፤ በሚል መርሕ የተመሰረተ ዩንቨርስቲ ነዉ። ከዚህ ዩንቨርስቲ የወጡትም ሰዎች የሰሩት ታሪክም በዓለም የተለያዩ ግኝቶች ላይ ያደረጉት ተሳትፎ በጣም ትልቅ ነዉ።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:24

ቬልሄልም ፎን ሁምቦልት ማን ናቸዉ?

 

በዓለማችን ዛሬ ለሚታየዉ ዘመናዊ ትምህርት መዋቅር እና የትምህርት አሰጣጥ መሰረት እንደጣሉ የሚነገርላቸዉ፤ ጀርመናዊ ምሁር ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ባለፈዉ ሳምንት 250 ኛ የልደት በዓላቸዉ ታስቦላቸዋል። በጀርመን መዲና ከ 200 ዓመት በፊት ባሳነፁት ዩኒቨርስቲም ከዓለም ሃገራት የመጡ ዜጎች ትምህርትን ይቀስማሉ፤ ታዋቂ ምሁራንንም አፍርቶአል። ቬልሄልም ፎን ሁምቦልት ማን ናቸዉ ?

«ሁምቦልት ዩንቨርስቲ የተመሰረተበት ሃሳብ ነዉ ዋናዉ ። ማንኛዉም ሰዉ፤ ደኃ አለ ኃብታም፤ የንጉሳዊ ቤተሰብ ሆነ፤ ሰራተኛዉ ክፍል ዩንቨርስቲ ገብቶ መማር ይችላል፤ በሚል መርሕ የተመሰረተ ዩንቨርስቲ ነዉ። ይህ ነዉ ዩንቨርስቲዉን ልዩ የሚያደርገዉ ከዚህ ዩንቨርስቲ የወጡትም ሰዎች የሰሩት ታሪክ በዓለም ታሪክ ላይ ፤ በዓለም የተለያዩ ግኝቶች ላይ ያደረጉት ተሳትፎ በጣም ትልቅ ነዉ።»  

በጀርመን የደረጃ መዳቢ መዘርዝር ዋንኛ ተብለዉ ከተቀመጡት አስር ከፍተኛ ተቋማት ማለት ዮንቨርስቲዎች መካከል አንዱ ስለሆነዉ ስለ ሁምቦልት ዩንቨርስቲ ያጫወቱን ዶክተር ፀጋዬ ደግነህን ነበሩ። ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ በርሊን ከሚገኘዉ ከሁምቦልት ዩንቨርስቲ በኤኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪአቸዉን፤ በቢዝነስ አድምኒስትሬሽን ማለት በንግድ አስተዳደር ዘርፍ  የማስትሬት ዲግሪያቸዉን አግኝተዋል። በዚሁ ዩንቨርስቲ ዉስጥ በንግድ ትምህርት ዘርፍ አስተማሪ ሆነዉም አገልግለዋል። በ1809 ዓ ም፤ የዛሬ 208 ዓመት ማለት በፕሬሻው ንጉሥ ሳልሣዊ ፍሪድሪኽ ቪልሄልም ዘመን የሁምቦልት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመቋቋም የበቃዉ በዊልሄልም ፎን ሁምቦልት ከፍተኛ አነሳሽነት ነበር። በቪልሄልም ፎን ሁምቦልት በጀርመን ትምህርትን ወደ ዘመናዊነት የለወጡ ፤ ዛሬ ጀርመን ለሚታየዉ የትምህርት ሥርዓት የመሰረት ድንጋይ ያኖሩ ፤ የቋንቋ ምሁር ፤ ፈላስፋ፤ ደራሲና፤ ብሎም በአንባሳደርንት ያገለገሉ መሆናቸዉ ይነገርላቸዋል።  በጀርመን ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸዉ እኝህ ምሁር ባለፈዉ ሃሙስ 250 ኛ የትዉልድ ቀናቸዉ ታስቦላቸዋል። በዚህ ዝግጅት ጀርመናዊዉን ምሁር ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ታሪክን እያየን በበርሊን ባቋቋሙት በሁምቦልት ዩንቨርስቲ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁ ኢትዮጵያዉያንንን በእንግድነት ይዘናል።

ጀርመናዉያን ባለፈዉ ሳምንት ዉስጥ የቪልሄልም ፎን ሁምቦልት 250 ኛ የልደት ቀንን ሲያስታዉሱና ታሪኩን ሲዘክሩ ዛሬ  ቪልሄልም ቢኖር ከሱ ሌላ የትምህርት ሚኒስትር የሚመኝ ባልነበር ያሉት። በጎርጎረሳዉያኑ 1779 ዓ.ም በርሊን አቅራብያ በሚገኘዉ ፖስትዳም ዉስጥ የተወለዱት የቪልሄልም ፎን ሁምቦልት በዝያ ዘመን የነበረዉ የፕሬሻውያ ንጉስ አገልጋይ ልጅ ነበሩ። ቪልሄልም  በቀድሞዉና በአዲሱ ዓለም ይነገሩ የነበሩ ዋንና የተባሉ ቋንቋዎችን ይናገሩ ነበር። በ 18ኛዉ ክፍለ ዘመን በአዉሮጳ ዋንና በተባሉት ማዕከሎች ማለትም በፓሪስ ለንደን ሮምና በፕሬሻውያዉ መዲና በርሊን እንደኖሩ ታሪካቸዉ ያሳያል።  ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ለጀርመን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ትምህርት ሥርዓት መሰረት የጣሉ በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ተቋማት በመንግሥት ሥር እንዳይተዳደሩ ያደረጉም እንደሆን ይነገርላቸዋል።  በበርሊኑ ሁምቦልት ዩንቨርስቲ የቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል። እንደ ረዳት መምህርም ለተወሰኑ ጊዜያት በዚሁ ተቋም ዉስጥ ያገለገሉ ኢትዮጵያዉያን ጥቂት አይደሉም። በበርሊን ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን አማረ በሁንቦልት ዩንቨርስቲ በፋይናንስ ኤኮኖሚ የማስትሪት ዲግሪያቸዉን ተቀብለዋል። የተቋሙንም የትምህርት ሥርዓት አድናቂ ናቸዉ። ስለ ጀርመናዊዉን ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ታሪክም ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። 

« ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ለኔ በሁለት በኩል ነዉ የማየዉ። በአንደኛ ደረጃ ለአሁኑ የጀርመን የትምህርት መዋቅር መሰረት የጣለ እሱ ነዉ። ይህ መሰረት የተጣለዉ መሰረት በ18 ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ነዉ። ሁለተናዉ ነጥብ ደግሞ አሁን ላለዉ በተለይ በዩንቨርስቲ ደረጃ ላለ ነፃነት ዋናዉን መሰረት የጣለዉ ቪልሄልም ነዉ። አንደኛ ዩንቨርስቲ የቲዮሪ መማርያ ብቻ ሳይሆን ቲዎሪዉን እና ምርምርን በአንድ አድርጎ  ዩንቨርስቲ ዉስጥ እንዲካሄዱ ሃሳብ አቅርቦ ይህ እንዲደረግ ያደረገ ሰዉ ነዉ። እንዲሁም ደግሞ ዩንቨርስቲ ነፃነት እንዲኖራት ከመንግሥትም ሳይቀር ነፃ እንድትሆን ጥገና እንዳትሆን የሚል አመለካከት የነበረዉ ሰዉ ነዉ። ከዝያ ተነስቶ በርካታ የምዕራብ ሃገር ዩንቨርስቲዎች በመቀበል ተግባራዊ አድርገዉታል። በብዙ ሃገሮች አሁንም ያለ ይህ ነዉ ፤ ዩንቨርስቲዎች በነጻነት ምርምርና ጥናታቸዉን እንዲያካሂዱ በመንግሥት ደግሞ ትልቅ ተጽኖ እንዳይደረግባቸዉ የሚለዉ ከዚህ የተነሳ ነዉ። ስለዚህ በተለይ በተለይ በአጠቃላይ ሁለተና ደረጃም ሆነ በከፍተኛ ትምህርት ቪልሄልም ትልቅ መሰረት የጣለ ሰዉ ነዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ።»

የአሁኑ ዘመን ጀርመናዉያን ሁምቦልትን እንዴት ነዉ የሚያዩት ለሚለዉ አቶ መስፍን ሲመልሱ «ለተራዉ ጀርመን ዘንድ ማንም ዞር ብሎ የሚያየዉ የለም። የሚያዉቀዉም ላይኖር ይችላል። ነገር ግን በተማሩት ሰዎች ዘንድ የትምህርት ነክን ነገር የሚያዉቁ ሰዎች ፕሮፊሰሮች አካባቢ ሁምቦልት መሰረት የጣለ ሰዉ ስለሆነ በጣም ያከብሩታል። በተለይ በምርምር ዉስጥ ያሉ ሰዎች በመንግሥት ተጽእኖ እንዳይኖርባቸዉ ፤ በፖለቲካ ተጽእኖ እንዳይኖርባቸዉ ፤ ራሳቸዉን ችለዉ የሚሰሩበትን መሰረት ስለጣለላቸዉ ፤ በጣም ይወዱታል ያከብሩታል። ግን እንድያም ሆኖ እለታዊ ሕይወታቸዉ ዉስጥ ሁምቦልት የሚጫወተዉ ሚና አነስተኛ ነዉ። »

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በበርሊን ነዋሪ የሆነዉ ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል የሆምቦልትን ዩንቨርስቲ አቅራብያ ነዋሪ ነዉ። ይልማ እንደሚለዉ ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት በተለይ ወጣቱን በእዉቀት ኮትኩቶ ማሳደግ በሚለዉ ጽንሰ ሃሳብ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ምሁር ሲል ይገልፃቸዋል።

«ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ወጣቶችን ኮትኩቶ ማሳደግ በሚለዉ ላይ ትልቅ ሚና የተጫወተ ሰዉ ነዉ። የሕይወት ታሪኩ በሁለት ነገሮች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነዉ። አንደናዉ ነፃ ትምህርት ለነፃ ዜጋ የሚለዉ የቪልሄልም ፎን ሁምቦልት መሰረታዊ ሃሳብ ነዉ። የነፃ ትምህርት ለነፃ ዜጋ ማለት አንድ ተማሪ የዘር ግንዱ ሳይታይ ማለትም ከደሃ ቤተሰብ ይሁን ወይም ከባለፀጋ ፤ ወይም ከባላባት ፤ከመሳፍንት ሳይባል ሁሉም ወጣት ትዉልድ ነፃ ትህርትና የከፍተኛ ትምህርት እድል ተሰጦት ተኮትኩቶ ቢያድግ ለሃገሪቱና ለሕዝቡ ይጠቅማል የሚለዉ አንደናዉ ሃሳብ ነዉ። ሁለተኛዉ ትምህርት ቤቶችና የዩንቨርስቲ ቅጽር ግቢዎች፤ ማንኛዉም የምርምር ጣብያዎች ከመንግሥት ነጻ ፤ ከፖለቲካ ቁጥጥር ነፃ ሆነዉ አስተማሪዎችም ሆኑ ተማሪዎች፤ በነጻ ሃሳባቸዉን አስተያየታቸዉን የምርምር ዉጤታቸዉንም እንዲያካሂዱ የሚል ነዉ። ቪልሄልም ይህን ሃሳብ ከእንግሊዝ የወሰደዉ ሲሆን ግን በሃገር ከፈረንሳይ አብዮት በኋላ ያስፋፋዉ ነዉ። ነገር ግን የቪልሄልምን ሃሳብ የጊዜዉ መሳፍንቶች ባለመቀበላቸዉ ቪልሄልም የትህርትን ስርአት ተሃድሶ ማድረግ ከሚለዉ ሃሳብ ሥራቸዉ ለቀዉ ወደ ዲፕሎማቲክ ስራ ተሰማርተዋል።

ግን ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ማን ነዉ ብለን ብንጠይቅ ማን ናቸዉ ብለን ልንገልጻቸዉ እንችላለን?

« ቬልሄልም ፎን ሁምቦልት ለሰዉ ነፃነትን ፊት ለፊት የተጋፈጡ የሴትና የወንድ እኩልነትን በራሳቸዉ የትዳር ሕይወት ያሳዩ በመሆናቸዉ ሰዉየዉ በጀርመንን ለዘብተኛ «ሊበራል» አስተሳሰብን ያስፋፉ ናቸዉ የሚባሉም ናቸዉ። ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ራሳቸዉ ዩንቨርስቲን የጨረሱ ሳይሆኑ አራት ሴሚስተር « ለሁለት ዓመት» ብቻ ትምህርታቸዉን ተከታትለዉ ያቋረጡ ናቸዉ ከዝያ ወጥተዉ ግን አንድ ሰዉ የራሱን እዉቀት ለማስፋት ራሱ  አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እድሜ ልኩን በማየት በማንበብ ይማራል የሚለዉን ፍልስፍና ስለያዙ ከዝያ ሃሳባቸዉ ተነስተዉ ብዙ እዉቀትን ሰብስበዋል። አባታቸዉ ከታናሽ ወንድሙ ከአሌክሳንደር ጋር የቤት አስተማሪ ቀጥረዉ ነዉ ያስተማርዋቸዉ።»

 የቪልሄልም ፎን ሁምቦልት የ 2 ዓመት ታናሽ ወንድም አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት በተለያዩ የዓለም ሃገራት በመጓዝ፣ እና  በመዘዋወር፣ በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች፣ በፊዚክስ፣ ሥነ-ህይወት ፣ ሥነ አራዊት፣ የወቅያኖስና የየብስ የአየር ንብረት፣ እንዲሁም ሥነ ፈለክ ጥናት ማድረጋቸዉ ይታወቃሉ።  ሁለቱ ወንድማማች ጀርመናዉያን ምሁራን ተነጣጥለዉ እንደማይታወሱ ፤ አቶ መስፍን አማረ ተናግረዋል።

የሁምቦልት ፎሩም አልያም የሁምቦልት የመሰብሰብያ አዳራሽ በሚል በርሊን በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የፈረሰና እየተገነባ  በሚገኘዉ የጥንት ቤተ- መንግሥት አፍሪቃን ጨምሮ የዓለምን ታሪክ ከተለያዩ ሃገራት ቤተ መዘክሮች በመሰብሰብ ሥነ-ጥበባትና ታሪክን በአንድ በማስቀመጥ ለዓለም ለእይታ የሚቀርብበት ትልቅ ማዕከል ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነዉ። አቶ መስፍን አማረ እንደሚሉት ይህ ታሪክን ሥነ ጥበባትን በአንድ ጥላ የማሰባሰብ መርህ ደግሞ ከ ቬልሄልም ፎን ሁምቦልት የተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል።

በጀርመን ለሚታየዉ ለዛሬዉ ዘመናዊ ትምህርት አሰጣጥ መዋቅር ትልቅ መሠረት የጣሉት ጀርመናዊዉ ቪልሄልም ፎን ሁምቦልት ትተዉ ባለፉት ቅርስ ሲታወሱ ይኖራሉ። ቪልሄልም የዩንቨርስቲ ትምህርታቸዉን ባያጠናቅቁም በርሊን ከተማ ከ200 ዓመት በፊት የመሰረቱት ሁምቦልት ዩንቨርስቲ ኢትዮጵያዉያን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ትምህርትን ቀስመዋል። ዩንቨርስቲዉ በዓለም ታዋቂ የሚባሉ ምሁራንንም አፍርቶአል።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

 

 

 

Audios and videos on the topic