ብሪክና ዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት | ኤኮኖሚ | DW | 17.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ብሪክና ዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ምዕራባውያን መንግሥታት የዓለምን የኤኮኖሚና የንግድ ሂደት ለብቻቸው የሚዘውሩበት ጊዜ ካለፈ ጥቂት ዓመታት ሆነዋል። በአሕጽሮት ብሪክ በመባል የሚጠሩት በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ ሃገራት፤ የብራዚል፣ የሩሢያ፣ የሕንድና የቻይና ተጽዕኖ እያደገና እየጠነከረ ሲሄድ ነው የሚታየው።

default

በተለይ ዓለምን የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ በወጠረበት በአሁኑ ወቅት የነዚህና መሰል ሃገራት ሚና ይበልጥ እየጨመረ መጥቷል። ቀደምቱ ስምንት የበለጸጉ መንግሥታት ለንደን ላይ ከጥቂት ወራት በፊት መድረካቸውን ሰፋ በማድረግ የቡድን-ሃያ ጉባዔ ማካሄዳቸውም ለዚህ ነበር። አዲስ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ስርዓት፤ እነዚሁኑ የጠቀለለ አዲስ የሃይል አቀነጃጀት ማስፈለጉም በየጊዜው የሚነገርለት ጉዳይ ነው። የብሪክ መንግሥታት መሪዎች ትናንት በሩሢያ-የካቴሪንቡርግ ተሰብስበው በመፍትሄ ፍለጋው ረገድ ተወያይተው ነበር።

ብሪክ በሚል አሕጽሮት የሚጠሩት አራት ሃገራት ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና በተፋጠነ ዕድገታቸው የተነሣ ይህን መለያ ያገኙት ከስድሥት ዓመታት በፊት ገደማ ነበር። ከአምሥት እስከ አሥር በመቶ የሚንሸራሸር የኤኮኖሚ ዕድገታቸው ከአውሮፓ ሁለት ከመቶ ሲነጻጸር ጠንካራ ሆኖ ቆይቷል። እነዚህ መንግሥታት ዛሬ ለዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት በሚደረገው ጥረትም ሆነ በዓለም ንግድ ጉዳይ ጥቅማቸውን ለማስከበር ግፊት የማድረግ የማይናቅ ሃይል አላቸው። ከዓለም ሕዝብ አርባ በመቶውን፤ ማለት 2,8 ሚሊያርዱን የሚጠቀልሉ ሲሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው በወቅቱ 33 ቢሊዮን ኤውሮ ገደማ ይደርሳል። ይህም 13 በመቶው ድርሻ መሆኑ ነው።

ብሪክ መንግሥታት በሚቀጥሉት 17 ዓመታት ውስጥ የበለጸገውን ዓለም አልፈው እንደሚሄዱና ቻይና ደግሞ በ 2050 ገደማ አሜሪካን በዓለም የኤኮኖሚ ልዕልና እንደምትተካ ነው የዘርፉ አዋቂዎች የሚናገሩት። ይህ መባሉ እርግጥ ያለ ምክንያት አይደለም። አራቱ መንግሥታት ሰፊ ሃብት ሲኖራቸው በቴክኖሎጂ ረገድም በፍጥነት የሚራመዱ ናቸው። ብራዚል ታላቅ የጥሬ ምርት አቅራቢ ስትሆን የእርሻ ሃብቷም ሰፊ ነው። ሩሢያ በተለይ በነዳጅ ዘይትና በተፈጥሮ ጋዝ ሃብት የካበተች ስትሆን በሶቪየቱ ዘመን የተዘረጋ ሰፊ የኢንዱስትሪ መዋቅርም አላት።
ሕንድ ደግሞ ምንም እንኳ ኢንዱስትሪ በማስፋፋቱ ረገድ በጅምሩ ላይ ናት ቢባልም በሌላ በኩል በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ በኩል ብዙ ተራምዳለች። አራተኛዋ ቻይና በምርትና በተሃድሶ የዓለምን ገበያ በሰፊው ከወረረች ሰንበት ብላለች። ደቡብ-ምሥራቅ እሢያይቱ አገር 800 ሚሊዮን ገበያተኛን የሚጠቀልል ግዙፍ የውስጥ ገበያም አላት። ይህ ራሱ ስለነዚህ ሃገራት የወደፊት ልዕልና ብዙ ይናገራል። በወቅቱ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ሃገራት በተከሰተው የኤኮኖሚ ዕድገት እጦት የተነሣ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በብሪክ አገሮች ላይ ማተኮራቸውም አልቀረም።

የነዚህ ሃገራት መሪዎች በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ድርጅት IMF ውስጥ የበለጠ ክብደት ለማግኘትና አዲስ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ስርዓት እንዲሰፍን በሚያደርጉት ጥረት የጋራ ግንባራቸውን ለማጠናከር ትናንት ሩሢያ ውስጥ የመጀመሪያ ጉባዔያቸውን አካሂደው ነበር። ሌሎች በዕድገት ላይ የሚገኙ የእሢያ መንግሥታት ተጠሪዎችም በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል። ጉባዔው የሃያላኑን የቡድን-ስምንት መንግሥታት ስብሰባ ያህል ዓለምአቀፍ ትኩረትን የሳበ ነበር። የሩሢያው ፕሬዚደንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በኡራል ላይ የሚገኘውን የጉባዔ ስፍራ የዓለም የፖለቲካ-ትርታ-ማዕከል ሲሉ ነው በስብስቡ ውስጥ እያደገ የሚሄደውን በራስ መተማመን ስሜት ያንጸባረቁት።

አራቱ መንግሥታት ከጉባዔው በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ በዓለም ኤኮኖሚ ስርዓት ላይ ጥልቅ የሆነ ለውጥ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት በተመለከተ ለኤኮኖሚ ተሃድሶ የሚበጅ ለውጥን ለማራመድ ቁርጠኛ መሆናቸውን ሲያስገነዝቡ አዳጊና ታዳጊ አገሮች በዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅቶች ድርጅቶች ውስጥ አብሮ የመወሰን የላቀ ድምጽ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስረግጠዋል። ከዚሁ ሌላ የድርጅቶቹ ከፍተኛ መሪዎችና አስተዳዳሪዎችም ግልጽና ፍትሃዊ በሆነ አመራረጥ መሰየም አለባቸው። የተረጋጋ፣ አስተማማኝና በዶላር ላይ ብቻ ጥገኛ ያልሆነ ዓለምአቀፍ የምንዛሪ ስርዓትም ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

መንግሥታቱ ዓለምአቀፉ ንግድና የውጭ መዋዕለ-ነዋይ የዓለም ኤኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ ታላቅ ሚና እንዳላቸው ዕምነታቸውን በመግለጽ ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ የብዙ ወገኑ የንግድ ስርዓት ተረጋግቶ እንዲቀጥል እንዲያደርግ፣ የገበያ እገዳ እንዲቀንስና በዶሃው የልማት አጀንዳ ረገድ አጠቃላይና ሚዛን የጠበቀ መፍትሄ እንዲገኝ ጥሪ ሰንዝረዋል። የመንግሥታቱ መሪዎች በኤነርጂው ዘርፍ አምራች፣ ተጠቃሚና መተላለፊያ ሃገራትን ጨምሮ ስጋትን ለመቀነስና የአቅርቦቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትብብርና ቅንብራቸውን እንደሚያጠናክሩም ቃል ገብተዋል።

የመንግሥታቱ የጋራ መግለጫ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ለውጥ እንዲደረግም የሚጠይቅ ነው። ብሪክ በኢንዱስትሪ ያደገችውን ደቡብ ኮሪያን፤ በኤነርጂ ሃብት የታደሉትን ካዛክስታንን የመሳሰሉ አገሮችን በማሰባሰብ ቁጥሩን ወደ 11 ገደማ ከፍ እያሳደገ እንደሚሄድ ነው የሚጠበቀው። ምዕራባውያኑ የበለጸጉ መንግሥታት በቀላሉ የሚመለከቱት ሃይል አይሆንም።

MM/DW/RTR/AA