ቤተ ክርስትያናት ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች በፍራንክፈርት የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.09.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ቤተ ክርስትያናት ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች በፍራንክፈርት የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ

ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለማቀፍ የሃይማኖት እና የዕምነት ነጻነት መብት ድንጋጌዎች በመጻረር በተለይም በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ላይ የሚደርሱ ውድመቶችና በካህናትና ምዕመናኑም ላይ የሚፈጸሙ የግድያ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ተጠየቀ::

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:34

ክርስትያኖች በፍራንክፈርት ሰልፍ አካሄዱ

ዛሬ በፍራንክፈርት ከተማ ጥቃቱን ለማውገዝ የተደራጀው ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በጠራው ሕዝባዊ ሰልፍ የተካፈሉ የዕምነቱ ተከታዮችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን መንግሥት የሃይማኖት ግጭትና ጥላቻን በመቀስቀስ አገሪቱን ወደብጥብጥ በሚመሩ የጥፋት ኃይሎች ላይ አፋጣኝ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድና የዜጎቹንም የደህንነት ዋስትና ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት:: በቅርቡ ፍራንክፈርት ውስጥ የተካሄደን ሕዝባዊ ስብሰባ "በዛቻና በማስፈራራት ለማወክ ሞክረዋል የዝግጅቱን አስተባባሪዎችና የዕለቱንም የክብር እንግዳ ለማሸማቀቅ ተንቀሳቅሰዋል" ያሏቸውን ግለሰቦች ጉዳይ ከጀርመን የሕግ አካላት ጋር በመነጋገር በሽብር ወንጀል በፍርድ ቤት እንዲታይ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ያወሱት የጊዜያዊ ሰልፉ ዋና አስተባባሪ እና በጀርመን የረጅም ጊዜ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ አቶ ስዩም ሃብተማርያም በበኩላቸውበኢትዮጵያም እንዲሁ በህዝቦች ላይ የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙና የሕዝብ ዕልቂትን የሚያስከትል ሃይማኖት ጠል የፖለቲካ ሴራ የሚያቀናብሩ ግለሰቦች ቡድኖችም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በዓለማቀፉ ችሎት እንዲጠየቁ እናደርጋለን ብለዋል::  ዝርዝሩን እንዳልካቸው ፈቃደ አጠናቅሮታል::

ዛሬ ከቀትር በኋላ በፍራንክፈርት ኮንስታብለርቭኻ በሚባለው የከተማዋ ዕንብርት በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ላይ የሚደርሱ ውድመቶችና በካህናትና ምዕመናኑም ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ለማውገዝ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ የተሰባሰቡት የዕምነቱ ተከታዮችና ኢትዮጵያውያን በጥቃቱ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለመግለጽ የህሊና ጸሎት በማድረግ ነበር የሰልፉን መርሃግብር የጀመሩት:: " የዕምነት ተቋማትን እና ታሪካዊ ገዳማትን ማቃጠል በአስቸኳይ ይቁም! የሽብር ጥቃትና የጥላቻ ቅስቀሳ በኢትዮጵያ ይብቃ ! ግጭትና ጥላቻን ቀስቃሾች በነጻው ዓለም ከመንቀሳቀስ ይታገዱ! በጥላቻ ቀስቃሽ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የአውሮጳ ህብረት ቪዛ ክልከላ ይደረግ ! ዓለማቀፍ የዜጎች የመኖርና የዕምነት ነጻነት በኢትዮጵያ ይከበር ! የሃይማኖትና የዘር ጥላቻን በመስበክ የንጹሃን ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ ለፍርድ ይቅረቡ ! " የሚሉና ሌሎችም ድርጊቱን የሚያወግዙ መፈክሮችንም ሰልፈኞቹ አሰምተዋል::

በሰልፉ ላይ ላለፉት ዓመታት በመላ አገሪቱ እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ላይ ጥላቻን መሰረት ባደረጉ ቅስቀሳዎች አስከፊ ጥቃቶች መድረሳቸውሃብትና ንብረት ንዋየ ቅዱሳት ሳይቀሩ  መመዝበራቸው ካህናትና ምዕመናኑም ላይ አሰቃቂ ግድያዎች መፈጸማቸውና ሕጻናትና ሴቶችም ጭምር በጥፋት ኃይሎች ተደፍረው ለስነ ልቦና ችግር መጋለጣቸው ተገልጿል:: በጀርመን የረጅም ጊዜ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ የሆኑት የሰልፉ ዋና አስተባባሪ አቶ ስዩም ሃብተማርያም ይህ ዓይነቱ የወንጀል ድርጊት አገርን የሚበታትንና የሃይማኖት ዕልቂትን የሚያስከትል በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ ህጋዊ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል ነው ያሉት:: በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ቤተክርስቲያኒቱንም የችግሩ ሰለባ እንዳደረጋት የጠቀሱት እነዚሁ ሰልፈኞች ከሁለት ሺህ ዘመን በላይ ለኢትዮጵያ አንድነት ታላቅ የታሪክ ገድል በፈጸመችው የተዋህዶ ዕምነት ላይ በተለይ ያነጣጠረው ይህ አሳዛኝ ጥቃት መቆሚያ ካጣ የህዝብ ቁጣን ሊቀሰቅስ አገሪቱንም ከባድ ምስቅልቅል ውስጥ ሊከት የሚችል በመሆኑ መንግሥትም ሆነ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሁሉ ቆም ብለው እንዲያጤኑት ነው ያሳሰቡት::

የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዘቡት በጀርመን የረጅም ጊዜ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ አቶ ስዩም ሃብተማርያም በቅርቡ በፍራንክፈርት ከተማ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የመሰብሰብ ነጻነታቸውን ተጠቅመው ያዘጋጁትን የውይይት መድረክ በዛቻና በማስፈራራት ለማወክ የሞከሩ የዝግጅቱን አስተባባሪዎችና የዕለቱንም የክብር እንግዳ ለማሸማቀቅ ተንቀሳቅሰዋል ያሏቸውን ግለሰቦች በጀርመን ፍርድቤት በሽብር ወንጀል ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው አሁንም በኢትዮጵያ ጥላቻና ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ቡድኖችና የፖለቲካ ድርጅቶች ከእኩይ ድርጊታቸው ካልታቀቡ በዓለም አቀፍ ህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እናደርጋለን ብለዋል:: ለእነዚህ ወንጀለኞች የገንዘብ ልገሳና ማናቸውንም ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችም ከህግ ተጠያቂነት አይድኑም ሲሉ ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት::

በኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያን በካህናቱና ምዕመናኑ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማውገዝ በፍራንክፈርቱ ሰልፍ ላይ የተካፈሉ ኢትዮጵያውያን ጨምረው እንደገለጹት እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር በ 1948 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ በአንቀጽ 18 ዕውቅና የሰጠውና በኋላም ድርጅቱ በ 1966 ዓ.ም በተቀበለው የሲቭልና የፖለቲካ መብቶች ዓለማቀፍ የቃልኪዳን ስምምነት ያረጋገጠው "የኃይማኖትና የግለሰቦች የዕምነት ነጻነት መብት ድንጋጌ" በኢትዮጵያ እየተጣሰ ነው:: በመሆኑም ዓለማቀፉን እና የአገሪቱን

መሰረታዊ የዕምነት ነጻነት ድንጋጌዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ የብሮድካስት ህግን በመጣስ የጥላቻና በሃሰት ላይ የተመሰረቱ የግጭት መልዕክቶችን በልዩ ልዩ ማኅበራዊና መገናኛ ዘዴዎች በሚያስተላልፉ የጥፋት ኃይሎች ላይ gመንግሥት ህጋዊ ክትትል እና የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ  አበክረው ጠይቀዋል:: በጀርመን ዋና መዲና በርሊን በኢጣልያ ሮም በፓሪስና በሌሎች የአውሮጳ ከተሞችም በዛሬው ዕለት ተመሳሳይ ሰልፎች መካሄዳቸውን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል::

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ልደት አበበ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች