ብራስልስን ያናወጠው የፈንጂ ጥቃት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ብራስልስን ያናወጠው የፈንጂ ጥቃት

በቤልጅየም መዲና ብራስልስ በዓለም አቀፉ የአየር ማረፊያ እና በአንድ የከርሰ ምድር የከተማ ባቡር ጣቢያ በተጣሉ የፍንዳታ ጥቃቶች ቢያንስ 31 ሰዎች ተገድለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:14 ደቂቃ

ሽብር በብራስልስ

የቤልጂግ እና የአዉሮጳ ሕብረት ርዕሠ-ከተማ ብራሥልስን ያሸበረዉን የቦምብ ጥቃት የተለዩ ሐገራት መንግሥታት እና ባለሥልጣናት እያወገዙ፤ ከቤልጂግ ጎን መቆማቸዉን እያረጋገጡ፤ የጥንቃቄ እርምጃም እየወሰዱ ነዉ።ሐቫና-ኩባን በመጎብኘት ላይ እንዳሉ አደጋዉን የሰሙት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጥቃቱን አዉግዘዉ መስተዳድራቸዉ ለቤልጂግ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።በብራስልስ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ግን ቤልጅግ የሚገኙ አሜሪካዉያን ከያሉበት ሥፍራ እንዳይንቀሳቀሱ አሳስቧል።የቱርኩ ፕሬዝደንት ጠይብ ኤርዶኻን ጥቃቱ አንካራም ደረሰ ብራስልስ አኩል ነዉ ብለዋል።የሩሲያ ባለሥልጣናት ግን አደጋዉን የአዉሮጳ ሕብረት የተቃርኖ መርሕ ዉጤት ብለዉታል። የጀርመን፤ የፈረንሳይ፤ የብሪታንያ፤ የኔዘርላንድስ፤ የኢጣሊያና የሌሎችም የምዕራብ አዉሮጳ መሪዎች ጥቃቱን ሲያወግዙ የፀጥታ ቁጥጥርና ክትትሉን አጠናክረዋል።ዮርዳኖስ በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ወይዘሮ ፌደሪካ ሞግሄሪኒ «ለአዉሮጳ አሳዛኝ ቀን» ብለዉታል።

«ይሕ አካባቢ፤ ሶሪያም ሆነ ሌላ ሥፍራ በየዕለቱ የሚያዉቀዉ (ጥቃት) አዉሮጳና ርዕሠ-ከተማዋ ላይ በመድረሱ ዕለቱ ለአዉሮጳም በጣም አሳዛኝ ነዉ።ብራስልስ ዉስጥ ሥለደረሰዉ ጥቃት አሁንም ዝርዝር መረጃ እየጠበቅን ነዉ።ይሁንና እኛጋም ሆነ እዚሕ ያለዉ ስቃይ መሠረታዊ ምክንያት ተመሳሳይ መሆኑ ግልፅ ነዉ።እና በጥቃቱ ሰለቦች ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን የፈፀሙትን በማደኑም ሆነ ፅንፈኝነትንና ሁከትን በመከላከሉም በጋራ መቆም አለብን።»

ዛሬ ጠዋት ብራስል አዉሮፕላን ማረፊያ እና አንድ የምድር ዉስጥ የባቡር ጣቢያ ላይ በደረሰዉ ሰወስት የቦምብ ፍንዳታ ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸዉ ተረጋግጧል።በርካታ ቆስለዋል።የቤልጂግ ፀጥታ አስከባሪዎችና ባለሥልጣናት የደረሰዉን ጥፋት ገና እያጣሩ በመሆናቸዉ የሟች-ቁስለኛዉ ቁጥር መጨመሩ እንደማይቀር እየተነገረ ነዉ።የቤልጂግ መንግሥት የመሠረተዉ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚሽን ጉዳዩን እየተከታተለ ለሕዝብ እንደሚያሳዉቅ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሻርል ሚሼል አስታዉቀዋል«መንግሥት የመሠረተዉ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚሽን መረጃዎችን አጠናቅሮ ኋላ ላይ ያቀርባል።የአደጋዉ ሰለቦች ቤተ-ሰቦች መረጃ የሚያገኙበት የቀጥታ ስልክ ቁጥር አዘጋጅተናልም።ቁጥሩ 17771 ነዉ።ባሁኑ ሰዓት የተጎዱትና የሞቱንን ማግለሉ እየተጠናቀቀ ነዉ።ሥለሟችና ቁስለኞች ትክክለኛ ቁጥርና ማንነት ለመናገር ግን አሁንም ጊዜዉ ገና ነዉ።ምክንያቱም የ(ሟችና ቁስለኞች) ማንነት ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነዉና።ይሕ የቤልጂግ ዜጋ ላልሆኑ የጥቃቱ ሰለቦችም ተመሳሳይ ነዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከየኤምባሲዎቻቸዉ ጋር እየተገናኘ ነዉ።»

ለጥቃቱ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት የሚለዉ ቡድን ሐላፊነቱን ወስዷል።በጥቃቱ የተሳተፉ ሰዎችን ለመያዝ፤ለመከታተልና ሌላ ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል መላዋ ቤልጂግ በከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር ሥር ወድቃለች።የሐገሪቱ መንግሥት ዛሬ ማምሻዉን የሰወስት ቀን ብሔራዊ ሐዘን አዉጇል።

በዜቭንቴም አየር ማረፊያ ዛሬ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት በነጎዱ ሁለት ፈንጂዎች 16 ሰው ሲሞት፣ ከሰማንያ የሚበልጡም ቆስለዋል፣ የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እንዳስታወቀው። በብራስልስ ማዕከል በሚገኘው የሜልቢክ የከርሰ ምድር የከተማ ባቡር ጣቢያ የፈነዳው ሶስተኛው ፈንጂ 15 ሰዎች ገድሎ፣ 55 ሰዎችን ሲያቆስል፣ ከነዚህም 10 በጠና መቁሰላቸው ተሰምቶዋል። ባለፈው ህዳር ወር የ130 ሰዎችን ሕይወት ያጠፋውን የፓሪሱን ጥቃት ጥሎዋል ተብሎ የተጠረጠረው ሳሌህ አብደስላም ከተያዘ ከአራት ቀናት በኋላ ነው የደረሰው። የቤልጅየም መንግሥት የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አውጆዋል። ስለብራስልስ ጥቃት ወኪላችንን ገበያው ንጉሤን ስቱድዮ ከመግባታችን በፊት በስልክ አነጋግሬው ነበር።

ገበያው ንጉሤ
አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic