ቦን፥ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ሰልፍ ወጡ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 04.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ቦን፥ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ሰልፍ ወጡ

በሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች መንግሥታት የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመግታት ርምጃዎችን መውሰድ እንዲጀምሩ በጀርመን ቦን ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ ጠየቁ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾቹ «ከባቢ አየርን ጠብቁ የድንጋይ ከሰል ቊፋሮን አቊሙ» ሲሉም መፈክር አስተጋብተዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች መንግሥታት የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመግታት ርምጃዎችን መውሰድ እንዲጀምሩ በጀርመን ቦን ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ ጠየቁ፡፡ ሰልፈኞቹ መንግስታት በድንጋይ ከሰል የሚሠሩ የኃይል ማመንጫዎችን በፍጥነት ከአገልግሎት ውጭ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አዘጋጆቹ ቊጥራቸው 25 ሺህ ይደርሳል ያሏቸው ሰልፈኞች ድምጻቸውን ያሰሙት በጀርመኗ ቦን ከተማ የአየር ጸባይ ለውጥን አስመልክቶ ከሚካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሁለት ቀን አስቀድሞ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾቹ «ከባቢ አየርን ጠብቁ የድንጋይ ከሰል ቊፋሮን አቊሙ» የሚለውን ዘመቻቸውን በዘፈን እና ከበሮዎችን በመምታት አሰምተዋል፡፡ የ100 ሲቪል ማኅብረሰብ ተቋማት ጥምረት ከሰልፉ በፊት ባወጡት መግለጫ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት «በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ነው» ብለዋል፡፡ «እየጨመረ በመጣው የባሕር ወለል ምክንያት በደሴት ላይ ያሉ ሃገራት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል» ሲሉም በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡ «የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ከባህር የሚገኝ ነዳጅ እና የድንይ ከሰልን በፍጥነት መጠቀም ማስቀረት ይኖርብናል» ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት የሚካሄደው 196 ሃገራት የሚሳተፉበት ስብሰባ እና ድርድር ከሰኞ ጥቅምት 27 ጀምሮ ለ12 ቀናት ይካሄዳል፡፡

 

የተቃውሞ ሰልፉ አደራጆች 25.000 ሰው ለተቃውሞ ሰልፍ መውጣቱን ገልጠዋል። ፖሊስ 11.000 ግድም ሰልፈኞች ነበሩ ብሏል። በሰልፉ ላይ ኦክስፋም፤ ግሪን ፒስ፤ ዳቦ ለዓለም፤ የቤተክርስትያን ተራድኦ ድርጅት ሚዜሮርም እንዲሁም አረንጓዴ ፓርቲ እና ግራዎቹ ፓርቲ ተካፋይ ሆነዋል።

ሰኞ በይፋ ከሚከፈተው ዩኤን ካምፑስ አዲሱ የባቡር ማቆሚያ አንስቶ እስከ ዶይቸ ቬለ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ህንጻ ድረስ በርካታ ፖሊሶች እና የፖሊስ ተሽከርካሪዎች ይታያሉ። መንገዶቹም በማገጃ ግዙፍ የሲሚንቶ ድንጋዮች ተዘግተዋል። የከባቢ አየር ጉባዔው የፊታችን ሰኞ ተከፍቶ እስከ ኅዳር 8 ድረስ ይዘልቃል። የንዑሷ ደሴት ፊጂ ጠቅላይ ሚንሥትር ፍራንክ ባይኒማራማ በሚመራው ጉባዔ እስከ 25,000 ታዳሚያን ተብሎ ይጠበቃል።

ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ