ብራዚል በዕድል ቺሊን ጥላ ወደ ሩብ ፍፃሜ | ዓለም | DW | 28.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ብራዚል በዕድል ቺሊን ጥላ ወደ ሩብ ፍፃሜ

ብራዚል ላይ እየተካሄደ ባለዉ የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ፤ ቅዳሜ ምሽት የደቡብ አሜሪካ አራት ሀገራት ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች የሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ዉድድር ተጀምሯል። ብራዚል ከቺሊ፤ ኮሎምቢያ ከዑሯጓይ። ብራዚልና ቺሊ ባካሄዱት ግጥምያ በብራዚል 4 - 3 በሆነ ዉጤት ጨዋታዉ ተጠናቆአል። ኮሎምቢያ ዑሯጓይን 2-0 አሸንፋለች

ሁለቱ ቡድኖች ዘጠና ደቂቃዉን ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ነጥብ ተለያይተዉ ተጨማሪ 30 ደቂቃዉን ግጥምያ በአቻ ዉጤት ነበር የተለያዩት። ሁለቱ ቡድኖች በመጨረሻ በተሰጣቸዉ ፍፁም ቅጣት ምት ነበር፤ በብራዚል 4- 3 በሆነ ዉጤት ቺሊን በዕድል ጥላ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፈችዉ። ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ የተጋጠሙት ኮሎምቢያ ዑሯጓይ ጥሩ ፍልምያን አሳይተዉ በኮሎምቢያ 2 - 0 አሸናፊነት ጨዋታዉ ተጠናቆአል።

በደቡብ አሜሪካ የሚገኙት ሀገራት በዘንድሮዉ የእግር ኳስ ግጥምያ፤ በጨዋታ ጥበብ ጠንክረዉ ብቻ ሳይሆን የተገኙት ከየትኛዉም ሀገራት በበለጠ በመጋጠምያ ስቴዲየም ዉስጥ በርካታ ደጋፊዎችንም በመያዛቸዉ ለየት አድርጓቸዋል። በአስተናጋጅ ሀገር ብራዚል፣ ባለፉት 2 ሳምንታት፤ ከዓለም ዙሪያ በተወከሉ ባጠቃላይ የ32 ሃገራት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የሰነበተው የመጀመሪያ ዙር ውድድር፣ ተጠናቆ፤ ዛሬ ቀጣዩ ጥሎ ማለፍ ዉድድር ይቀጥላል። ናይጀርያ እና አልጀርያ በመካሄድ ላይ ባለዉ የዓለም እግር ኳስ ግጥምያ፤ ከአፍሪቃ ያለፉ ብቸኛ የአህጉሪቱ ሀገሮች ሲሆኑ፤ የፊታችን ሰኞ አልጀርያ እና ጀርመን የሚያደርጉት ግጥምያ በተለይ እዚህ ጀርመን በጉጉት በመጠበቅ ላይ ነዉ።
በዘንድሮዉ የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያ፤ የዑሯጓዩ አጥቂ ሉዊስ ሱሬስ ላይ ከፍተኛ ቅጣት መጣሉ፤ በዓለም የእግር ኳስ ዉድድር ታሪክ የመጀመርያ የፊፋ ጠንካራ እርምጃ እንዲሆን አድርጎታል።

ለዑሯጓይ ብሄራዊ ቡድንና ለእንግሊዙ ሊቨርፑል የእግር ኳስ ቡድን፤ ታዋቂ ጎል አዳኝ የሆነዉ የዑሯጓዩ ተወላጅ ሉዊስ ሱዋሬስ፤ ዑሯጓይ ከኢጣልያ ጋር ባደረገችዉ ጨዋታ፤ የኢጣልያዉን ቡድን ተከላካይ ትከሻዉ ላይ በመንከሱና፣ ይህን ድርጊት ለሶስተኛ ግዜ በመፈፀሙ የዓለም የእግር ኳስ ፌደሬሽን «FIFA» ለአራት ወራት ከማንኛዉም ዓለማቀፍ የእግር ኳስ ግጥምያ አግዶታል። በተጨማሪ ሱዋሪስ፤ ወደ 112 ሽ ዶላር ቅጣትም እንዲከፍል ተወስኖበታአል። አሁን በብራዚል እየተካሄደ በሚገኘዉ የእግር ኳስ ግጥምያ ሱዋሪስ በማንኛዉም የብራዚል ስቴዲየም ገብቶ እንዳይከታተል ጭምርም ነዉ ዉሳኔዉ የተላለፈበት። ይህ ፍርድ የተጣለበት የግብ አዳኝ ሱዋሪስ በበኩሉ ወድያዉኑ ወደ ትዉልድ ሀገሩ ዑሯጓይ የተመለሰ ሲሆን፤ በዝያም በርካታ የሀገሪቱ ኳስ አፍቃሪዎች የጀግና አቀባበል እድርገዉለታል።


አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ