ብርቱው አውሎ ንፋስ ወደ ፍሎሪዳ እየገሰገሰ ነው | ዓለም | DW | 09.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ብርቱው አውሎ ንፋስ ወደ ፍሎሪዳ እየገሰገሰ ነው

ወደ አሜሪካዋ የፍሎሪዳ ግዛት የሚገሰግሰው ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ንፋስ የኩባን ሰሜናዊ የባሕር ወደብ አካባቢ መታ። ሔሪኬን ኢርማ የሚል ሥያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋስ በካሪቢያን ደሴቶች 22 ሰዎች ገድሏል።

ወደ አሜሪካዋ የፍሎሪዳ ግዛት የሚገሰግሰው ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ንፋስ የኩባን ሰሜናዊ የባሕር ወደብ አካባቢ መታ። ሔሪኬን ኢርማ የሚል ሥያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋስ በካሪቢያን ደሴቶች 22 ሰዎች ገድሏል። ከኩባ የባሕር ዳርቻዎች ሲደርስ ኃይሉ የተቀዛቀዘው አውሎ ንፋስ ዛሬ ማለዳ በሰዓት 215 ኪ.ሜትር ይጋልብ እንደነበር የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአውሎ ንፋስ ማዕከል (NHC) አትቷል።  

ከኩባ የባሕር ዳርቻዎች በራቀ ቁጥር ኃይሉ እንደሚጨምር የገለጠው ማዕከሉ ነገ እሁድ ወደ ፍሎሪዳ እንደሚደርስ አስጠንቅቋል። ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ከተነሱት አውሎ ንፋሶች ሁሉ ኃይለኛው ነው የተባለው ኢርማ በፈጣን ንፋስ እና ብርቱ የጎርፍ መጥለቅለቅ የከፋ ውድመት ያስከትላል የሚል ሥጋት አጭሯል።

ከፍሎሪዳ ግዛት ነዋሪዎች አራት እጁ ማለትም 5.6 ሚሊዮን ሰዎች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። "ይህ ግዛታችን ዐይቶት የማያውቅ አደገኛ አውሎ ንፋስ ነው" ያሉት የፍሎሪዳ ግዛት አስተዳዳሪ ሪክ ስኮት ነዋሪዎች በጊዜ ከቀያቸው ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል። የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያዎች በሰዓት 260 ኪ.ሜትር የሚጋልብ ነውጠኛ አውሎ ንፋስ ይፈጥራል ያሉት ኢርማ ፍሎሪዳን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያዳርሳል ተብሎለታል። ኃያሉ አውሎ ንፋ ከመድረሱ በፊት ከፍሎሪዳ በአስቸኳይ እንዲወጡ የታዘዙት ነዋሪዎች ቊጥር 6.3 ሚሊዮን መድረሱን ዘገባዎች ያመለክታሉ። 

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተዛማጅ ዘገባዎች