«ብሪስላዉ»የአዉሮጳ የባህል ማዕከል | ባህል | DW | 29.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«ብሪስላዉ»የአዉሮጳ የባህል ማዕከል

ዘንድሮ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ተብለዉ ከተሰየሙት ሁለት የአዉሮጳ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በፖላንድዋ ብሪስላዉ አጠገብ ነዋሪ የሆኑት አቶ መርሻ ወልዱ ፖላንዳዉያን እንደ ኢትዮጵያዉያን እንግዳ ተቀባዮች ናቸዉ ሲሉ ይናገራሉ። የህክምና ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ በተለያዩ ሃኪም ቤቶች የሚያገለግሉ ኢትዮጵያዉያን ቁጥርም ጥቂት አይደለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 17:11

«ብሪስላዉ»የአዉሮጳ የባህል ማዕከል

የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ባህላቸዉን እንዲተዋወቁ ብሎም ለዓለም እንዲያሳዉቁ በሚል የኅብረቱ ዓባል ሃገራት ከጎርጎረሳዉያኑ 1985 ዓ,ም ጀምሮ የአንድ ሃገር ከተማን በመምረጥ የዓመቱ የባህል ከተማ ሲሉ ያስተዋዉቃሉ። በርግጥ የአዉሮጳ ኅብረት ከ 17 ዓመት ወዲህ የባህል ከተሞች ሲል በዓመት ሁለት የአባል ሃገራቱን ከተሞች በመሰየም በከተሞች ዉስጥ የሚታዩት የተለያዩ ባህሎች ታሪክ ቋንቋና አኗኗን በአዲስ ማስተዋወቁን መጀመሩም ይታወቃል። በዚህ ቅንብር ዘንድሮ የአዉሮጳ የባህል ከተሞች ተብለዉ ከተመረጡት የሁለት ሃገራት ከተሞች መካከል የፖላንድዋን ብሪስላዉ ከተማን ልናስተዋዉቅ ይዘናል።

Rafal Dutkiewicz Oberbürgermeister Breslau

ራፋል ዱኬቪትዝ - የብሪስላዉ ከንቲባ


በተሰናበትነዉ የአዉሮጳዉያኑ 2015 ዓመት የቤልጅየሟ ሞንስ ከተማና የቼክ ሪፐብሊኳ ፒልስን ከተማ፤ ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ ፤ በከተሞቻቸዉ ዉስጥ የሚታዩትን የተለያዩ ባህልና አኗኗር በመተረክ፤ ዓዉደ ርዕዮችን በመዘርጋት ታሪክን በማሳየት ከአዉሮጳ ብሎም ከዓለም ሃገራት ነዋሪዎችን ጎብኝዎችን ራሳቸዉን አስተዋዉቀዋል። አሮጌዉ ዓመት ተጠናቆ አዲሱ የጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ,ም አንድ ሲል የፖላንድዋ ብሪስላዉና የስፔንዋ ሳን ሰበስታያን ከተሞች የዓመቱ የአዉሮጳ የባህል መዲኖች ተብለዉ ስያሜዉን ተረክበዋል።
ደቡባዊ ምዕራብ ፖላንድዋ ዉስጥ የምትገኘዉ የዘንድሮዋ አንዷ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ብሪስላዉ 600 ሺህ ነዋሪዎች አሏት። ከቼክ ሪፐብሊክ የሚፈልቀና ፖላንድና ጀርመንን በድንበር የሚከፍለዉ የኦደር ወንዝን ተቀብላ ወዳ ባልቲክ ባህርም ትሸኛለች።
ከ 10 ቀናት በፊት የብሪስላዉ ከተማ ነዋሪ ቤርታ ላቡል፤ በሺዎች ከሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በጋራ የከተማዋን የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ተብላ መሰየምን በማስመልከት የተለያዩ የጎዳና ትርኢቶችን በከተማዋ እንብርት ላይ አቅርበዋል። እዚህ በአዉሮጳ ሃገራት ጊዜዉ የክረምት ወራት በመሆኑም እጅግ ቀዝቃዛ ቢሆንም ቤርታ ላቡል ባህላዊዉንና ከሸክላ የተሰራዉን የሸክላ ቃጭል በመደወል ደስታቸዉን ይገልጻሉ ያዜማሉም። ከቤርታ ቃጭል የሚወጣዉ ድምፅ

Polen Breslau Kulturhauptstadt

የብሪስላዉ ነዋሪ -ቤርታ ላቡል

በከተማዋከሚገኙት አራት ግዙፍ የካቶሎክ አብያተ-ክርስትያናት በሚሰማዉ ደወል የተደገፈም ይመስላል። ባለፉት ዓመታት ከተማዋ የደረሰባት የጎርፍ አደጋ ፤ የተካሄደው መልሶ ግንባታና በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የደረሰውን መፈናቀል በጎዳና ትርዒት በትርኢት ቀርቧል። 75 ሚሊዮን ይሮ በጀትን ያገኘችዉ የፖላንድዋ ብሪስላዉ ከተማ፤ የባህል ማዕከሉ ዳይሪክተር ክሪዝቶፍ ማያ እንደሚሉት ከተማዋ በርካታ መስዕቦች አሏት።
« እዚህ ትያትርና ፊልም ቤት ተገብቶ ብቻ አይደለም፤ ባህል አኗኗር መተዋወቅ የሚቻለዉ። በከተማዋ አዉራጎዳናዎች የመዝናኛ ፓርኮችና በመሳሰሉትም የሰዉን አኗኗር ልማድ ማየትና መተዋወቅ ይቻላል። በዚህ ብቻ ሳይሆን በነዋሪዉ እንግዳ መቀበያ ቤትም ቢሆን ስለከተማዋ ማወቅ ይቻላል። ሰዎች በግላቸዉ የሚጠሩት የትያትር ተዋንያን ቡድን አለን፤ አነስ ባለ ድግስ ላይ አጠር ያለ ትያትር ብጤ ማዘጋጀት ይችላሉ። በዚህ መልኩ ነዋሪዉን፤ ሰዎችን ለባህል ትዉዉቅ ለመግባባት ጥሪ እናደርጋለን እንቀሰቅሳለን»

በፖላንድ ሲኖሩ ከ ሰላሳ ስምንት ዓመት በላይ የሆናቸዉ አቶ መርሻ ወልዱ የደርግ መንግስት ወደ ስልጣን እንደመጣ ነዉ። ለትምህርት ወደ ፖላንድ ያቀኑት። ከዝያም ፖላንዳዊት አግብተዉና ቤተሰብ መስርተዉ ሁለት ልጆችን ወልደዉ ፤ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዉ ሦስት ዓመት ኮኖሩ በኋላ ፖላንድ መመለሳቸዉን ነግረዉናል። አቶ መርሻ ወልዱ ። ወደ 10 ዓመት የሆነዉን የኢትዮጵያና የፖላንድ ማኅበር በሊቀመንበርነት ሲመሩም አስር ዓመት ሆኖአቸዋል። የዘንድሮዋ የአዉሮጳ የባህል ማዕከል ብሪስላዉ ከተማ ከሚኖሩበት ስድሳ ኪሎሜትር ርቀት ላይ እንደምትገኝ ነግረዉናል። ብሪስላዉ ይላሉ አቶ መርሻ ወልዱ፤ በአገሪዉ አጠራር ቭሮስዋቭ ትባላለች።
የከተማዋ ዋና ተጠሪ ራልፍ ዱኪቪትዝ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ከተማዋ ከሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በፊት የጀርመኖች ነበረች ከጦርነቱ በኋላ ግን የፖላንድ ከተማ ሆናለች።

Polen äthiopische Gesellschaft

የኢትዮጵያ ፖላንድ ማኅበር


«ብሪስላዉ አንድ ጥሩ ምሳሌ ናት። ከሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በፊት ከተማዋ የጀርመን ነበረች፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን ብሪስላዉ አንዷ የፖላንድ ከተማ ሆናለች። በዚህ ለዉጥ በፊት እዚህ የነበሩት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ወጥተዉ ከለዉጡ በኋላ አዲስ ፖላንዶች መኖር ጀምረዋል። ይህ ማለት በዝያን ጊዜ ከተማዋ በቶ በመቶ አዲስ ነዋሪዎች ነዉ የመጡባት። ሕዝቡ መፈናቀሉ በጣም የሚያሳዝን ነዉ። ዛሬ ብሪስላዉ በጣም ዉብ የፖላንድ ከተማ ናት። ከተማዋ የነዋሪዎችዋ ሁሉ ኃብት ናት። ከተማዋ ደግሞ ጀርመናውያን ኦስትርያውያንንና የቼክ ሪፐብሊክ ዜጎችን ፤ እንዲሁም አይሁዶችን አቅፋ የያዘች ናት። በዚህ ዓመት ለከተማዋ ጎብኝዎች ማሳየት ማስተላለፍ የምንፈልገዉ ይህንን አብሮነት ነዉ። »
በጥንት ጊዜ አዉሮጳዉያንም ሆኑ ከእስያ የመጡ ከተማዋን ለመያዝና ለማስተዳደር ስለሞከሩ በዝያን ጊዜ የገባ የተለያየ ባህልና ሌሎች የተለያዩ እዉቀቶች ለዛሬዉ የከተማዋ እድገት ግብአት ሆነዋል ሲሉ በፖላንድ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ነዋሪ የሆኑት አቶ መርሻ ወልዱ አጫዉተዉናል።
ብሪስላዉ ፖላንድ ዉስጥ ከሚገኙ ከተሞች ሁሉ ለየት እንደምትል የከተማዋ የቱሪስት አስጎብኝ ኡልሪሽ ክሮናካ ይናገራሉ። ለዉጭ ገዥዎችም አልገዛም ባይነትን አሳይታለች በዚህም ይላሉ ክሮኒካ ብሪስላዉ ከተማ ዉስጥ የትግል መገለጫ የሆኑ ሶስመቶ ያህል ምስሎች ቆመዋል
«እዚህ የሚገኙት ነዋሪዎች፤ በአንድ ላይ ሾጣጣ ቆብ ነገር እና ቱታ ብጤ ለመልበስ ተስማምተዉ ነበር። ቡርቱካናማ ሾጣጣ ኮፍያና ቲ -ሸርት አድርገዉ በፊዝና ምፀት የቀድሞዉን የኮሚኒስት መንግስት ለመታገል ፈልገዉ ነበር።»

በጎርጎረሳዉያኑ 2004 ዓ,ም የአዉሮጳን ኅብረት በተቀላቀለችዉ ፖላንድ የኢትዮጵያዉያን ቁጥር ጥቂት መሆኑን አቶ መርሻ ወልዱ ተናግረዋል።

Polen Breslau Kulturhaupstadt

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ጎዳና ላይ ትርዒት


ፖላንድ ዉስጥ የማኅበራት ማቋቋምያ መስፈርትን አሟልቶ ሕጋዊ እዉቅና ያገኘዉ የኢትዮጵያና ፖላንድ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መርሻ ወልዱ ፤ ፖላንድ ዉስጥ በሜካኒካል ኢንጂኔሪንግ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ በዚሁ ሞያ አገልግለዋል። እንደ አቶ መርሻ ምንም እንኳ እጅግ ከባድ ቢሆንም ማኅበራቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሥራዎች ይሰራል። በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በተለይ ላሊበላ አካባቢ ለ 2 ሺህ የዓይን ህመምተኞች የቀዶ ጥገና ህክምና ሰጥቶ የዓይን ታማሚዎችን አድኖአል። በፖላንድ ከሚኖሩት ኢትዮጵያዉያን አብዛኞቹ እዛው ከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው በሙያቸው ተሰማርተው ይገኛሉ።
በፖላንድ የገና በዓል ፤ ፋሲካ እዲሁም አዲስ ዓመት በድምቀት ይከበራል። ገና በዓል ግን ከሁሉም በዓላት በድምቀት የሚከበር እንደሆነ አቶ መርሻ ወልዱ ገልፀዉልናል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶይቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic