1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤንሻንጉል፦ ሰሚ ያጡ የጣዕር ድምፆች

ማክሰኞ፣ ጥር 11 2013

የሰው ልጅ ሰብአዊ ክብሩ ተገፎ ለካራ የሚጋዝበት የደም መሬት፤ ቤንሻንጉል። ክቡር ገላ በየጢሻው የሚረግፍበት ምድር፤ መተከል። የመቶ ሺህዎች ስጋት እና ሰቀቀን ምንጭ፦ ሕይወት የረከሰበት የኢትዮጵያ ጥግ። በግፍ የታበዩ ጦረኞች የዛር ቆሌያቸው ሲያስጓራቸው ካራቸውን ስለው፤ እንደ እብድ የሚሮጡበት ውድም።

https://p.dw.com/p/3nzbv
ምስል Negassa Dessakegen/DW

መተከል ግፉ አልተቋረጠም

የሰው ልጅ ሰብአዊ ክብሩ ተገፎ ለካራ የሚጋዝበት የደም መሬት፤ ቤንሻንጉል። ክቡር ገላ በየጢሻው የሚረግፍበት ምድር፤ መተከል። የመቶ ሺህዎች ስጋት እና ሰቀቀን ምንጭ፦ ሕይወት የረከሰበት የኢትዮጵያ ጥግ። በግፍ የታበዩ ጦረኞች የዛር ቆሌያቸው ሲያስጓራቸው ካራቸውን ስለው፤ እንደ እብድ የሚሮጡበት ውድም። የፖለቲከኞች ቊማር የነፍስ ግብር ማወራረጃ። ለመሆኑ ቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ውስጥ የሚደጋገመውን እልቂት እና ግፍ የክልሉ አስተዳደር ማስቆሙ እንዴት ተሳነው? የፌዴራል መንግሥትስ ምን እያደረገ ነው? የዛሬው ማኅደረ ዜናችን የሚያጠነጥንባቸው ዐበይት ጥያቄዎች ናቸው።

አንድ ጊዜ፤ ቡሌን፣ ሌላ ጊዜ ዳንጉር፤ ቆየት ብሎ ደግሞ ማንዱራ እና ድባጤ ወረዳዎች እያለ የሚመላለስ ስቃይ በርትቷል። የመተከል ሰባቱም ወረዳዎች ይብዛም ይነስም የስቃይ ምድሮች ከኾኑ ሰነባብተዋል። ወረዳዎቹ፦ የሕጻናት የሰቆቃ ድምፆች፤ የእናቶች የስቃይ ዋይታዎች ይስተጋቡባቸዋል፤ ግድያ እና ግፍ አዙሪት ኾነው ይመላለሱባቸዋል።  

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ በመተከል ዞን በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ስልታዊ በኾነ መልኩ ተደጋጋሚ የጅምላ ግድያ እና ጥቃት ሲፈጸምባቸው በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ ግድያው በአካባቢው በሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይም ያነጣጠሩ እንደኾኑ ያመላክታሉ።

«አካባቢው ላይ የሚንቀሳቀሰው የጉምዝ ኃይል ቀለም ለይቶ የማጥቃት ጉዳይ ነው እዚህ አካባቢ የሚታየው። አገራችን የእኛ ነው፤ መተከል የእኛ ነው የሚለውን ጉዳይ አንስቶ በዚህ ጉዳይ ነው ተኩስ የከፈቱት።»

በአካባቢው የተከሰተው ችግር ድምፅ አጥፍቶ በርካቶችን ጭዳ ሲያደርግ ዓመታትን አስቆጥሯል።  ወርሓ ሐምሌ 2011 ዓ.ም ላይ በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ ሲገለጥ ግን ግድያው እንደሚቆም ብዙዎች ገምተው ነበር። በግድያ እጃቸው እንዳለባቸው የተጠረጠሩ የወረዳ አመራርና የጸጥታ ኃይሎች በቊጥጥር ስር መዋላቸውም የተነገረውም ወዲያም ነበር። ግድያ እና ማፈናቀሉ በተጠናከረ መልኩ ዳግም ለመጀመሩ ግን አፍታም አልቆየ። እንደውም በአጭር ጊዜያት ውስጥ ተደጋገመ።

ከዛሬ ሁለት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን በፊት፦ ተቃውሞ እና ቁጣው ከእየ አቅጣጫው ሲበረታ ግን የክልሉ ባለሥልጣናት ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቊ ሚሊሺያዎችን መልምያለሁ ሲል ዐስታወቀ።  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በመተከል ዞን ከሰባቱም ወረዳዎች ከ3000 በላይ ሚሊሻዎች መመልመላቸውን በወቅቱ ይፋ ሲኢደርጉ እንዲህ ቃል ገብተው ነበር።  

Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

«የድባ ቡሌንና ማንዱራ ወረዳዎች የመሳሰሉት ሙሉ በሙሉ አሰልጥነው ወደ ተግባር የሚገቡበት ኹኔታዎች አሉ። ከዛ ውጪ ዳንጉር ምልመላ ሥራዎችን ጨርሷል [ማለት ይቻላል] ፓዌ ወረዳም የምልመላ ሥራዎን ጨርሶ ሥልጠናዎችን መስጠት ነው። ጉባ ወረዳም በተመሳሳይ መልኩ የምልመላ ሒደቱን ጨርሶ በቀጣይ ስልጠናዎችን ሰጥቶ ሚሊሺያዎችን በአግባቡ አደራጅቶና አስታጥቆ ወደ ሥራ የሚያስገባበት ኹኔታዎች አሉ»

ኃላፊው ሚሊሺያዎቹ የተመለመሉት በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍና ኅብረተሰቡም ራሱን እንዲጠበቅ ለማስቻል ነው አሉ። አሉ ነው። ከዚያ በኋላ ግን መተከል በተደጋጋሚ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ነዋሪዎቿን ገብራለች።  የጠቅላይ ሚንሥትሩ በቦታው መገኘት ነዋሪዎችን ከመገደል አልታደገም።

የዛሬ አንድ ወር አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተገኝተው ከነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው ተዘገበ።  በውይይቱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ አሻድሊ ሐሰን እና ሌሎች ከፍተኛ አመራርም ተገኝተው ነበር። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ስለመተከሉ ውይይት በይፋዊ የማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፦ «ችግሮችን እንዳይደገሙ አድርገን እንፈታቸዋለን» ብለውም ነበር። ብለው ነበር።

በዛው ቤንሻንጉል ክልል፤ ታጣቂዎች ጥይት ለማዝነብ እና አስክሬን ለመከመር ግን አንድ ሙሉ ቀን እንኳን አላስቆጠሩም። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ውይይቱን ባደረጉ ማግስት በማለዳው በዛው መተከል ዞን፤ ቡለን ወረዳ፤ በኩጂ በተባለች ቀበሌ በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ መንገድ መገደላቸውን የአካባቢዉ ነዋሪዎች አረዱ።

«በመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ ነው ያለሁት። በአንድ ወረዳ ከ106 በላይ ሰው ነው የታረደው እና የተገደለው። እና በጣም ዘግናኝ እና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ድርጊት ነው የተፈጸመው።  በተጨማሪም ከ50 በላይ ቤቶችም ተቃጥለዋል። በዚህ ድርጊት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ 96 ሰዎች ነበር፤ አሁን እየተፈተሸ እየተፈተሸ ሄዶ ወደ 106 ሰዎች ደርሷል።»

በቡለን ወረዳ ከተገደሉት ከ200 በላይ ሰዎች መካከል የስድስት ወር ጨቅላን ጨምሮ 17 ሕፃናት እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገልጧል። ከግድያው በኋላ ከ43 ሺሕ በላይ መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግሥት አረጋግጧል። የጥቃቱ ሰለባዎች በጅምላ በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን ወረዳው አረጋግጧል። ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት የመከላከያ ሠራዊትም ኾነ ሌሎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአቅራቢያዉ እንዳልነበሩ እና ዘግይተው መድረሳቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት ስለደረሰው ጥቃት ለዶይቸ ቬለ የተናገሩ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ግድያዎች ሲፈጸሙ የፀጥታ ኃይላት ከለላ አለመኖሩን በማማረር ይገልጣሉ።

«የመከላከያ ሥራ በዚህ ሰአት ላይ የሌባ እና[ፖሊስ] ጨዋታ የሚባል አይነት ህጻናት የሚጫወቱት አይነት ነገር ነው እየኾነ ያለው። ምክንያቱም ጥቃት ከደረሰ በኋላ ደርሶ ጉዳዩን እንትን ከማለት ውጪ ቀድሞ የመከላከል ሥራ ላይ ምንም እየተሠራ ያለው ነገር ዐይታየኝም እንደእኔ። ምክንያቱም፦ ያ ነገር ከመጀመሪያውኑ መከላከያ፤ ሕዝብ እኮ ያውቃል አንዳንዱን ነገር። ቀድሞ ጥቆማዎችን ያደርጋል። እና እዛ ላይ ቀድሞ የመድረሱ ነገር የተገታ ነው። በሚፈለገው መጠን እየተሠራ ነው ብዬ ለመናገር በእውነት ይከብደኛል። ለዛ ነው። መከላከያዎች አኹን ጥቃት ከደረሰ በኋላ ሬሳውን ኼደው ከሰው ጋር ሰብስበው ለማምጣት እንደዚህ አይነት ነገር ነው አብዛኛውን ጊዜ እየሠሩት ያሉት።»

Karte Äthiopien Metekel EN

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን፦ አንድ ጊዜ በቀስት፣ ሌላ ጊዜ በስለት እና በጥይት በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸው አሁን አሁን የተለመደ ይመስላል።  ጥቃቱ ቀጥሏል። ባሳለፍነው ሳምንት በደረሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችም የተገደሉ በርካቶች ናቸው። አንድ የመተከል ዞን ዳሌታ የተባለ አካባቢ ነዋሪ ባሳለፍነው ረቡዕ ቀጣዩን ለዶይቸ ቬለ እንዲህ ተናግረው ነበር።

«ከሦስት ሰአት ጀምሮ እስከ ዐሥራ አንድ ሰአት ድረስ ሬሳ ዳሌታ ከምትባል ከተማ ነበር በአንድ አይሱዙ መኪና ተጭኖ ቁሞ የነበረው። እና በዐይኔ ዐይቻለሁ። ሬሳ ተጭኖ ሲመጣ በዐይኔ ዐይቻለሁ። አምቡላንስ ቀኑን ሙሉ ቊስለና ስታመላልስ ነበር ወደ ፓዊ እና ባሕር ዳር። ትናንትና ሚዲያ 80 ሲል ነበረ ከሰማኒያ በላይ 168 እየተባለ ነው ያለው።»

ይኽንኑ እና ሌሎች ግድያዎችን አስመልክቶ ረቡዕ ጥር 5 ቀን፣ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ያወጣው መግለጫ በእርግጥም አስደንጋጭ ነው። ኢሰመጉ፦ «መቆሚያ ያጣው በመተከል ያሉ ሰዎች እልቂት» ሲል ያስነበበው መግለጫ ባለፉት 5 ወራት ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጣል።  በ100 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ይላል ዘገባው። የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ ረቡዕ ዕለት ዳለቲ በተባለዉ ሥፍራ የነበረውን ሰቆቃ እንዲህ ያብራራሉ።

«በድባጤ ወረዳ ቆርቃ ቀበሌ፤ ዳሌቲ በተባለች መንደር ላይ ነው ይኼ ግድያ የተፈጸመው እስካሁን እኛ ባለን መረጃ ከ100 በላይ የሚኾኑ ንጹሃን ሰዎች በአሰቃቂ ኹኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በርካታ ቊጥር ያላቸውም ዜጎች እንደዚሁ ቊስለኛ ኾነው በጋሊሣ ጤና ጣቢያ ቡለን ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እንዳሉ ከአካባቢው በሚደርሱን መረጃዎች ለማረጋገጥ ችለናል።»

በመተከል የበረታውን ግድያ እና ማፈናቀል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ የዛሬ ወር ግድም፦ «አማራን ዒላማ ያደረገ ጥቃት» ብለውት ነበር።  «በቀላሉ የሚታይ አይደለም» ሲሉም ከአማራ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባዳረጉት ቃለ መጠይቅ ጠጠር ባለ መልኩ ሲናገሩም ተደምጠው ነበር።

«እና የመተከል ጉዳይ ያነሳኸው ልብ የሚሰብር፣ ቊጭት ውስጥ የሚከትት ነው። ተጠያቂ የምናደርጋቸውም ሰዎች አሉ። በዚህ ላይ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። መተከል ያለ ዜጋ ሕይወቱ መዳን አለበት፣ መጠበቅ አለበት። አኹን የመሬት ጥያቄ የምናምን ጥያቄ፤ መሬቱ የትም አይኼድም። መሬቱ የኢትዮጵያውያን ነው። ማነው ለተወሰኑ ሰዎች የሰጠው ያንን መሬት? የኢትዮጵያ መሬት እኮ ነው። ማንም ሰው እዛ መሬት ላይ ኼዶ መኖር ይችላል፤ መብቱ ነው። ይኽንን የሚከለክል ካለ ደግሞ እኛ እስከ መጨረሻው እንዋጋዋለን። አንታገስም ከዚህ በኋላ።»

የፖሊስ ኃላፊው ይኽን ካሉ አንድ ወር አለፋቸው። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግን ዛሬም ሕይወት መቀጠፉ አልተቋረጠም። ገዳዮችም እንዳሻቸው ይርመሰመሳሉ።

«አረመኔያዊ ድርጊት የሚፈጸምበት ምድር፤ በምድር ላይ በኢትዮጵያ ላይ አይደለም፤ በምድር ላይ መተከል ነው። ይኼን ግፍ ኢትዮጵያውያን ማወቅ አለባቸው። ይኼን ግፍ እዚያ አካባቢ አስተዳድራለሁ የሚለው አካል ማወቅ አለበት፤ ተጠያቂም ነው።»

Äthiopien Benishangul Region, Stadt  Metekel
ምስል Negassa Dessakegen/DW

በእርግጥ ምን ያኽሉ ተጠያቂ ኾኑ ብሎ መጠየቅ ይቻላል። ስለአጠቃላዩ የመተከል ተደጋጋሚ ግፍ የአካባቢው ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡን ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተደጋጋሚ ደውለን ነበር። ኾኖም ያብዛኛዎቹ ስልኮች አይነሱም። የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን  በተለይ ከመተከል ዞን የሚወጡ መረጃዎች በኮማንድ ፖስት ስር ብቻ የሚከወኑ እንዲሆኑ መንግሥት መወሰኑን ለዶይቸ ቬለ በመግለጥ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

የኮማንድ ፖስቱ መሪ ሌተናል ጄነራል አስራት ደነሮ ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም። ከኮማንድ ፖስቱ መረጃዎችን በዋናነት እየተቀበለ የሚያሰራጨው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)በበኩሉ ሰሞኑን ባወጣቸው ዘገባዎቹ ርምጃ ስለመወሰዱ ጽፏል።  «በመተከል ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ባለው የጥፋት ቡድን ላይ የተጠናከረ ርምጃ እየተወሰደ ነው ... ግብረ ሃይሉ» ሲልም በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል። ተወሰደ የተባለው ርምጃ መጠኑ እና አይነቱ ግን አልተገለጠም። የኹኔታው አሳሳቢነትን እንደገመገመ የጠቀሰው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጊዜያዊ መፍትኄ ያለውን አቅርቧል።  ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

«በአጠቃላይ እንደው እስከ አሁን የደረሱትን ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ቀውስ በመመልከት እና የክልሉ መስተዳደር ደግሞ በአካባቢው ፀጥታውን ለመቆጣጠር እና አጥፊዎቹን ተቆጣጥሮ ለዳኝነት ለማቅረብ አቅሙ ውሱን መኾኑ፤ በጣም በተደጋጋሚ የታየ ስለኾነ እኛ አኹን ነገሩ ባለበት ኹናቴ እያቀረብን ያለነው የመፍትኄ ሐሳብ በጊዜያዊነትም ቢኾን የዞኑ መስተዳደር ለጊዜው በፌዴራል መንግሥት መስተዳደር ስር ኾኑ አንደኛ አጥፊዎቹን ከገቡበት ገብቶ በመቆጣጠር ለዳንነት ለማቅረብ፤ ኹለተኛ የቶጎዱትን ሰዎች ሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስላቸው ለማድረግ፤ ሦስተና ይኽ ነገር ደግሞ ተደጋግሞ መድረሱን ለመከላከል እጅግ የተጠናከረ የፀጥታ ምላሽ እንዲሰጥበት የፌዴራሉ መንግሥትን ሙሉ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ብለን ነው የምናስበው።»

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋም መንግሥት ሊያደርግ ይገባዋል የሚሉትን እንዲህ ያብራራሉ።

«አሁንም መንግሥትን ደግመን የምንጠይቀው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ፤ ጥናት ላይ መሠረት አድርጎ አስቸኳይ ዘለቄታዊ መፍትኄ እንዲሰጥ ነው የምናሳስበው። ግድያው እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው። ከሟቾቹ ውስጥ ህጻናት እና እናቶች ጭምር በዛ ያለውን ቊጥር ይይዛሉ። ስለዚህ ኢሰመጉ ይኼ በጣም የሚያሳስበው ጉዳይ ስለኾነ መቆሚያ ያጣው በመተከል ያሉ ሰዎች እልቂት ባስቸኳይ ይቊም የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥተናል።»

ከሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች እና የሰላማዊ ሰዎች መጎዳት ከሚያማቸው ዜጎች ውትወታ ባሻገር የመገናኛ ብዙኃን እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለቤንሻንጉል ጥቃት ትኩረት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ እየተጠየቀ ነው። የቤንሻንጉል የህጻናት እና የእናቶች ዋይታ፤ የጣዕር ድምጾች ግን ዛሬም ሰሚ አላገኙም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ