ብሉ ካርድ በአውሮጳ | ዓለም | DW | 07.12.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ብሉ ካርድ በአውሮጳ

በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ተለያዩ አገር ዜጎች ወደ አውሮጳ ገብተው መስራት የሚያስችላቸውን የሰማያዊ ካርድ ወይንም ብሉ ካርድ ህግን አስመልክቶ የአውሮጳ ህብረት አባል አገራት ትላንት በቤልጂየም ብራስልስ ስብሠባ አድርገዋል። ጀርመን ገና ከወዲሁ ያደረባትን ጥርጣሬ እየገለፀች ነው።

default

ጀርመናውያኑ ባለስልጣናት ዎልፍጋንግ ሾይብለ እና ኦላፍ ሾልትስ ብሉ ካርድን አስመልክቶ ትላንት በቤልጂየም ከተሠየመው የአውሮጳ ኅብረት ስብሰባ ብዙም የሚጠብቁ አልነበሩም።በስብሰባው ላይ ያሰሙት አቓማቸውን የሚገልፀው ንግግራቸውም ከሁለት ደቂቃ ያልበለጠ መሆኑም የሚደንቅ አልነበረም።በአቓም ደረጃ ሁሉም ነገር በፊት እንደነበረው እንዳለ ነው የገለፁት። በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሀይል፤አዎ ያስፈልገናል።ሆኖም ግን ውሳኔውን በተመለከተ እያንዳንዱን አባል አገራት የሚመለከት ነው።በጀርመን ያለው ዕድል ግን በጣም አናሣ ነው፤ሲሉ የጀርመን ሠራተኛ ሚንስትር ሾልትስ ገልፀዋል።

እንደሾልትስ እምነት ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚገመት ስራ አጥ ባለባት አገር ላይ ተጨማሪ የሰው ሀይል አስፈላጊነቱ የሚታይ አይደለም።ብሉ ካርድ ወይንም የሰለጠነ የሰው ሀይል ወደ አውሮጳ መጥቶ መስራት የሚያስችለውን ፍቃድ በተመለከተ ጀርመን ተቃውሞ የላትም።ድንገት የሚጎርፈውን የሰው ሀይል መቆጣጠር አያሰቸግርም ያሉት ደግሞ የአገር ውስጥ ሚንስትሩ ሾይብለ ናቸው።

መጓዝ ይፈቀዳል፣መስራት ግን ያጠራጥራል።ይህ አዲሱ የብሉ ካርድ ዕቅድ ለበርካታ የሠለጠኑ ሰዎች ምን ያህል ሳቢ እንደሆነ አጠያያቂ ሆኗል። አውሮጳ አሁን ካላት አጠቃላይ ነዋሪዋ በመጪው ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ሃያ ስድስት ሚሊዮን ነዋሪዋ እንደሚቀንስ እየተነገረ ነው።ይህም በመሆኑ ወደፊት በርካታ የሠራተኛ ሀይል አስፈልጓል።ሆኖም ግን ይህ ሀሳብ ለጀርመን ብዙም የተዋጠላት አይደለም።ነገሮች በተገቢው መልኩ ገደብ ሊደረግባቸው ይገባል እያለች በመሞገት ላይ ናት።

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ፍራንኮ ፍራንቲኒ ይህን የብሉ ካርድ አስመልክተው በአባል አገራት ዘንድ ለመስራት የፈለገ የሠለጠነ ግለሰብ በየሁለት ዓመቱ የሚታደስ የስር ፈቃድ እንዲሰጠውና በመላው የአውሮጳ አባል አገራት ዘንድ ተንቀሳቅሶ መስራት እንዲችል በስብሰባው ላይ አንስተዋል። ሆኖም ጀርመን ብሉ ካርድን በተመለከተ ውሳኔው የየአባል አገራቱ መሆን አለበት ስትል፤ጣሊያን ስፔንና ግሪክ ደግሞ በህገወጥ መንገድ ወደ አገራቸው እየተግተለተለ ያለውን ስደተኛ ማገድ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው በአፅንኦት ገልፀዋል።