ቦኮ ሃራም ላይ ያነጣጠረዉ የፓሪሱ ጉባኤ | አፍሪቃ | DW | 17.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ቦኮ ሃራም ላይ ያነጣጠረዉ የፓሪሱ ጉባኤ

ፈረንሳይ ፓሪስ ላይ የተደረገዉ ፀረ- ሽብር ጉባኤ፤በተለይ በናይጀርያ በሚንቀሳቀሰዉ አሸባሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኮ ሃራም ላይ ማነጣጠሩ ተመለከተ። የናይጀርያዉን አሸባሪ ቡድን ለመዉጋት፤ በተሻለና በተቀናጀ መንገድ የትብብር ሥራ ወሳኝ መሆኑም ዛሬ ፓሪስ ላይ በተካሄደዉ የደኅንነት ጉባኤ ላይ ተመልክቶአል።

የናይጀርያዉ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ፤ ሀገራቸዉ አሸባሪነትን ለመዋጋት በምታደርገዉ ትግል ላይ ርዳታ እንደምትሻ ተናግረዋል። በናይጀርያ የሚንቀሳቀሰዉ ቦኮ ሃራም የተሰኘዉ እስላማዊ ፅንፈኛ ቡድን፤ በተለይ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እጅግ ጭካኔ የተሞላዉ፤ዘግናኝ ጥቃት በመጣል ላይ መሆኑ ይታወቃል። ዛሬ ቅዳሜ ፓሪስ ላይ በተካሄደዉ ፀረ- ሽብር ጉባኤ ላይ ፤ የናይጀርያዉን ፕሬዚዳንት ጆናታን እና የአካባቢዉ ሀገራት መሪዎች፤ቦኮ ሃራምፅንፈኛ ደፈጣ ተዋጊ ቡድንን ለመዉጋት በቁርጠኝነት መነሳታቸዉ ተዘግቦአል። በጉባኤዉ ላይ የቻድ፤ የካሜሩን የኒጀር፤ የቤኒን ፕሬዚዳንቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ ተወካዮችም በጉባኤዉ ላይ ተገኝተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የናይጀርያዉ አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራም ጎረቤት ካሜሩን ውስጥ በሚገኝ አንድ የቻይና ፋብሪካ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ሁለት ሰዎችን መግደሉ

ተዘግቦአል።ሌሎች 10 ሰዎችም ከሰሜን ካሜሩን በቦኮ ሃራም ተጠልፈው መወሰዳቸውን የአካባቢው አገረ-ገዢ አውጉስቲን አዋ ፎንካ ይፋ አድርገዋል። ሟቾቹ አንድ ቻይናዊ የመንገድ ግንባታ ሠራተኛና ካሜሩናዊ ወታደር መሆናቸውም ተገልጿል። ይህ ጥቃቱ በካሜሩን ሲደርስ ፤ፕሬዚዳንት ፖል ቢያ በፈረንሣይ-አፍሪቃ የደኅንነት ጉባዔ ላይ ለመምከር ፓሪስ እንደሚገኙ ይታወቃል። የናይጀርያዉ አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራም ባለፈዉ ወር ከ 200 በላይ ልጃገረዶችን ከትምህርት ቤት አፍኖ መዉሰዱና፤ እነዚህ በ 15 እና 18 ዓመት የዕድሜ ዕርከን የሚገኙትን ልጃገረዶች ገበያ አውጥቶ በአደባባይ እንደሚሸጣቸው ይፋ ባደረገው ቪዲዮ ላይ መዛቱ ይታወቃል።

አክራሪው ቡድን ቦኮ ሃራም፤ ሚያዝያ 6 ቀን 2006 ዓ ም፤ 276 ተማሪዎችን በአመዛኙ ክርስቲያን ተማሪዎችን ጠልፎ ከወሰደ በኋላ አንዳንዶቹ ልጃገረዶች ከጠላፊዎቹ እጅ አምልጠው ሲመለሱ ከ 200 በላይ የሚሆኑት፣ አሁንም የት እንደሚገኙ አልታወቀም። የናይጀሪያ ፖሊስ ልጃገረዶቹ የሚገኙበትን ቦታ ለሚጠቁም 300,000 ዶላር ስጦታ ለማቅረብ ቃል በመግባት የጠፉትን ሴት ተማሪዎች በመፈለግ ላይ መሆኑን ገልጾአል።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ