ብሪታንያ፤ የአዉሮጳ ሕብረት እና አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 22.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ብሪታንያ፤ የአዉሮጳ ሕብረት እና አፍሪቃ

የብሪታንያ ሕዝብ በመጪዉ ሐሙስ በሚሰጠዉ ድምፅ ሐገሩ ከሕብረቱ እንድትወጣ ከወሰነ በጋራ ብልፅግና በኩል ከብሪታንያ ጋር፤ በብሪታንያ አማካይነት ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር የተሳሰሩት የአፍሪቃ ሐገራት የሚደርስባቸዉ ጫና ይኖር ይሆን ወይ ነዉ-የአፍሪቃዉያኑ የሰሞኑ ርዕስ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:34

የብሪታንያ፤ ከአዉሮጳ ሕብረት እና አፍሪቃ

ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ትዉጣ፤አትዉጣ የሚለዉ ክርክር አፍሪቃዉያንንም እያነጋገረ ነዉ።አፍሪቃዉያንና ሥለ አፍሪቃ ከሚያጠኑ ባለሙያዎች ገሚሱ ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ከወጣች የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ይጎዳል ሲሉ፤ ሌሎች ይሕን አይቀበሉትም ።ሁለቱም ግን ብሪታንያ ከሕብረቱ አባልነት ከወጣች አፍሪቃ ከአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ ከብሪታንያ ጋር ያላት ግንኙነት እስካሁን ባለበት አይቀጥልም ብለዉ ያምናሉ። ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ትዉጣ አትዉጣ የሚለዉ ክርክር የሐገሪቱ ሕዝብ ነገ ሐሙስ በሚሰጠዉ ድምፅ ይወሰናል።ያን ፊሊፕ ቪልሔልም የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

Brexit-ይሉታል እነሱ-ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት ትዉጣን ሲያሳጥሩት።ግን ከአፍሪቃ ጋር ምን አገናኘዉ? ከብሪታንያዎች ይልቅ መልስ ሰጪዎቹ አፍሪቃዉያን ናቸዉ።«በጣም ብዙ» ትላለች-ናጄሪያዊ ብሪታንዊቷ የአምደ መረብ ፀሐፊ ዩሶ ማዱ።እንዴት ትወጣለች ጋ ለመድረስ ግን እንዴት ገባችን ታስቀድማለች።ማዱ። ታሪክን።

«ብሪታንያ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ስትሆን፤ የጋራ ብልፅግና ማሕበር አባል የሆኑ የአፍሪቃ ሐገራትም የሕብረቱን ክበብ ተቀየጡ እንደማለት ነበር።ብሪታንያ

የአዉሮጳ ሕብረትን እንድትቀላቀል ያደረገዉ ስምምነት፤ሥለ ጋራ ብልፅግና ማሕበር ብዙ ጠቅሷል።ይሕ የጋራ ብልፅግና አባል የሆኑ የአፍሪቃ ሐገራት ከሕብረቱ ጋር የንግድ ልዉዉጥ ለማድረግ ረድቷቸዋል።»

የብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ በ1960ዎቹ ሲያበቃ፤ ገሚስ ዓለምን ያስገበረችዉ ሐያል ግን ትንሽ አዉሮጳዊት ደሴት ምጣኔ ሐብት ተንኮታኩቶ ነበር።በ1973 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) የዛሬዉን የአዉሮጳ ሕብረት ስትቀላቀል ግን የወደቀ ምጣኔ ሐብቷ እንዲያንሰራራ ከቀድሞ ቅኝ ተገዢዎችዋ ጋር የመሠረተችዉን የጋራ ብልፅግና ማሕበርን ከሕብረቱ ጋር አስተዋወቀችዉ።

የብሪታንያ ሕዝብ በመጪዉ ሐሙስ በሚሰጠዉ ድምፅ ሐገሩ ከሕብረቱ እንድትወጣ ከወሰነ በጋራ ብልፅግና በኩል ከብሪታንያ ጋር፤ በብሪታንያ አማካይነት ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር የተሳሰሩት የአፍሪቃ ሐገራት የሚደርስባቸዉ ጫና ይኖር ይሆን ወይ ነዉ-የአፍሪቃዉያኑ የሰሞኑ ርዕስ።የአምደ መረብ ፀሐፊዋ ዩዞ ማዱ በተለይ በንግዱ መስክ ብዙም አይኖርም ባይ ናት።«እስካሁን ካነበብኩት የተረዳሁትና የማዉቀዉ ብሪታንያ ከሕብረቱ መዉጣትዋ አፊሪቃ ንግድ ላይ በቀጥታ የሚያደርሰዉ ጫና የለም።»

የአዉሮጳ ሕብረት ከየምዕራብ አፍሪቃዉ ECOWAS እና ከምሥራቅ አፍሪቃዉ EACን ከመሳሰሉ ቀጠናዊ የምጣኔ ሐብት ትብብሮች ጋር በ2000 ያደረገዉ ሥምነት የሁለቱን ክፍለ-ዓለማት የንግድ ልዉዉጥ እና ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነዉ።ስምምነቱ አነሰም በዛ ሁለቱን ወገኖች በንግድ ያስተሳሰረ ነዉ።አሁን ብሪታንያ ከሕብረቱ አባልነት ከወጣች ግን፤ ጊጋ በተሰኘዉ የጀርመን ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ሮበርት ኮሕ እንደሚሉት ሥምምነቱ ከመሠረቱ መቀየር አለበት።

«ንግዱን በተመለከተ መታወቅ ያለበት ነገር የአዉሮጳ ሕብረት እና የአፍሪቃ ሐገራት ኮቶኑ ላይ ያደረጉት ስምምነት የንግድ ልዉዉጣቸዉ (ገዢ)ደንብ ነዉ።ብሪታንያ ከሕብረቱ ከወጣች በስምምነቱ የተዘረዙሩት መሠረታዊ ደንቦች የግድ መለወጥ አለባቸዉ።»

ከንግድ በተጨማሪ በእርሻ ልማት ከሁሉም በላይ በልማት ርዳታ ላይ የተመሠረተዉ የሕብረቱና የአፍሪቃ ግንኙነት ክፉኛ መናጋቱ አይቀርም።በተለይ አፍሪቃዉያን ከልማት ርዳታ የሚያገኙት ጥቅም ማዱ እንደምትለዉ መጎዳቱ አይቀርም።

«ብሪታንያ በቋሚነት እርዳታ ከሚሰጡ የሕብረቱ አባል ሐገራት አንዷ ናት።ከዚሕም በተጨማሪ ሕብረቱ ለሚሰጠዉ የልማት ርዳታ ከፍተኛ መዋጮ የምታደርግ ሐገር ናት።በዚሕ ረገድ የብሪታንያ (ከሕብረቱ መወጣት) ከሰሐራ በስተደቡብ ለሚገኙ ሐገራት በሚሰጠዉ የርዳታ መጠን ላይ ብቻ ሳይሆን በአሰጣጡ ላይም ከፍተኛ ተፅኖ ይኖረዋል።»

አፍሪቃዉያን ፌስ ቡክን በመሳሰሉ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያደርጉት ክርክርና የሚሰጡት አስተያየት እንደቀጠለ ነዉ።አንዳዶቹ እንደሚሉት የብሪታንያ ሕዝብ ዉሳኔ ምንም ሆነ ምን የነፃነት ምልክት ነዉ ባዮች ናቸዉ።ለአፍሪቃዉያን ጥሩ ትምሕርት ባዮችም አሉ።ሌሎች ግን አሉ «ምን አገባን።»

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic