ቤተ-እሥራኤላውያን ከኢትዮጵያ ሊወሰዱ ነው | ዓለም | DW | 10.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ቤተ-እሥራኤላውያን ከኢትዮጵያ ሊወሰዱ ነው

እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ-እሥራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ልትወስድ መሆኗን ገዢው ፓርቲ አስታወቀ። ውሳኔው መንግሥት የማውረድ ስጋት ለፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሔ እንደሚሆን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የቤንያሚን ኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ ጥምር መንግሥት ከመሰረቱ አጋሮቹ ጋር በመሆን 1,300 ኢትዮጵያውያን በዚህ አመት ወደ እስራኤል ለማጓዝ መወሰኑን የዜና አውታሩ ጨምሮ ዘግቧል። ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ-እሥራኤላውያን ወደ እስራኤል የሚጓዙበት ሁኔታ ወደ ፊት እንደሚታሰብም ተገልጧል።

የእስራኤል መንግሥት በበጀት ምክንያት ኢትዮጵያዊ ቤተ-እሥራኤላውያንን ለመውሰድ የነበረውን እቅድ በመሰረዙ ቤተ-እስራኤላውያን ባለፈው ወር የአደባባይ ተቃውሞ አድርገው ነበር።

ክኔስት በመባል የሚታወቀው የእስራኤል ምክር ቤት አባላቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቭራሃም ንጉሴ እና ዴቪድ አምሳለም ተቃውሞውን በመደገፍ ድምጸ-ተዓቅቦ አድርገዋል። የሁለቱ የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ የገዢው ሊኩድ ፓርቲ ኅልውናን አደጋ ላይ ጥሎታል።

120 አባላት ባሉት ምክር ቤት የአንድ መቀመጫ ብቻ ብልጫ ያለው ሊኩድ ፓርቲ በርካት ረቂቅ አዋጆች በቂ ድምጽ ላያገኙ ይችላሉ በሚል ስጋት ለውሳኔ የሚቀርቡበትን ጊዜ ለማራዘም መገደዱን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ትውልደ-ኢትዮጵያዊው የምክር-ቤት አባል አቭራም ንጉሴ «ታሪካዊ ፍትኅ» ያሉት የቤኒያሚን ኔታንያሁ ጥምር መንግሥት ውሳኔ እጅግ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ