ቦኮ ሐራም-የናጄሪያዉ አሸባሪ ቡድን | 1/1994 | DW | 08.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

1/1994

ቦኮ ሐራም-የናጄሪያዉ አሸባሪ ቡድን

ቡድኑ ባደረሰዉ ጥቃት ከሁለት መቶ ሐምሳ በላይ ሰዎች መግደሉን አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ዘግቧል። የናጄሪያ ፀጥታ አስከባሪዎች ባንፃሩ በተጠርጣሪ የቡድኑ አባላት ላይ ከፍተኛ በደል ያደርሳሉ

default

ማይዱጉሪ-ከቦኩ ሐራም ጥቃቶች አንዱ

08 09 11

አቡጃ የሚገኘዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፅሕፈት ቤት በቅርቡ በቦምብ ያጋየዉ ቦኮ ሐራም የተሰኘዉ ቡድን እንደሆነ በሰፊዉ ይታመናል።በአደጋዉ ከሃያ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ብዙ ቆስለዋል።ናጄሪያ ከአለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት አል-ቃኢዳ ጋር ስሟ የተነሳዉ አንድ የሐገሪቱ ወጣት የዩናይትድ ስቴትስን የመንገደኞች አዉሮፕላንን ለማጋየት በሞከረበት ወቅት ነበር፥- በጎሮጎሮሳዉያኑ 2009 በገና ዋዜማ።ይሁንና ወጣቱን ለሽብር ያስታጠቁና ያዘመቱት ወገኖች ፍንጭ ከናጄሪያ ይልቅ ወደ የመን ነበር ያመራዉ።በዚያዉ አመት ግን፥ ናይጄሪያ የራስዋ አሸባሪ ቡድን በቅሎባታል።ቦኮ ሐራም-የሚባል።የቡድኑን አለማና ምግር በመለከተ የሐዉሳ ክፍል ባልደረባ ቶማስ መሽ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።


ወደ ሰሜን ናጄሪያዊቷ ከተማ ማይዱጉሪ መጓዝ የፈለገ ቶማስ መሽ እንደሚለዉ እዚሕም-እዚያም የተገጠገጡ የፍተሻ ኬላዎችን ማለፍ፥ አይናቸዉን በሚያጉረጠርጡ፥ ጠመንጃዎቻቸዉን በወደሩ ወታደሮች መፈተሽ ግድ አለበት።

ከከተማይቱ መሐል ግን ሁሉም ነገር አማን ነዉ።እነዚያ አስፈሪ ወታደሮች አይታዩም።ሱቆች፥ሆቴሎች፥ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሁሉም ደንበኛ-ባለጉዳዮችን ያስተናግዳሉ።አንዲት የከተማይቱ ነዋሪ እንደሚሉት ግን የነዋሪዎችዋ ዉስጣዊ ስሜት ከከተማይቱ ዉጪያዊ ገፅታ ጋር ይቃረናል።

NO FLASH Nigeria Anschlag von Boko Haram in Maiduguri


«ቢሮ ተቀምጠሕ እንኳን ሐሳብሕ ሌላ ሥፍራ ነዉ።በተለይ የቦምብ ፍንዳታ ከተሰማ፥ መኖሪያ አካባቢዬ ይሆን የፈነዳዉ፥ ትምሕር ቤት ያሉ ልጆችስ እንዴት ይሆኑ ይሆን? እያልክ ታስባለሕ። ወደ ቤትሕ፥ ወይም ልጆች ወዳሉበት ስትጣደፍ ደግሞ እዚሕም-እዚያም አደጋ ያጋጥምሐል።እና ሁሉም ሰዉ በስጋት ነዉ-የሚኖረዉ።»

ማይዱንጉሪ የቦርኖ ጠቅላይ ግዛት ርዕሠ-ከተማ ናት።ኒጀርን፥ ቻድንና ካሜሩንን ከናጄሪያ ጋር ታዋስናለች።ሥልታዊናት።ደማቅ የንግድ ከተማ።በቅርቡ ግን ሕዝቧን ሥጋት፥ ምጣኔ ሐብቷን ዉደቀት አጥልተዉባቸዋል።ምክያት-ቡኮ ሐራም።በሐዉስኛ-ፍቺዉ «ዘመናይ ሥልጠና ሐጢያት፥ ሐራም ነዉ እንደማለት ነዉ።

ቡድኑ ከ2010 ማብቂያ -ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሰሜን ናጄሪያ የሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎችን በቦም አጋይቷል።ማይዱጉሪም በየዕለቱ በሚባል ደረጃ እየተሸበረች ነዉ።ፖሊስ ጣቢያና የጦር ሠፈሮች በተደጋጋሚ ጋይተዋል።መጠጥ ቤቶች፥ፖለቲከኞች፥ አብያተ-ክርስቲያናት፥ መሳጂዶችም እንዲሁ።

የቡድኑ መሪ መሐመድ የሱፍ ዘመናዊዉን ሥርዓት የሚፃረር ፍልስፍናዉን መስበክ፥ ወጣቶችን ማሰባሰብ የጀመረዉ በ2002 ነዉ።ከነዚያ ወጣቶች አንዱ፥ እራሱን ሙጃሒድ ነዉ ሚለዉ።

«በቢኤ ዲግሪ ተመርቄያለሁ።ግን የትምሕርት መረጃዬን በሙሉ አቃጥዬ፥ የመምሕር መሐመድ የሱፍን አስተምሕሮት ተቀብያለሁ።ከዚያ በፊት ዩኒቨርስቲ ከጨረስኩ በሕዋላ ሥራ አላገኘሁም።እርሻ ለመጀመር አስቤ ነበር።መሬት ለማልማት እርዳታ እንደሚሰጠን ቃል ተገብቶልን ነበር።ሰባት፥ ስምት ወር ጠበቅን ምንም የተሰጠን ርዳታ የለም።በዚሕች ሐገር ሐቅና ርትዕት ኖሮ ቢኖር ኖሮ ይሕ በደል አይደርስብንም ነበር።»

የቦኮ ሐራም ሸማቂዎች ከሁለት አመት በፊት ማይዱጉሪ ተራራ ላይ ከናጀሪያ ጦር ጋር በገጠሙት ዉጊያ ስምንት መቶ ሰዎች ተገድለዋል።የቡድኑ መሪም ቆለዉ ከተማረኩ በሕዋላ ሞተዋል።ከዚያ በሕዋላ ቡድኑ ባደረሰዉ ጥቃት ከሁለት መቶ ሐምሳ በላይ ሰዎች መግደሉን አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ዘግቧል።

የናጄሪያ ፀጥታ አስከባሪዎች ባንፃሩ በተጠርጣሪ የቡድኑ አባላት ላይ ከፍተኛ በደል ያደርሳሉ።ባለፈዉ ሚያዚያ የተመረጡት የቦርኖ አገረገዢ ካሺም ሼቱማ ግን የድርድር ሐሳብ አቅርበዋል።

«ቦኮ ሐራም የፖለቲካ ችግር ነዉ።ፖለቲካዊ ችግር ደግሞ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል። በወታደራዊዉ ዘመቻ ብቻ ካተኮርን ተጨባጭ ዉጤት በማይገኝበት የረጅም ጊዜ ዉጊያ እንገባለን።ከነሱ ጋር የምንደራደረዉ ግን የበላይነቱን እንደያዝ እንጂ ደካማ መሠረት ላይ ሆነን አይደለም።»

Anschlag auf ein UN Büro in Abuja Nigeria

በአቡጃ የተመድ ቢሮ ፍንዳታም ቦኮ ሐራም ይጠረጠራል

ሐሳቡን-ቡድኑ አልተቀበለዉም።እንዲያዉም አገረገዢዉ ሥልጣን እንዲለቁ አስጠንቅቋል።አንዳድ ቦኮሐራም አባላት ከአል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለዉ የሚባለዉ የሶማሊያዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብ እንዳሰለጠናቸዉ በሚስጥር ይናገራሉ።ይሕ ታዛቢዎች እንደሚሉት በሥራ እጦትና በድሕነት የሚበሳጨዉ ናይጄሪያዊ ወጣት ቡድኑን እንዲቀየጥ እንደ ዉጪዊ ተፅዕኖ የሚታይ ነዉ።

ቶማስ መሽ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic