ባግዳድ የተያዘችበት አራተኛ አመት እና የኢራቅ ሁኔታ | ዓለም | DW | 10.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ባግዳድ የተያዘችበት አራተኛ አመት እና የኢራቅ ሁኔታ

ምሳሌነቱን ያኔ የተረጎመ ከነበረ-እሱ የአዋቂዎች አዋቂ ነዉ።

የሺዖች ተቃዉሞ

የሺዖች ተቃዉሞ

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የኢራቅን ርዕሠ-ከተማ ባግዳድን የተቆጣጠረበት አራተኛ አመት ትናንት ታስቦ ዉሏል።ዕለቱ የቀድሞዉ የኢራቅ አምባገነን መሪ ሳዳም ሁሴን ከሥልጣን የተወገዱበት በመሆኑ ለኢራቅ ሕዝብ አስደሳች በሆነ ነበር።ግን አልሆነም።ባለፉት አራት አመታት በርካታ ወገኖቹ ያለቁበት የኢራቅ ሕዝብ ዕለቱን ትናንት ያከበረዉ በሐዘንና አሜሪካንን በሚያወግዝ የአደባባይ ሰልፍ ነዉ። ኢራቅን የወረረዉ የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር በአረባዊቷ ሐገር ምሥቅልቅል ሰበብ ከዉስጥም-ከዉጪም የገጠመዉ ተቃዉሞ መካከረሩም የተመሰከረበት ዕለት ነዉ።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክተኞችን አሰባስቧል።

የአሜሪካ ጦር ባግዳድ መሐል ተገትሮ የነበረዉን የሳዳም ሁሴንን ግዙፍ ሐዉልት በቡልዶዞር ገንድሶ ሲጥለዉ-ለኢራቆችም-ለተቀረዉ አለምም-የዶቼ ቬለዉ የፖለቲካ ተንታኝ ፔተር ፊሊፕ እንደሚለዉ የአዲስ ዘመን ብርቀት መስሎ ነበር።ዘንድሮ ትናንት አራት አመቱ።ሐዉልቱ ሥሩን እየለቀቀ፤ እያዘመመ-እያዘገመ ቁል ቁል ሲንሸራተት በአካባቢዉ ተሰብስቦ የነበረዉ ባግዳዳዊ ግዙፉን ድንጋይ በትናንሽ ድንጋዮች ለመዉገር የመረባረቡን፤ የመጨፈር-መቦረቁን ያሕል አንድ የአሜሪካ ወታደር የሐዉልቱን አናት በአሜሪካ ባንዲራ ለመሸፈን ያደረገዉን ሙከራ በቁጣ ጮኸት ነበር-የተቃወመዉ።

ምሳሌነቱን ያኔ የተረጎመ ከነበረ-እሱ የአዋቂዎች አዋቂ ነዉ።

ሐዉልታቸዉ ሲገነደስ ከቤተ-መንግሥታቸዉ የጠፉት ሳዳም ሁሴን ከጎሬ ተመዘዉ፤ ከወሕኒ ተጎትተዉ በገመድ ተጠልጥለዋል።ለኢራቅ የበረቀ አዲስ ዘመን ካለ ግን-እልቂት፤ ጥፋት ነዉ።

ሐዉልቱ በቦልዶዘር-እየተጎተም እያዘገመ-እየተንገዳገደ ከመሬት-እደተላተመ ሁሉ ኢራቅም አመት፣ ሁለት፣ ሰወስት አመት እያለች ከፍጅት፣ ዉድመት ድቀት ተነክራለች።በ

ሳዳም እንደተወገዱ-የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይሉት እንደነበረዉ የወራሪዎቹ ጠላቶች የባዓዝ ፓርቲ ቅሪቶች፤ ብሔረተኞች፣ ሥልጣን ያጡት ሱኒዎች ነበሩ።ወዲያዉ አልቃኢዳዎች ታከሉ።አሁን-በሱኒዎች አገዛዝ «ክፉኛ የተጨቆነ፤ የተሰቃየ አብዛሐዉ ኢራቃዊ» የሚባለዉ የሺዓ ሙስሊም አረብ ታከለበት።ትናንት የአሜሪካኖችን ባንዲራ እየረገጠ አሜሪካንን መቃወም ናጃፍን ያጥለቀለዉ ሺዓ ነበር።

ኢራቅ ሳዳም ሁሴን ከተወገዱ ወዲሕ ዲሞክራሲያዊ የሚባል ሕገ-መንግሥት ተረቆላታል።ምርጫም ተደርጓባታል።በአሜሪካኖች ፍቃድና ይሁንታ ሕገ-መንግስት ከማስረቀቅ እስከ ምርጫ ድረስ ሥልጣን ላይ የነበረዉ መንግሥት የንግድ፣ የመከላከያ እና የገንዘብ ሚንስትር ሆነዉ የሰሩት አሊ አላዊ ዛሬ አሜሪካንን የሚደግፉበት ምክንያት ሊያገኙ አልቻሉም።አላዊ በቅርቡ ባሳተሙት መፅሐፍ አሜሪካኖችን ይተቻሉ።እንዲሕ እያሉ፣-

«እንደሚመስለኝ ዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ በሙሉ የመርሕ ለዉጥ ማድረግ የሚገባት ጊዜ አሁን ነዉ።ይሕ ጊዜ ወታደራዊዉ አማራጭ በቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ማመንን ይጠይቃል።ጊዜዉ የአረጎራባች ሐገራት ጥቅም እና ፍላጎትን ከግምት ያስገባ የትርፍ-ኪሳራ መመዘኛ ከሌለ በስተቀር በሐገር ዉስጥ ያሉ የኢራቅ የፖለቲካ ቡድናት የሚያደርጉት ስምምነት ዋጋ እንደሌለዉ መቀበልን ይጠይቃል።»

ኢራቅ የሚሞት-የሚቆለዉ አሜሪካዊ ወታደር ቁጥር መናር፤ የሚከሰከሰዉ ገንዘብ መጠን መብዛት አሜሪካኖችን ከማነጋገር አልፎ-በመስተዳድራቸዉ አንፃር ለተቃዉሞ እያሳደመ ነዉ።የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማድሊን ኦል ብራይት በለፈዉ እሁድ እንዳሉት ደግሞ ኪሳራዉ ከዚሕም በላይ ነዉ።

«የጉዳዩ አሳሳቢነት በሞቱት አሜሪካዉያን ቬትናማዉያን ወይም ኢራቃዉያን ቁጥር ብቻ የሚመዘን አይደለም።ባስከተለዉ ያልታሰበ መዘዝ ጭምር እንጂ።በጠቅላላዉ በአካባቢዉ ባስከተለዉ ሁከት፤ ኢራን ባካባቢዉ እጅግ ታላቅ ሐይል አለኝ የሚል ስሜት እንዲኖራት በማድረጉ፤ አቡ ግራይብ እስር ቤት እና ሌላ ሥፍራ በተወሰደዉ እርምጃ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ በደረሰባት የሥነ-ምግባር ኪሳራ መመዘን አለበት።»

የኢራቅ የአምስተኛ አመት ጉዞ ዛሬ አንድ-ቀን አለ።