ብራስልስና የበጀት ቁጥጥሩ ስምምነት | ኤኮኖሚ | DW | 01.02.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ብራስልስና የበጀት ቁጥጥሩ ስምምነት

ብዙሃኑ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል መንግሥታት መሪዎች ብራስልስ ላይ ባካሄዱት ጉባዔ ከትናንት በስቲያ ጥብቅ የበጀት ቁጥጥርን በሚያሰፍን አንድ ውል ለመስማማት በቅተው ነበር።

ብዙሃኑ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል መንግሥታት መሪዎች ብራስልስ ላይ ባካሄዱት ጉባዔ ከትናንት በስቲያ ጥብቅ የበጀት ቁጥጥርን በሚያሰፍን አንድ ውል ለመስማማት በቅተው ነበር። ከ 27ቱ የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት መካከል ስምምነቱን ያልደገፉት ብሪታኒያና ቼክ ሬፑብሊክ ብቻ ናቸው። በስምምነቱ መሠረት ዓባል ሃገራቱ ዓመታዊ የበጀት ኪሣቸውና ብሄራዊ ዕዳቸው መጠን እንዳያልፍ ገደብ ማበጀት አለባቸው። አለበለዚያ ጥብቅ መቀጮ ይጠብቃቸዋል። ለነገሩ ግዴታው በየአገሩ አሣሪ ሕግ ሆኖ እንዲቀመጥም ነበር በጀርመን የተፈለገው። ግን በዚህ ስምምነት አልተገኘም።

የስምምነቱን ይዘት በተጨባጭ ግልጽ ለማድረግ የበጀት ኪሣራው ከቀድሞው የማስትሪሽት መስፈርት ከሶሥት በመቶ በልጦ የተገኘ ዓባል አገር በቀጥታ መቀጮ የሚጣልበት ይሆናል። ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱ 0,1 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ወደ ብራስልስ ማስተላለፍ ይገደዳል ማለት ነው። መቀጮውን ሊያስቆም የሚችለው ሁለት-ሶሥተኛ የአውሮፓ ሕብረት የፊናንስ ሚኒስትሮች ብዙሃን ድምጽ ብቻ ነው ተብሏል። ጀርመን ድንቡን ይበልጥ ጥብቅና አስተማማኝ ለማድረግ ግዴታውን የሚመለከት አንቀጽ በያንዳንዱ አገር ሕገ-መንግሥት ውስጥ እንዲሰፍር ያቀረበችው ሃሣብ ተቀባይነት አለማግኘቱ ውሉ ከቀድሞው ይበልጥ ፍቱን መሆን መቻሉን ጥቂትም ቢሆን አጠያያቂ ማድረጉ አይቀርም። ይህም ሆኖ ግን የሕብረቱ ሸንጎ ፕሬዚደንት ሄርማን-ፋን-ሮምፑይ ስምምነቱ ምንም እንኳ ብሪታኒያን ጠቅሎ ባይሰፍንና ቀውሱን ለማስወገድ ብቻውን በቂ ባይሆንም ትልቅ ክብደት ነው የሰጡት።

“ውሉ የተፈለገው የበለጠ ሃላፊነትንና የተሻለ ቁጥጥርን ለማስፈን ነው። እና ስምምነቱን የሚፈርሙ ሃገራት ሁሉ ዕዳውን መጥኖ ለመያዝ ወይም በሕግና ከዚያው በተጣጣመ ደረጃ አንድ አሣሪ ደምብ ለማስፈር ግዴታ ይገባሉ። እርግጥ የፊናንስ መረጋጋት ብቻውን ከኤኮኖሚው ቀውስ ለመላቀቅ በቂ እንዳልሆነ እናውቃለን። ስለዚህም በተለይ በኤኮኖሚ ዕድገትና በስራ መስኮች ፈጠራ ረገድ የበለጠ ጥረት ማድረጋችን ግድ ነው የሚሆነው”

በነገራችን ላይ ቀውስን ለመቋቋም የሚረዳ ገንዘብ ለማግኘት በባንኮች የገንዘብ ልውውጥ-ትራንስአክሺን ላይ ግብር ለመጣል ቀርቦ በነበረው በፈረንሣይ በጣሙን በሚደገፈውና እንግሊዝ በአንጻሩ አጥብቃ በምትቃወመው ሃሣብ ላይ ግን በጉባዔው ላይ ውይይቱ ቀጥሎ ቢታይም ከአንድ ማሰሪያ ላይ አልተደረሰም። በሌላ በኩል የኤኮኖሚ ዕድገትና የስራ አጥ ቅነሣው ጥረት ከተነሣ በዚህ በጉባዔው ዓቢይ ርዕስ ላይ የተደረገው ውይይት እምብዛም ትልቅ ተሥፋ የሚሰጥ አልነበረም። እያደገ የሚሄደውን ስራ አጥነት ለመግታት ባለው ውጥን ዕድገትን ከቁጠባ ጋር አጣምሮ ለማራመድ ነው የሚፈለገው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ነገሮች ጠበብት እንደሚናገሩት እርስበርሳቸው አይጣጣሙም።

በመሠረቱ አሁን በብዙዎቹ የሕብረቱ ዓባል ሃገራት ካለው ከባድ ሁኔታ አንጻር የዕድገት ዕርምጃዎች በተቻለ መጠን ወጪን የሚጠይቁ መሆን የለባቸውም። ሕብረቱ የሚሰጠውን ማራመጃ ገንዘብ ወይም ድጎማ አብቃቅቶ በአግባብ መጠቀሙ ነው አማራጭ ሆኖ የሚታየው። በሌላ አነጋገር በቀውሱ መጀመሪያ ወቅት የነበረውን ያህል ገንዘብ ዛሬ ሰፊ ለሆነ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕርምጃ ለማቅረብ አይቻልም። አቅሙ ወይም ፍላጎቱ የለም። ያም ሆነ ይህ የአውሮፓው ሕብረት ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ በበኩላቸው መዋቅራዊ ለውጦችን በማካሄድ ችግሩን ለመቋቋም ይቻላል ባይ ናቸው።

“በስብሰባችን ላይ ዛሬ በአብዛኛው በኤኮኖሚ ዕድገት፣ በስራ መስክ ፈጠራና በዋናነትም በወጣቶች ስራ አጥነት ላይ አተኩረናል። እርግጥ መለስተኛ መጠን ባላቸው ኩባንያዎችና ውስጣዊ ገበዮች ችግርም ላይ እንዲሁ! እና በጉዳዩ የተገኘው ትልቅ መልዕክት አንድ ወጡን ገበያ እንድናጠናክር የሚያሳስብ ነው። በተጨባጭ ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር የበለጠ ማድረግ ይኖርብናል። ግን ይህን ለማራመድ በቂ በጀት ባለመኖሩ የአውሮፓን የዕድገት አቅም በሚያንቀሳቅሱ መዋቅራዊ ለውጦች ላይ ማተኮሩ ግድ ነው የሚሆነው”
የመንግሥታቱ መሪዎች ከበጀት ቁጥጥሩ ሌላ የአውሮፓ የቀውስ ጊዜ መድህን አካል ከታቀደው ጊዜ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በፊታችን ሐምሌ ወር ገሃድ እንዲሆንም ተስማምተዋል። ይሄው ቀውስ የሚገጥመማቸውን የሕብረቱን ሃገራት የፊናንስ ሁኔታ ለማረጋጋት የሚያገለግል አካል በ 500 ሚሊያርድ ኤውሮ መጠን የማበደር አቅም የሚኖረው ነው። እርግጥ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም አስተዳዳሪ ክሪስቲን ላጋርድ ገንዘቡን በቂ አድርገው አይመለከቱትም። እና በተለይም በጥሩ የኤኮኖሚ ሁኔታ ላይ የምትገኘው ጀርመን የበለጠ ገንዘብ እንድታቀርብ ነበር ባለፈው ሰንበት በተዘዋዋሪም ቢሆን በዳቮሱ የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ላይ ያስገነዘቡት።
“ገና አቅም ያላቸው ሌሎች አገሮች አሉ። እነዚህ ደግሞ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ። እርግጥ ብዙ አይደሉም፤ አንድ ወይም ሁለት! እነዚህ ታዲያ ዕድገትን ለማጠናከር፣ ራሳቸውንና ኤውሮ-ዞንንም ለማገዝ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው”

በሌላ በኩል በከፍተኛ የበጀት ቀውስ እንደተወጠረች የቀጠለችው የግሪክ ጉዳይ በቀጥታ የጉባዔው አጀንዳ ርዕስ አለመሆኑ ሊያስገርም ቢችልም እርግጥ ጥላው በስብሰባው ላይ ማንዣበቡ ግን አልቀረም። ጉባዔው የሰጠው ይፋ ምክንያት የግሪክን ሁኔታ የሚከተለው ሶሥትዮሽ ቡድን የአውሮፓ ሕብረት፣ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ. ልዑካን ዘገባ እየተጠበቀ ነው የሚል ነው።

ከዚሁ ሌላ የግሪክ መንግሥት ከግል አበዳሪዎች፤ ከባንኮች ጋር የዕዳ ቅነሣ ስምምነት ለማድረግ የያዘው ድርድር ገና እንደቀጠለ መሆኑም በምክንያትነት ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ ግሪክ እስካሁን የቁጠባና የለውጥ ግዴታዋን በማሟላቱ ረገድ የሚገባውን ያህል እንዳልተራመደች በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። በዚሁ የተነሣም ጀርመን ባለፈው ሣምንት ግሪክ በበጀት ፖሊሲዋ ላይ ያላት የበላይነት ተነጥቆ በአንድ የኤውሮ-ዞን የቁጠባ ኮሜሣር ቁጥጥር ስር እንድትውል ሃሣብ አቅርባ ነበር። ሆኖም ሃሣቡ በብራስልሱ የመሪዎች ጉባዔ አኳያ ተከታይ ሳያገኝ ቀርቷል። ሃሣቡ በአዲሱ ጀርመናዊ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚደንት በማርቲን ሹልስ ፊት ሳይቀር ቅሬታን ነበር ያስከተለው።

“ሃሣቡ የሚያመለከተው በኤውሮ-ዞን ዓባል ሃገራት መካከል ያለውን ውጥረት ማርገብ ሲገባ ለዚህ አስተዋጽኦ የማያደርጉ ሰዎችን መኖራቸው ነው። እና የተባለው ችግሩን የሚያባባስ ሲሆን የምንፈልግውን ይጻረራል”

የሉክሰምቡርግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን አሰልቦርንም ሃሣቡ እንዳልጣማቸው በመጥቀስ ጀርመን የኤኮኖሚ ጥንካሬዋ በአውሮፓ አገሮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዳትረሳ ነው ያስገነዘቡት።

“ጀርመን የቀድሞ ቻንስለሯ ሄልሙት ሽሚት አንዴ እንዳሉት የኤኮኖሚ ጥንካሬዋ በአብዛኛው በአውሮፓ ሃገራት ዕዳ ላይ የተገነባ መሆኑን ምንጊዜም መዘንጋት የለባትም። ጀርመን ናት ይልቁን ከኤውሮ ተጠቃሚዋ”

ያም ሆነ ይህ ግሪክን ከበጀት ቀውሷ የማላቀቁ ጥረት ለአውሮፓ ሕብረት ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል። አለበለዚያ የኤውሮ-ዞን የመሸርሸር አደጋ እየጨመረ እንዳይሄድ የሚያሰጋ ነው። እንደሚታወቀው ግሪክን ለማዳን እስካሁን የተደረገው ጥረት ሁሉ ፍሬ አልሰጠም። ግን ይህ አውሮፓ የያዘችው የመፍትሄ ስልት የተሳሳተ ነው ማለት አይደለም። እርግጥ ተጨማሪ ገንዘብ በማቅረብ ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም። ለነገሩ ግሪክ ገንዘቡን እንድታገኝ ለውጦችን የማካሄድ ግዴታም ተጥሎባታል። እነዚህ ለውጦች ደግሞ ግሪክን ጤናማ አቅጣጫ እንደሚያስይዟት ነው የሚታመነው። ግን ያሳዝናል፤ ለውጦቹን በማካሄዱ በኩል እስካሁን የተፈለገው ዕርምጃ አልተረገም። ለዚሁ አንዱ ምክንያትም ጠንካራው ግዴታ በግሪክ ዕድገትን አላላውስ ያለ መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻር ታዲያ እንዴት ከቀውሱ መላቀቅ ይቻላል? የጀርመን ታላቅ መድህን ድርጅት የአሊያንስ የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ሚሻኤል ሃይዘ እንዲህ ይላሉ።

“አዎን፤ ግሪክ ውስጥ ጠንካራ የኤኮኖሚ ቀውስ ነው ያለው። ከተጠበቀው በላይ እየጠነከረም መጥቷል። ይህም ከበጀት ቁጠባው ግብ ላይ እንዳይደረስ ሊያደርግ የሚችል ነው። ብሄራዊውን የበጀት ኪሣራ ዝቅ ማድረጉ ከታቀደው በታች ሆን ይቀራል። ይህ እንግዲህ የበጀት ኪሣራው ውጤት ነው። በሌላ በኩል ወጪን በሰፊው መቀነሱና ግብርንም ይበልጥ ከፍ ማድረጉ እንዲቀጥል መወትወቱ ፍሬ እንደማይኖረው መታወቅ ይኖርበታል። በአንጻሩ ግን ሊጠየቅ የሚገባውና በረጅም ጊዜ ስሌት የማይቀር የሚሆነው መዋቅራዊ ለውጥ ማካሄዱ ነው”

ግን እዚህም ላይ ግሪክ የተፈለገውን ያህል ወደፊት አልተራመደችም። ለምሳሌ በመንግሥት ተቋማት ላይ ለውጥ ማካሄዱና ንብረትን ወደ ግል ዕጅ ማሻገሩ ወይም ግብር ስብሰባን ማጠናከሩ ሲታሰብ! ታዲያ ከዚህ አንጻር ግፊት መደረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ነው ጀርመናዊው የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ሚሻኤል ሃይዘ የሚናገሩት። በጥቅሉ የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች ብራስልስ ላይ የደረሱበት የበጀት ቁጠባ ስምምነት በፖለቲከኞች ትልቅ እመርታ ሆኖ ቢወደስም በኤኮኖሚ ጠበብትና በፊናንስ ገበዮች ዘንድ ግን በጥርጣሬ ዓይን ነው የታየው። እናም በወቅቱ ፍቱንነቱን ከመተንበይ ውጤቱን እያደር መታዘቡ ይመረጣል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic

 • ቀን 01.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13tnr
 • ቀን 01.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13tnr