ብሪታንያና የአውሮፓ ህብረት ማሻሻያ ጥያቄዋ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 09.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ብሪታንያና የአውሮፓ ህብረት ማሻሻያ ጥያቄዋ

ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት አንዷ ብሪታንያ በህብረቱ አባልነት መቀጠል አለመቀጠሏ ከ 2 ዓመት በኋላ በሚካሄድ ህዝበ ውሳኔ ይለይለታል ተብሎ ይጠበቃል ። ከዚያ በፊት ግን ብሪታንያ ህብረቱ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ እየጠየቀች ነው ። የብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ዛቻና የጠየቀችው ማሻሻያ የዛሬው ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:03 ደቂቃ

ብሪታንያና የአውሮፓ ህብረት ማሻሻያ ጥያቄዋ

ከአንድ ወር በፊት በተካሄደ ምርጫ አሸንፈው ብሪታንያን ለ2ተኛ የስልጣን ዘመን የሚመሩትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን መንግስት መርሃ ግብሮች የብሪታኒያ ፓርላማ ባለፈው ሳምንት ተቀብሏል ። በመርሃ ግብሩ ከተካተቱት ውስጥ አንዱ ፤ብሪታኒያ በአውሮፓ ህብረት አባልነት በመቀጠል አለመቀጠሏ ላይ የሚሰጠው ህዝበ ውሳኔ ነው ። በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ከዚህ ህዝበ ውሳኔ አስቀድሞ ግን የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን ከ27ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ጋር ህብረቱ ያስፈልገዋል በሚሉት ማሻሻያዎች ላይ መደራደር ይፈልጋሉ ። ጠቅላይ ሚኒስትር ካምረን ተሃድሶ ይደረግ በሚሉባቸው ጉዳዮች ላይ የአባል መንግሥታትን ድጋፍ ለማግኘትና ማሻሻያውም ለሌሎቹም አባል ሃገራት ጠቃሚ መሆኑን ለማስረዳት ከአንድ ሳምንት በፊት የፈረንሳይ የጀርመን የኔዘርላንድስና የፖላንድ መሪዎችን እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንትን አነጋግረዋል ። በርሊን ውስጥ ከጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር ከተወያዩ በኋላ ካምረን በሰጡት መግለጫ ማሻሻያው የሚያስፈልገው የብሪታኒያ ህዝብ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ለመቆየት እንዲወስን መሆኑን አስረድተው ነበር ።

«የአውሮፓ ህብረት የተሻለ አቋም የሚኖረው ብሪታንያ አባል እንደሆነች ብትቆይ ነው ። በኔ እምነት የብሪታኒያን ብሔራዊ ጥቅሞች በተሻለ ሁኔታ ሊያስጠብቅ የሚያስችለው በማሻሻያው ላይ የተመሰረተው ስምምነት ነው ። ሁለታችንም እንዲሆን የምንፈልገው፣ በሚቀጥሉት ወራት በጋራ የምናከናውነውም ይህንኑ ነው ።ውጤቱም እኛ የምንፈልገው ህዝቡን የሚያሳስቡትን ጉዳዮች የሚመለከቱ ለውጦች ናቸው ። እነዚህ ስጋቶች ምን እንደሆኑ ተናግሬያለሁ ። እንደሚመስለኝ ለነዚህ ስጋቶች መፍትሄ ስንፈልግ ህዝቡ ብሪታንያ ማሻሻያ በተደረገበት በአውሮፓ ህብረት የመቆየት መብት እንዳላት ይገነዘባል ።»

ብሪታኒያ ይሻሻሉ ከምትላቸው የአውሮፓ ህብረት አሰራሮች መካከል የተለያዩ አባል ሃገራት ዜጎች ኑሮአቸውን ብሪታኒያ ሲያደርጉ ከመንግሥት ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ የሚፈቅደው ደንብ አንዱ ነው ።ከዚህ ሌላ የህብረቱ አባል ሃገራት ፓርላማዎች ሥልጣን እንዲጠናከርም ትጠይቃለች ። የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ እንደሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር ካምረን ማሻሻያ እንዲደረግባቸው አበክረው ከሚያሳስቡዋቸው ጉዳዮች ውስጥ እነዚህ ዋነኛዎቹ ናቸው።

ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደ ጥናት የአውሮፓ ህብረትን ጥሎ ለመውጣት የሚፈልጉ ብሪታንያውያን 46 በመቶ ነበር ። በህብረቱ ጥላ ስር መቆየት የሚሹ ዜጎች መጠንም በመቶኛ ሲሰላ እንዲሁ 46 በመቶ ነበር ። ዘንድሮ ግን ይህ ተለውጧል ።ከቅርብ ጊዜው የብሪታኒያ ምርጫ በኋላ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደጠቆመው ከአውሮፓ ህብረት ጋር ለመቆየት የሚፈልጉ ብሪታንያውያን ቁጥር ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ጨምሯል። ባለፈው ሳምንት ይፋ በተደረገ ለ1 ሺህ ብሪታንያውያን

Multikulturelle Gesellschaft in Großbritannien

በቀረበው የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ መጠይቅ ውጤት መሰረት 55 በመቶው ብሪታንያ በአውሮፓ ህብረት አባልነትዋ እንድትቀጥል ይፈልጋሉ ። ይህም የዛሬ ሁለት ዓመት ተመሳሳይ መልስ ከሰጡት ተጠያቂዎች ቁጥር ጋር ሲነፃጸር በ9 በመቶ ይበልጣል ።ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ጋር ብራሰል ውስጥ በተነጋገሩበት ወቅት የብሪታንያ ህዝብ በአውሮፓ ህብረት ደስተኛ አለመሆኑን ነው የተናገሩት ። ብሪታንያውያን በአውሮፓ ህብረት የማይደሰቱበት ምክንያት ምን ይሆን ተብለው ከዶቼቬለ ጥያቄ የቀረበላቸው ብሪታንያዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አንቶኒ ግሊስ አለመደሰታቸው ከተለያየ አቅጣጫ የሚታይ ነው ብለዋል ።

«የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ።ታሪካዊ ምክንያቶችም አሉ ። መለስ ብሎ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የነበረውን ማስታወስ ይቻላል ። ስለ ኛ ታላቅነት መመስከር የሚቻለው በ1940 ነው ። ናዚ ጀርመንን ብቻችንን በድል አድራጊነት መወጣታችንን ልብ ይሏል ። ምናልባት ከዛም በላይ ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው ባለፉት 5 ና 6 ዓመታት የብሪታንያ ተወላጆች ስለ አውሮፓ ህብረት መጥፎ መጥፎው ነገር ብቻ ሲሰሙ መቆየታቸው ነው ። አንድ ነገር ከተሰናከለ ተጠያቂ የሚባለው የአውሮፓ ህብረት ነው። ከተቃና ደግሞ ያስተካከለው የዌስትሚኒስትሩ ብሔራዊ መንግሥት ነው የሚባለው ።»

ይሁንና እጅግ ብዙ ወጣት ብሪታንያውያን አገራቸው ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ አይፈልጉም ። ፒው የተባለው አሜሪካዊው የጥናት ድርጅት እንዳመለከተውአሁን ህዝበ ውሳኔ ቢካሄድ ከ18 እስከ 29 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣት ብሪታንያውያን 69 በመቶው በአውሮፓ ህብረት ውስጥ መቆየትን ይመርጣሉ ። ምክንያቱን ድልነሳው ይነግረናል ።

የብሪታንያ ህዝብ ከ2 ዓመት በኋላ በአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመቆየት ወይም ህብረቱን ጥሎ ለመውጣት የሚሰጠው ድምጽ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመቱ አዳጋች ነው ። ምናልባት እስከዛሬ ሁለት ዓመት ካምረን ያቀረቧቸው የአውሮፓ ህብረት ማሻሻያዎች ሙሉ በሙሉ የአባል ሃገራትን ይሁንታ ባያገኙ አለያም በሚፈለገው ጊዜ መልስ ባይሰጥባቸው ብሪታንያ እንደዛተችው ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መውጣቷ አይቀርም ተብሎ ይገመታል ። ያኔ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን ? ብሪታንያ የሌለችበት የአውሮፓ ህብረትስ ምን ዓይነት ጥንካሬ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል ። ተንታኝ ግሊ ለዚህ ጥያቄ ሁለት ዓይነት አስተሳሰቦች አሉ ይላሉ ።

« አንደኛው ብሪታኒያ በዛም ሆነ በዚህ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ትልቅ የሚባል ድርሻ የላትም የሚል አለ ። ስለዚህ አውሮፓውያን ብሪታኒያ በማህበሩ ውስጥ ሆነች አልሆነች ወጣች አልወጣች የምታመጣውው ለውጥ የለም ብለው የሚያስቡ

Multikulturelle Gesellschaft in Großbritannien

አሉ ። በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩን በጥሞና ሲመለከቱት መውጣት የሚሹትንም ካየን ከአውሮፓ ህብረት ይልቅ ሌላ ዓይነት ማህበር ወይም ህብረት ትስስር እንዲፈጠር የሚሹ ናቸው ። ብሪታንያም እንግዲህ ከተለያዩ መንግሥታት ጋር በተናጠል እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት ጋር ነፃ የንግድ ስምምነት ማድረግ ትችላለች ይህ እስኪሆን ግን ዓመታት ሊፈጅ ይችላል ።»

ድልነሳ እንደሚለው ብሪታንያ ከህብረቱ የምትወጣ ከሆነ ሌሎችም የርስዋን ፈለግ ሊከተሉ የመቻላቸው ስጋትም አለ ።

ብሪታንያ የጠየቀችው የአውሮፓ ህብረት ማሻሻያ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ ድልነሳ እንደሚለው ለብሪታንያ በአውሮፓ ህብረት አባልነት መቀጠል ወይም አለመቀጠል ወሳኝ ጉዳይ ነው ።

በብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ዛቻና ህብረቱ እንዲወስድ በጠየቀችው የማሻሻያ እርምጃ ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አበቃ ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic