ብዙ የሚቀረው ወባን ማጥፋት ጥረት | ጤና እና አካባቢ | DW | 01.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ብዙ የሚቀረው ወባን ማጥፋት ጥረት

ወባ ዛሬም ዕድሜ ሳትለይ መከላከል ሲቻል የሰዉ ሕይወት ከሚቀጥፉ ግንባር ቀደም በሽታዎች ተርታ አልወጣችም። የዓለም የጤና ድርጅት በወባ በሽታ ላይ የሚያደርገውን የመከላከል እና የመቆጣጠር ርምጃ ለማጠናከር እንደሚሻ ነው ዘንድሮም ለዓለም አሳውቋው። ድርጅቱ ለዚህ እንዲረዳውም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:01

ወባን ጨርሶ ማጥፋቱ ጊዜ የሚጠይቅ ይመስላል፤

ወባ የምታደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግም ወደ ኅብረተሰቡ ዝቅ ብሎ ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ በድርጅቱ የወባ ማጥፊያ ትብብር በምሕፃሩ RBM ተብሎ የሚታወቀው ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ከሰተ አድማሱ እንዲህ መግለጣቸውንም ያመለክታል።

«ወባን ለመዋጋት የኅብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ወባን ለመከላከል የሚሠራውን ሥራ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ሊይዘው ይገባል።  ወባን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርም ሆነ ለማጥፋት የሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ወባን ከነጭራሹ ለማጥፋትም ከታች ያለውን ኅብረተሰብ ያሳተፈ እንቅስቃሴ የግድ መኖር አለበት፤ ይህ ደግሞ ዘመቻው በኅብረተሰቡ ባለቤትነት መያዝ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብም ሆነ ግለሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል።»

በኢትዮጵያዊዉ የሚመራው ዓለም አቀፉ ወባን የማጥፊያ ትብብር እንቅስቃሴ ከጀመረ ሁለት አስርት ዓመታት አስቆጥሯል። እንደ እቅዱም በጎርጎሪዮሳዊው 2010ዓ,ም ወባ በሰዎች ጤናም ሆነ ሕይወት ላይ ታስከትል የነበረውን ጫና ቢያንስ በግማሽ የመቀነስ ነበር። እንደዓለም የጤና ድርጅት መረጃ በጎርጎሪዮሳዊው 2016ዓ,ም 216 ሚሊየን ሰዎች በመላው ዓለም በወባ በሽታ ተይዘዋል። 445ሺህዎች ደግሞ ከወባ ጋር በተገናኘ የጤና ችግር አልቀዋል። ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2017 ድርጅቱ ያወጣዉ ዓመታዊ ዘገባ ደግሞ ምንም እንኳን ከዚያ ቀድመው በነበሩ ዓመታት ወባን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ስኬት ቢያስመዘግብም በተጠቀሰው ዓመት ግን መሻሻሎቹ ለውጥ እንዳልታየባቸው አመልክቷል።

በዚህ ምክንያትም ስኬቶቹ ተቀልብሰው የኋሊት ጉዞ እንዳይጀምሩ ስጋቱንም ይፋ አድርጓል። የተገኙት ስኬቶች እንዳይቀጥሉ እንቅፋት ሆነው ከቀረቡ ጉዳዮችም ዋነኛዉ የበጀት ጉዳይ መሆኑንም የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል። በዚሁ ምክንያትም በጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም በወባ በሽታ የሚጠቃውን ወገን ቁጥር በ40 በመቶ ለመቀነስ የያዘውን ዕቅድም ከግብ የማድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑንም አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ይመስላል ወባን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ብሎታል። ይህም ሆኖ ግን ሃገራት በየበኩላቸው ወባ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ ማጠናከራቸውን እየገለፁ ነው። ጎረቤት ዩጋንዳ በቅርቡ በወባ የሚያዝ እንዳይኖር ለማድረግ ጥረቷን ማጠናከሯን አስታውቃለች። በወባ የሚጠቁት አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ይህን በሽታ ለመከላከል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ከለጋሾች በሚገኝ ገንዘብ  የሚደረገፍ ነው። ከሳምንታት በፊት በለንደን የተካሄደው በወባ የሚጠቁ ሃገራት ጉባኤ በበሽታው ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ያጠናክራል ያሉትን የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የእንግሊዙን ልዑል ቻርለስ እና የማይክሮ ሶፍት መሥራች ቢል ጌትስ የተገኙበት ይህ ጉባኤም 3,8 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በዚሁ ዘርፍ ላይ ለሚደረግ ምርምር ፈጠራ እና ወባን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማቅረብ እንዲቻል እንደሚለግሱ ተናግረዋል። ቢል ጌትስ በወቅቱ ተገቢዉ የገንዘብ ድጋፍ ካልቀረበ በቀር ወባ የምትገድለው የሰው ቁጥር ዳግምከፍ ሊል ይችላል የሚችል ስጋታቸውን አሰምተዋል።

«በርካታ መንግሥታት፣ የግል ዘርፉ እና የዓለም መሪዎች በተገኙበት ዛሬ የተገባው ቃል ፤ ምንም እንኳን ከፍተኛ ተግዳሮች ቢኖርም የኃይል ሚዛኑን በወባ ላይ እንደምንገለብጠው ያለኝን እምነት አድሶልኛል። የእኛ ተቋም በመጪዉ አምስት ዓመት የጋራ ብልፅግናው ሃገራት ላይ የተጫነውን የወባ ችግር የማስወገድ ጥረት ለማሳካት እና ወባን ፈፅሞ ለማጥፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ወደ ቦታው ለመመለስ ተጨማሪ ቢሊየኖች የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብቷል።» 

ኬንያ እና ፓኪስታንን ጨምሮ አብዛኞቹ የቀድሞ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ሃገራት ወባ ክፉኛ የምታጠቃቸው እንደሆኑ ነው የተገለፀው።

ለ17ኛ ጊዜ በሀገር ደረጃ የወባ ቀንን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሃዋሳ ከተማ ያሰበችው ኢትዮጵያ ካለፉት አምስት ዓመት ወዲህ በወባ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም እየቀነሰ መምጣቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገፁ ላይ የወጣው ሰንጠረዥ ያሳያል። በዚሁ መሠረትም የዛሬ አምስት ዓመት 1451 ሰዎችን የገደለው ወባ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 356 ሰዎች ብቻ በበሽታው መሞታቸውን ጠቅሷል። ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን በድምፅ ከሰጡት አንዱ የራያ ቆቦ ነዋሪ እንደሚሉት ግን ዛሬም ወባ በአካባቢያቸው ገዳይ በሽታነቷ አንዳለ ነው። አንዳንዶች ደግሞ በአካባቢያቸው የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር የማከፋፈሉ ጥረት መልካም እንደሆነ በመግለፅ ሕክምና የማዳረሱ ሂደት ገና ብዙ እንደሚቀረው። ጠቁመዋል።

የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ላለፉት 14 ዓመታት ወባ በወረርሽኝ ደረጃ በሀገሪቱ አልተከሰተም። ከ2004ዓ,ም አንስቶም የወባ ታማሚዎች ቁጥር በ50 በመቶ ቀንሷል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ በመልክዓ ምድር እና የአየር ጠባይ ሁኔታ ምክንያት 75 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ ትንኝ መራቢያነት እና ለበሽታው ስርጭት አመቺ መሆኑን ነው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያመለከተው። በዚህ ምክንያትም 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች