ብሔራዊ ውይይት፤ ሕወሓት እና ድሮኖቹ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 24.12.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ብሔራዊ ውይይት፤ ሕወሓት እና ድሮኖቹ

የኢትዮጵያ መንግሥት አካታች አገራዊ ምክክር እንደሚጀምር ዐስታውቋል። ሕወሓት ከአፋርና አማራ ክልሎች ተዋጊዎቼን አስወጥቻለሁ ማለቱን መንግሥት ራስን የማታለል «የውሸት ትርክት» ብሎታል። ቱርክ ሰው አልባ ድሮኖችን ለኢትዮጵያ ሽጣለች መባሉ አሜሪካ እጅግ እንዳሳሰባት መግለጧ ተዘግቧል። በእነዚህ 3 ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:52

የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት

የኢትዮጵያ መንግሥት አካታች አገራዊ ምክክር ሊጀምር እንደሆነ ዐስታውቋል። ሕወሓት ከአፋር እና አማራ ክልል ተዋጊዎቼን አስወጥቻለሁ ማለቱን መንግሥት ራስን የማታለል «የውሸት ትርክት» ብሎታል። ዩናይትድ ስቴትስ ቱርክ ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎችን (ድሮኖች) ለኢትዮጵያ ሽጣለች መባሉ እጅግ እንዳሳሰባት መግለጧ ተዘግቧል። በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል 

ባለፉት ጥቂት ቀናት የኢትዮጵያ መከላከያ፤ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያ እና ፋኖ እንዲሁም ከአፋር ኃይሎች ጋር በመጣመር በሰሜን ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ድሎችን ማስመዝገቡን እያስታወቀ ነው።

«አሸባሪ» ያለው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት)ተዋጊዎችን ገሚሱን በመደምሰስ፤ ቁስለኛ እና ምርኮኛ በማድረግ ቀሪው እንዲሸሽ ማድረጉን ይፋ አድርጓል። ሕወሓት በበኩሉ ከአማራ እና አፋር ክልሎች ኃይሉን ያስወጣው በራሱ ፈቃድ መሆኑን ገልጧል።  መንግሥት በኩል ሕወሓት ስለተናገረው ሲገልጥ ፦ «ራሱን እና ሌላውን ለማታለል የተፈጠረ የውሸት ትርክት» ብሎታል። ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰሰበትም ዐስታውቋል። ቱርክ ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎችን(ድሮኖች)ለኢትዮጵያ ሸጣለች ያለችው ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ጉዳይ፦ «ከፍተኛ የሰብአዊ ስጋት» እንዳላት መግለጧ ተዘግቧል።  የኢትዮጵያ መንግሥት አካታች አገራዊ ምክክር እንደሚኖር ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። በምክክሩ የትኞቹ አካላት ሊሳተፉ እንደማይችሉ እና በምን ጉዳይ እንደሆነ ግን በቀጥታ የተነገረ ነገር የለም። 

ሕወሓት ተዋጊዎቼን ከአማራና አፋር ክልሎች አስወጣሁ ስለማለቱ

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ መከላከያ፤ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ፤ ፋኖ፤ የአፋር ልዩ ኃይል እና የእየ አካባቢዎቹ ታጣቂዎች ሕወሓትን በማሸነፍ በርካታ ከተሞችን መቆጣጠራቸው ተገልጧል። በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሕወሓት ከአማራ እና አፋር ክልሎች ስለመውጣቱ ባሳወቀበት ወቅት የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት (AFP) የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን አነጋግሮ ነበር። ቃል አቀባዩ፦ «ከእነዚህ ቦታዎች ወደ ትግራይ ለመልቀቅ ወስነናል። ለሰብአዊ ርዳታ በሩን ለመክፈት እንፈልጋለን» ማለታቸዉን የዜና ምንጩ አስነብቧል።  «ለቆ ነው እንዴ የወጣው የአድማሱ ወርቅነህ አጭር የፌስቡክ አስተያየት ነው። ጄሪ ጸጋዬ በበኩላቸው፦ «ተሸንፈው ነዋ የወጡት» ሲሉ በአጭሩ ጽፈዋል።

ሕወሓት በኢትዮጵያ ኃይሎች በደረሰበት ሽንፈት ማፈግፈጉን ለመሸፋፈን እየሞከረ ነው ሲል የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ዐስታውቋል።  «ሕወሓት» ዳግም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ስጋት በማይሆንበት ደረጃ እስከሚደርስ ድረስም መከላከያ «አስፈላጊ» ያለውን ማንኛውንም ርምጃ እንደሚወስድ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገልጧል።

ቶክ ኦሎክ ፑክ የተባሉ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ፦ «የትግራይ ኃይሎችን ያባረረው የኢትዮጵያ መከላከያ አይደለም። በራሳቸው ውሳኔ ግጭቱ እንዲያከትም ወደ ትግራይ ክልል የተመለሱት» ብለዋል። «ተሽነፈን ወጥተናል ማለት በርግጥ ሼም ስለሆነ እንደዚህ ማለቱ ይሻላል» ያሉት ደግሞ ሸምስ ኤን ሴልማን ናቸው በፌስቡክ።

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)  በበኩላቸው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ ሳምንት ፃፉት በተባለው ደብዳቤ፦ የሚመሩት ጦር የአማራና የአፋር ክልሎችን ለቅቆ እንዲወጣ ማዘዛቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አስነብቧል። ከዚህ ቀደም ግን ትግራይ ላይ  መንግሥት አደረገ ያሉት «ከበባ» እስኪነሳ ድረስ ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንደማይወጡ ዐሳውቀው ነበር ሲል ይኸው የዜና ምንጭ አክሎ ጠቅሷል። «የጭነቀለት አለ» ሲሉ ጽፈዋል ዝናሽ ወርቁ። «ተሸንፈው ነው የፈረጠጡት እየመረረህ ዋጠው።» አስተያየቱ የአብርሃም ታደሰ ነው። ፍስሃ ኩሩ ፍቅሩ ድግሞ፦ «እውነት ከኢትዮጵያ ጋር ነው ሐገራችን ታሸንፋለች» ሲሉ ጽፈዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የድሮኖቹ ጉዳይ እንዳሳሰባት መግለጧ

የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ቱርክ ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎችን (ድሮኖች)ለኢትዮጵያ ሸጣለች ያም እጅግ ያሳስበኛል ማለቷን ሰሞኑን የውጭ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሮይተርስ የዜና ምንጭ ረቡዕ ዕለት ባስነበበው ጽሑፉ፦ ጢያራዎቹ ከቱርክ ለኢትዮጵያ ተሸጡ መባሉ ለዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፦ «ከፍተኛ የሰብአዊ ስጋት» እንዳሳደረበት ዘግቧል። አንድ የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣን ነገሩኝ ያለው ይኸው ዘገባ፦ ዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሣሪያዎች ለኢትዮጵያ እንዳይሸጡ የጣለችው እገዳ ሳይጣስ አይቀርም የሚል ስጋት እንዳላት ጠቅሷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ እጅግ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። «እና ምን ይሁንሲሉ ዘገባው ላይ ያላቸውን ተቃውሞውሞ በጥያቄ የጀመሩት ማይክ ስሜ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው።  ዩናይትድ ስቴትስ ለሳዑዲ ዓረቢያዎች ጦር መሣሪያዎችን እንደምትሸጥና በዚያም የየመኖች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን በመጥቀስ፦«እስኪ የዚህን ፍትኃዊነት ዐሳዩ» ሲሉም አክለዋል። ታሜ እሸቱ በበኩላቸው፦ «ሰላማዊ ዜጎች ለጥቃት እንደሚጋለጡ ካወቀች ለምን እሷ በመካከለኛው ምስራቅ እንደፈለገች ትጠቀምበታለችነው የነሱ ሂወት አያሳስብም ሲሉ ለአሜሪካ ጥያቄ አቅርበዋል። «እና ቱርክ አልሸጥኩም አላለች፤ ኢትዮጲያም አልገዛሁም አላለች፤ ምን አይነት ውንጀላ ነው በማለት  የጠየቁት ኢብራሒም እንድሪስ ናቸው በፌስቡክ። «አይ አሜሪካ እንደ ዘመነ መሳፍንት በጎራዴ እንድንሞሻለቅላት ነው የፈለገችው። እሷ ኒኩሌር የታጠቀችው ለራሻ ልታበራላት ነው» በማለት የተሳለቁት ደግሞ ስንታየሁ ትእዛዙ ናቸው። «ለምድን ነው ግን ዩናይትድ ስቴትስ በሕወሓት እጅ ስለተገደሉ፤ ስለተጨፈጨፉ እና ሥቅየት ስለደረሰባቸው ግድ የማይሰጣት ሲሉ በትዊተር የጠየቁት ደግሞ ኄኖክ ታደሰ ናቸው። ኢትዮጵያ የፈለገችውን የጦር መሣሪያ የመግዛት እና ሀገሪቱን የማስጠበቅ መብት አላትም ሲሉ አክለዋል።  

ለምለም ታደሰ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ተማጽኖዋቸውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቅርበዋል። «ትግራይ ውስጥ የምንለምነው ምግብ እንዲወርድልን እንጂ ቦንብ እንዲጣልብን አይደለምም» ብለዋል።   ኤስ ደብሊው ትግራይ በሚል ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ቱርክ ለኢትዮጵያ የምትሸጣቸው ሰው አልባ ደምሳሽ ጢያራዎች ትግራይ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን ፍርሐት አንግሶባቸዋል» ሲሉ ጽፈዋል። መልእክታቸውም ለሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) እንዲደርስ የድርጅቱን የትዊተር አድራሻ አያይዘዋል።

«ቱርክ መስሚያዋ ጥጥ ከሆነ ረፋፍዷል።» የጌዲዮን ገረመው አጭር መልእክት ነው። «በነገራችን ላይ አገራት ድሮን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ሕግ አለ እንዴ ይህን ደግሞ የጠየቁት አርጋ ታድ ናቸው ፌስቡክ ላይ። «መጀመሪያ አፍጋኒስታን ውስጥ በድሮን ለጨፈጨፍሻቸው ንፁሃን ኃላፊነት ውሰጂ በሏት» ሲሉ ጽፈዋል የዩናይትድ ስቴትስን አቋም በመቃወም። «በሶሪያ፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን ለሰብአዊ መብት እቆረቆራለሁ በምትለዋ አሜሪካ በድሮን እና በጦር ጀቶች ያለምንም ርህራሄ የፈጀቻቸው ንፁሀን ደምስ ማን ነው የሚጮኽላቸው? ወይ አሜሪካ» ሲሉ ትዝብታቸውን ያሰፈሩት አቡ ፈይሰል ናቸው በፌስቡክ ጽሑፋቸው። ዳውድ አብራር፦ «ምነው የጆ ባይደን መንግሥት ዓለም የሜሪካ ግዛት ናት አለሳ» ብለዋል በአጭሩ። በዚሁ ወደ ሌላ ርእሰ ጉዳይ እንሻገር።

አካታች አገራዊ ምክክር

ሌላው የሰሞኑ መነጋገሪያ የኾነው በመንግሥት በኩል «አካታች አገራዊ ምክክር ለማካሄድ አስፈላጊዉ ዝግጅት» እንደተደረገ መገለጡ ነው። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዚሁ ሳምንት እንዳስታወቀው፤ «ምክክሩን ለማስጀመር ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ስለሚያስፈልግ ምክክሩን የሚያስተባብር ኮሚሽን ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማፀደቅ ዝግጅት እየተደረገ ነዉ» ብሏል። ምክክሩ ግን በምን ጉዳይ፣ እንዴትና ከማን ጋር እንደሚደረግ ይፋ አልተደረገም። «በሂደት የሚታወቅ ይሆናል» ግን ተብሏል። «አገራዊ ምክክር እና ድርድር የተለያዩ ጉዳዮች መሆናቸዉ መታወቅ አለበት»ም ብሏል ኮሚሽኑ።

ሚሚ ሚሚ ፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት፦ «ሁሉም የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሰጥተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቁ» ብለዋል። «ድርድር አይታሰብም» ሲሉም አክለዋል። «ጦርነት ለማንም አይበጅም ስለዚህ ድርድር ይበጃል» ያሉት ደግሞ ካማሽ ብርሃኑ ናቸው። «የትግራይ ምሑራን ቢሳተፉ ጥሩ ነው» ያሉት አብዱ ሺፋ፤ ሕወሓት ግን አይመለከተውም ብለዋል። ኤልሲ አማኑኤል፦ «ጦርነቱ እኮ አልቁዋል ከማን ነው ምንደራደረውሲሉ ተሳልቀዋል። የሕወሓት ጦር የማዕከላዊ እዝ ባልደረባ ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ ይህንኑ ተመሳሳይ ቃል ከዚህ ቀደም በቅርቡ ተጠቅመው ሲናገሩ በቴሌቪዥን ታይተው ነበር።

በተወካዮች ምክር ቤት «አሸባሪ» በሚል ከተሰየመው ሕወሓት ጋር «መደራደር የሚቻልበት ማዕቀፍ» እንደማይኖር የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት ተናግረዋል። የሚካኼደው «ሁሉን አቀፍ ውይይት» ነው ብለዋል። «ሕዝብን አቀፍ ውይይት ይካኼዳል። ድርድርም ውይይትም አይደለም» ሲሉም አክለዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች